በክረምት የተጀመረን በጎነት ወደ ላቀ ከፍታ ለማሸጋገር ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል!

 

መልካም ሃሳብ ከበጎ ልብ ይወለዳል፤ ይሄ ከበጎ ልብ የተወለደ መልካም ሃሳብ ደግሞ በመልካም ተግባር ይገለጣል። እናም የሰው ልጆች የበጎነት መነሻው ቀና የሆነ እሳቤያቸው ውጤት፤ የበጎ ልባቸው ፍሬ ነው። ይሄ ፍሬ ደግሞ በሰው ልጆች ይገለጥ ዘንድ ደግሞ ተፈጥሯዊም፤ ማህበራዊም ግዴታዎች አሉ። ተፈጥሯዊው ግዴታ የሰው ልጅ ከፈጣሪው የተሰጠው አንዱ ኃላፊነት እርስ በእርሱ እንዲረዳዳ የሚያስገድደው ሲሆን፤ ይሄን የፈጣሪ ትዕዛዝ በመፈጸም ሂደት ውስጥ የሰው ልጆች የሚኖራቸው መልካም መስተጋብር ደግሞ በጎነት የሰው ልጆች ማኅበራዊ ኃላፊነትም ሆኖ እንዲገለጥ አድርጎታል።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያውያን ከራሳችን አልፈን ለሰዎች የምንገልጣቸው አያሌ በጎነቶች አሉን። እንግዳ ተቀባይ ሕዝቦች ስለመሆናችንም ዓለም የሚናገርልን በዚሁ መልካችን በመገለጣችን ነው። ይሁን እንጂ በአንድም በሌላም መልኩ ይሄ በጎነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ፤ በምትኩ ግለኝነትና እኛ ብቻ የሚል እሳቤ ስር እየሰደደ መሆዱን መታዘብ ይቻላል። ይሄ ደግሞ ወገን ለወገኑ ደራሽ ከመሆን ይልቅ፤ አንዱ አንዱን ገፍቶ እና ቀምቶ የሚኖርበትን ማኅበራዊ አውድ የሚፈጥር ነው።

ምንም እንኳ በዚህ መልኩ የሚገለጡ ከማኅበራዊም፣ ከተፈጥሯዊም ግዴታዎች ያፈነገጡ ተግባራት የሚስተዋሉ ቢሆንም፤ ዛሬም መልካምነት ጨርሶ ከውስጣችን ወጥቷል የሚያስብል አይደለም። ለዚህም ነው በርከት ያሉ ለመልካምነት የታጩ ግለሰቦችንና የቡድን ስብስቦችን ማየታችን። ለዚህም ነው ጊዜና ወቅትን እየጠበቁ የሚከወኑ የበጎነት ተግባራትን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ሲሄዱ ማስተዋላችን።

አሁን አሁን ደግሞ እነዚህ በጎ ተግባራት ከአንድ ወቅትና ሁለት ክዋኔ በዘለለ መልኩ እየተገለጡ ይገኛሉ። በተለይ ከ2010ሩ ሀገራዊ ለውጥ ማግስት ያለው ሁነት በእጅጉ የበጎነትን ትርጉም ያሳደገው፤ መሠረቱም በሁሉም ዘንድ እንዲደላደል ያደረገ ሆኗል። ለዚህ ደግሞ ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀምሮ የከተማ ከንቲባዎች እና የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ጭምር ከፍ ያለ ኃላፊነትን ወስደው ራሳቸውን በበጎነት መንገድ ላይ መግለጣቸው ተጠቃሽ ምክንያት ነው።

ለምሳሌ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተነሳሽነት፤ የአቅመ ደካሞችንና ድሆችን የተጎሳቆለ ቤት አፍርሶ የሰው ልጅ የሚመጥነውን ኑሮ እንዲኖር የሚያስችላቸውን ዘመናዊ ቤቶች ገንብቶ እፎይታን ከመስጠት የጀመረ ነው። ይሄ ተግባር አድጎ ዛሬ ላይ በአዲስ አበባ አቧሬ አካባቢ ያሉ ጎስቋላ መንደሮችን ከማዘመን አልፎ፤ በክልል ከተሞችና ቀበሌዎች ሳይቀር ዜጎች በየአካባቢያቸው ያሉ ደሳሳ ቤቶችን በማደስና ለወገኖቻቸው እፎይታን በመስጠት ሰፍቶና ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ጉዳዩ ቤት በማደስ ብቻ አልቀረም፤ ይልቁንም በክረምት ብቻ ተወስነው የቆዩ ቤት የማደስ፣ ደም የመለገስ፣ አቅመ ደካሞችን የማገዝ፣ ችግኝ የመትከል፣ የማስተማር፣ የትራፊክ አገልግሎት የመስጠት፣… ተግባራት ዓመቱን ሙሉ የሚከናወኑበትን ጅማሮ ማየት ተችሏል። ይሄን መሰል አካሄድ ደግሞ እንደ ሀገር ከፍ ያለ ወጪና ጉልበት የሚጠይቁ ሥራዎች ሳይቀር በበዙ በበጎ ፈቃደኞች ተሳትፎ በቀላል ወጪና በተባበረ አቅም እንዲፈጸሙ አድርገዋል።

ለአብነትም፣ የማዕድ ማጋራት ተግባር በመንግሥት በጀት ብቻ የሚከናወን ቢሆን ኖሮ የሚጠይቀው በጀት ከፍ ያለ ነበር። ይሁን እንጂ በግለሰቦችም ሆነ በባለሀብቶች ተሳትፎ መከወን መቻሉ፤ በአዲስ አበባ ብቻ ከአስር በላይ የምገባ ማዕከላት በመቶ ሺህ ለሚቆጠሩ ወገኖች በቀን አንድ ጊዜ የሚበሉበትን ዕድል ሰጥቷቸዋል። በዚህም ወገን ለወገኑ ደራሽ መሆኑን አረጋግጧል። ከምንም በላይ በራስ አቅም ማድረግና መረዳዳት እንደሚቻል እና ክብረ ነክ ከሆነው የውጭ ርዳታ ጠባቂነት አስተሳሰብ መላቀቅ የሚቻልበትን አስተሳሰብ እየፈጠረ ይገኛል።

ይሄን አይነት በጎነት ታዲያ፤ እኛ ሩህሩህ ነን፣ ለወገን ደራሽ ነን፣ እንግዳም ተቀባይ ሕዝቦች ነን፤… ለምንል ኢትዮጵያውያን ያንሱብን እንደሆን እንጂ አይበዙብንም። ምክንያቱም ስም ከግብር ይወለዳልና። ግብር ሲያምር ስም ይገዝፋል፤ በአንጻሩ ግብር ሲጎድል ስም ይኮስሳል። በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሕዝብ ያለንን በጎ እሴት፤ እንደ አማኝም ያለብንን የፈጣሪ ትዕዛዝ የመፈጸም ከፍ ያለ ኃላፊነት አለብን። ለዚህ ደግሞ ዛሬ ላይ እያበበ ያለውን የበጎነት ተግባር ማስቀጠል፤ በግርምት ገዝፎ የሚገለጠውን በጎ ተግባር በማተለቅ ሳይቆራረጥ እንዲዘልቅ የማድረግ ኃላፊነታችንን መወጣት ይጠበቅብናል!

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You