ሚዲያዎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አስቀድመው እውነታን መግለጥ ይጠበቅባቸዋል

ኢፕድን ጨምሮ 11 ሚዲያዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕውቅና ተሰጣቸው

አዲስ አበባ፡- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በዘጋጀው የሚዲያ ዕውቅና መርሐ ግብር የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን ጨምሮ 11 ሚዲያዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዕውቅና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያዘጋጀው የሚዲያ ዕውቅና መርሐ ግብር ትናንት በዓድዋ ሙዚየም ሲካሄድ፤ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ የአማራ ሚዲያ ኔትወርክን ጨምሮ 11 የመንግሥትና የግል ሚዲያዎች የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር ሚዲያዎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አስቀድመው ዕውነታን መግለጥ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አስጠብቀው ዘገባ የሚሠሩ መገናኛ ብዙሃን መኖራቸውን ጠቁመው፤ ሽልማት ውስጥ ባይካተቱም በተለይ የ “ኪንግ ኦፍ ዓባይ ሚዲያ” ባለቤትና የዓባይ ግድብ ተሟጋች ዑስታዝ ጀማል በሽር ለሚያከናውኑት ሥራ ምስጋና አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የሚዲያ እውቅና መርሃ ግብር መጀመሩ አንድ ርምጃ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሽልማቱ ሳንካተት ቀረን ብላችሁ የምታስቡ ካላችሁ ኢትዮጵያ በሥራችሁ ልክ ዛሬም ነገም ትከፍላችኋለች ሲሉ ተናግረዋል።

ሚዲያዎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አስቀድመው እውነታን መግለጥ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ መልክዕት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሥራችሁም የኢትዮጵያን ልክ፣ ዕድገትና ፍላጎት ማሳየት አለባችሁ ሲሉ ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳመላከቱት፤ በትንሽ ሀገር ውስጥ ትልቅ ሚዲያ አይኖርም፣ ትልቅ ሀገር ስንገነባ ልክ እንደ ህንድና ቻይና ትላልቅ ሚዲያዎች ይፈጠራሉ። ከሀገራት እድገት ነው ትልቅ ሚዲያና የጋዜጠኝነት ማንነት የሚፈጠረውና በሀገራችን ጉዳይ በጋራ እንድንሠራ አደራ እላለሁ ብለዋል።

በሌሎች አጀንዳዎች በመሳብና የተውሶ ግጥሞችን ከማስተጋባት ይልቅ ሀገራዊ አጀንዳዎችንና ብሔራዊ ጥቅሞችን የሚያጎሉ ሥራዎች ወሳኝ መሆናቸውን አንስተዋል።

በተለይ በወደብ ጉዳይ መንግሥት ያነሳውን አጀንዳ ባለመረዳትም ሆነ አውቀው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በተጻራሪ የቆሙ ሚዲያዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ይሁንና የኢትዮጵያ የወደብ ጉዳይ መቶ በመቶ የተሳካ አጀንዳ እንደነበር አስታውቀዋል።

በርካታ ሀገራት ኢትዮጵያን የሚያክል ትልቅ ሀገር ወደብ ያስፈልጋታል የሚለውን ሃሳብ ተቀብለውታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በገበያ ሕግና በፍትሃዊነት የባህር በር መጠቀም ይኖርባታል ነው ያልነው፣ አጀንዳውም ውጤታማ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

የወደብ ጉዳዩ ጊዜውን ጠብቆ የሚሳካ በመሆኑ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በተቃራኒ የቆማችሁ ሁሉ እራሳችሁን ላይ ሂስ ማድረግና መታረም ይኖርባችኋል ብለዋል።

ማንም ቢሆን የኢትዮጵያን ብልጽግና ሊያስቆመው አይችልምና ብሔራዊ ጥቅምን ያስከበረ የሚዲያ ሥራ ለማከናወን ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በልዩ ተሸላሚ ሆኗል፤ ቲክቫህ ኢትዮጵያና ድሬ ቲዩብ በሌላ መድረክ ዕውቅናው እንደሚበረከትላቸው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መሳፍንት ተፈራ ለኢፕድ የተበረከተውን ሽልማት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እጅ ተቀብለዋል።

ጌትነት ተስፋማርያም

አዲስ ዘመን ሐምሌ 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You