ለሀገር ጥቅም ለሠሩ መገናኛ ብዙሃን እውቅና መስጠት ተገቢና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው !

መገናኛ ብዙሃን ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ። በተለይም በለውጥ ሂደት ውስጥ የሚገኙ ሕዝቦች / ሀገራት የሚያጋጥሟቸውን የመለወጥ ፈተናዎች ተሻግረው ስኬታማ እንዲሆኑ የመገናኘ ብዙሃን ተልእኮ ወሳኝ እንደሆነ ይታመናል ።

ለውጥ በባህሪው በአዲስ እሳቤዎች የተሞላ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ፣ እነዚህ አዳዲስ እሳቤዎች በማህበረሰቡ ውስጥ ተገቢውን ትርጓሜ እና ስፍራ አግኝተው መላውን ሕዝብ የለውጥ ሃይል ሆኖ በተሻለ መነቃቃት እንዲሰለፍ በማድረግ ሂደት ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ሚና መተኪያ የሌለው ነው።

በተለይም ባለንበት የዲጅታል ዘመን እና የዲጅታል ቴክኖሎጂ እድገት ይዞት ከመጣው ዓለም አቀፍ ተግዳሮት አኳያ ፣ ለውጡና እና የለውጥ አስተሳሰቦች ሊያጋጥማቸው የሚችለውን የመረጃ ጦርነት በአሸናፊነት ለመወጣት የተቀናጀ የመገናኛ ብዙሃን ንቅናቄ መፍጠር ወሳኝ ነው።

የተለያዩ ፍላጎቶች በሚስተናገዱበት ፣ እነዚህን ፍላጎቶች በአንድም ይሁን በሌላ በሌሎች ላይ ለመጫን መገናኛ ብዙሃን ስትራቴጂክ መሣሪያ ሆነው በሚያገለግሉበት ባለንበት ዘመን ፣ ሀገራዊ የመገናኛ ብዙሃንን አቅም ማሳደግ ሆነ የብሄራዊ ጥቅሞቻችንን ማስፈጸሚያ አቅም አድርጎ መቅረጽ ተገቢ ነው::

በርግጥ በየትኛውም ዓለም የሚገኝ የመገናኛ ብዙሃን የራሱ የሆነ ዓላማ እና ተልእኮ ያለው ነው ። የእለት ተእለት እንቅስቃሴውም ይህንኑ ተልእኮውን መስፈጸም ነው ። የሥራቸው ስኬት የሚመዘነውም በግልጽ ሆነ በስውር የተቀመጠላቸውን ተልእኮ በምን ያህል ማስፈጸም ችለዋል በሚል ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሆነ በሀገር ደረጃ የሚታወቁ የመገናኛ ብዙሃን የእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸው ከዚህ የተለየ አይደለም ። ሁሉም የተፈጠሩበትን ዓላማ እና ተልእኮ ታሳቢ ባደረገ መንገድ ይሠራሉ። ከሁሉም በላይ ላሉበት ሀገር ብሄራዊ ጥቅም ከፍ ባለ መነሳሳት ይንቀሳቀሳሉ።

የሀገርን ገጽታ ከመገንባት ጀምሮ ፣በሀገር ውስጥ የሚከናወኑ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ፤ እንቅስቃሴዎቹ የተገዙበትን አስተሳሰብ ያስተዋውቃሉ ። አስተሳሰቦች ከሀገር አልፈው ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ ፣ በዓለም አቀፍ የሃሳብ ገበያ ውስጥ የሚሸጡበትን አማራጮችን ወስደው ይሰራሉ።

በተለይም ሀገር በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በምትሆንበት ፣ ብሄራዊ ጥቅም እና ክብር አደጋ ውስጥ በሚወድቅበት ወቅት ፣ ለብሄራዊ ጥቅም እና ለሀገር ክብር ዘብ ይቆማሉ። እንደ እንድ ብሄራዊ ተቋም ፣ ሃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋም ሁለንተናዊ አቅማቸውን አቀናጅተው ይንቀሳቀሳሉ።

በሀገራችን የሚገኙ የመገናኛ ብዙሃንም ከዚህ የተለየ እጣ ፈንታ የላቸውም። በሰላም ጊዜ ከተቋቋሙበት ተልእኮ አኳያ ፣ ሀገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ፣ሙያዊ ሥነምግባርን በተላበሰ መንገድ መሥራት ፤ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።

ሀገር ችግር ላይ ስትወድቅ ፤ ብሄራዊ ጥቅም እና ክብራችን አደጋ ሲያጋጥመው ፣ የተልእኮ ልዩነታቸውን አቻችለው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል ። ይህ በየትኛውም ሁኔታ ፣ ደረጃ እና አቅም ላይ ይገኙ የጋራ ተልእኳቸው ነው ። በየትኛውም ሁኔታ በሕዝብ እና በብሄራዊ ጥቅም ዙሪያ መደራደር የሚያስችል የሞራልም ሆነ የሕግ ግዴታ የለባቸውም።

ይህ ደግሞ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እንደሀገር ባጋጠሙን ፈተናዎች ወቅት በተጨባጭ ታይቷል። አብዛኞቹ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ሀገርን በመታደግ ሂደት ውስጥ ትልቅ ጉልበት ሆነው ተገልጿል። ሀገርን እና ብሄራዊ ጥቅምን በማስቀደም በቁርጠኝነት ተንቀሳቅሰዋል።

ከሁሉም በላይ የሀገር ህልውና በየትኛውም መመዘኛ ለድርድር እንደማይቀርብ በተጨባጭ ማሳየት ችለዋል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር ተከፍቶብን የነበረውን የተቀናጀ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በመከላከል ፣ ትክክለኛውን ሀገራዊ እውነታ አደባባይ በማውጣት እና ስለ ሀገር በብዙ አማራጮች ወታደር በመሆን ሙያዊ ሃላፊነታቸውን ተወጥተዋል።

በለውጡ ማግስት ፣ ብዙ ፍላጎቶች በለውጡ መንገድ ላይ ተሰልፈው ለውጡን መንገጫገጭ ውስጥ በጨመሩበት ወቅት፣ እንደ ሀገር የታየው የመገናኛ ብዙሃን ለሀገር ጥቅም እና ክብር በአንድነት የመቆም ታሪካዊ ክስተት በብዙ መልኩ እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው።

ይህ በችግር ወቅት ለሀገር የመቆም የመገናኛ ብዙሃኑ ተሞክሮ ፤ ተቋማቱ ብሄራዊ ጥቅም እና ክብርን ከሙያዊ ሥነምግባር ጋር አስተሳስሮ ፤ ለሀገር ወታደር ሆኖ መቆምን በተጨባጭ ያሳየ ፤ በቀጣይም ሀገርን ለማሻገር ለሚደረገው ትግል ተጨማሪ አቅም የሚሆን ነው።

መንግሥት ይህን የመገናኛ ብዙሃኑን በአስቸጋሪ ወቅት ለብሄራዊ ጥቅም እና ክብር ለሀገር ዘብ የመቆም ሙያዊ ቁርጠኝነት ፤ እውቅና ለመስጠት የሂደት መንገድ የሚደገፍ እና የሚበረታታ ፤ተቋማቱ እና የተቋማቱ ባለሙያዎች ለብሄራዊ ጥቅም እና ክብር በጽናት እንዲሠሩ ተጨማሪ አቅም የሚሆን ነው ።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 4/2016 ዓ.ም

Recommended For You