በአራቱም ማዕዘናት የተገነቡት የገበያ ማዕከላት- የዋጋ ንረትን የማረጋጋት ሚና

በተለያዩ ምክንያቶች እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት መንግሥት አማራጮችን እየወሰደ ይገኛል። ከእነዚህ አማራጮች መካከል ምግብና ምግብ ነክ ምርቶችን በህብረት ሥራ ኤጀንሲ፣ በንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን፣ በኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት እና በሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እያቀረበ መሆኑ አንዱ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ መግቢያና መውጫ በሮች በአራቱም አቅጣጫ የገበያ ማዕከላትን በመገንባት ገበያን የማረጋጋትና የማህበረሰቡን የኑሮ ጫና የማቃለል ሥራ እየሰራ ይገኛል።

በከተማዋ በአራቱም አቅጣጫ ተገንብተው ወደ ሥራ የገቡት የገበያ ማዕከላት ሸማቹንና አምራቹን በቀጥታ በማገናኘት የማህበረሰቡን የኑሮ ጫና ማቃለል ዋነኛ ዓላማቸው ነው። የገበያ ማዕከላቱ ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ አበረታች ለውጥ ተመዝግቧል። ይሁንና የገበያ ማዕከላቱን ይበልጥ ማጠናከርና ተደራሽነታቸውን በማስፋት ሸማቹ ጥራት ያላቸውን ምርቶች ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ መሸመት እንዲችል አሁንም ቀሪ ሥራዎች እንዳሉ ይታመናል።

የገበያ ማዕከላቱ የከተማው ማህበረሰብ በየጊዜው የሚገጥመውን የኑሮ ውድነት ለማቃለልና የኑሮ ውድነት ጫናውን ለመታደግ ታስበው የተገነቡ እንደመሆናቸው በየጊዜው መሻሻል እንዳለባቸው ይታመናል። በአሁን ወቅትም ከተማ አስተዳደሩ የገበያ ማዕከላቱን የበለጠ ለማሻሻልና አገልግሎታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። ከተማ አስተዳደሩ በተለይም በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የምግብና ምግብ ነክ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ የሚያደርገው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ነው። ይሁንና አቅርቦትን በማሳደግና ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ ቀሪ ሥራዎች እንዳሉ አይዘነጋም።

ከተማ አስተዳደሩ በአራቱም አቅጣጫ በከተማዋ መግቢያና መውጫ በሮች ያስገነባቸው የገበያ ማዕከላት በቂ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የማሻሻልና የማጠናከር ሥራ እየሠራ ስለመሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የንግድ ግብይትና ገበያ ልማት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍስሃ ጥበቡ ገልጸዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ከተማ አስተዳደሩ በዓለም አቀፍና በሀገር አቀፍ ሁኔታ በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰት የዋጋ ንረትን ለመቋቋምና የማህበረሰቡን የኑሮ ጫና ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሰራ ነው። ለዚህም በከተማ ውስጥ የተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ የገበያ ማዕከላት አንድ ማሳያ ናቸው። የገበያ ማዕከላቱ የማህበረሰቡን የኑሮ ውድነት ጫናን ለማቃለል አይነተኛ ድርሻ ያላቸውና በተጨባጭም ለውጥ የታየባቸው ናቸው፡፡

የገበያ ማዕከላቱ በተለይም ከፍጆታ አቅርቦት ጋር በተገናኘ አምራችና ሸማቹን በቀጥታ ማገናኘት የሚችሉበትን ዕድል ፈጥሯል። በዚህም የግብይት ሰንሰለቱ እጅግ ያጠረና ግብይቱን ማፋጠን ተችሏል። በመሆኑም በከተማ ውስጥ ያለው ሸማች በቀጥታ ከአርሶ አደሩ ጋር በመገናኘት ትኩስ የሆኑ የአትክልትና የፍራፍሬ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት አስችሎታል። በከተማዋ መግቢያና መውጫ በሮች ለተገነቡ የገበያ ማዕከላት ከተማ አስተዳደሩ ለእያንዳንዳቸው ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ አውጥቷል፡፡

የገበያ ማዕከላቱ ዋና ዓላማም ግብይቱን ማፋጠን፣ አምራችና ሸማቹን ማገናኘትና ገበያን ማረጋጋት ነው። ከዚህም ባለፈ የገበያ ማዕከላቱ ዋጋን የማረጋጋት ተልዕኮ ያላቸው ናቸው። ይህም ሲባል በምርቶች ላይ ምንም አይነት እሴት ሳይጨምሩ በየማዕከሉ ዋጋ ለመጨመር የሚደረገውን ቅብብሎሽ ማስቀረት ችለዋል። በዚህም አምራቹ ምርቱን በቀጥታ ወደ ማዕከላቱ የሚያመጣበትና ለጅምላ አቅራቢዎች የሚያቀርብበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህም ዋጋን በማረጋጋት ረገድ አበርክቶው የጎላ ነው፡፡

ከአንድ ዓመት አስቀድመው የተጀመሩት እነዚህ የገበያ ማዕከላት ተጠናክረው እንዲቀጥሉና የታለመላቸውን ዓላማ ግብ እንዲመቱ የተለያዩ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ያነሱት፤ አቶ ፍስሃ፤ በተለይም ማዕከላቱ የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የማጠናቀቅና የማጠናከር ሥራ ሲሰራ መቆየቱን አስረድተዋል፤ ለአብነትም አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን እንዲሁም አቅርቦቶችን በማሟላት አሁን ላይ የገበያ ማዕከላቱ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መስጠት መቻላቸውንና በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ሥራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የገበያ ማዕከላቱን ከማጠናከር አንጻር እየተሰራ ያለው ሥራ አበረታች አንደሆነ ሲያስረዱ፤ አሁን ላይ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ብቻ 92 መጋዘኖች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን ገልጸዋል። እሳቸው እንዳሉት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የተገነባው የገበያ ማዕከል በአሁን ወቅት ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ መግባት የቻለ ሲሆን፤ ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ባዛርና ኤግዚቢሽንም በትናንትናው ዕለት ተከፍቷል። ይህም የአካባቢው ማህበረሰብ በገበያ ማዕከሉ ተገኝቶ ጤፍን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት የሚያስችለው ይሆናል፡፡

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑ 92 መጋዘኖችን ወደ ሥራ ለማስገባትና በተሟላ መንገድ ግብይት መፈጸም እንዲችሉ ከተሰሩ ሥራዎች መካከል ባዛርና ኤግዚቢሽን አንዱ ነው። የበዛርና ኤግዚቢሽኑ ዋና ዓላማም የገበያ ማዕከሉ በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድ በስፋት እንዲታወቅና ሸማቹ በቀጥታ ከአምራቹ መሸመት እንዲችል ነው። እስካሁን ባለው ሂደትም ሸማቹ በሚጠበቀው ልክ ወደ ገበያ ማዕከሉ ሲሄድ አልታየም። ስለሆነም የገበያ ማዕከሉ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ መግባቱን ማሳወቅና ማህበረሰቡ እንዲጠቀም በሚል የተዘጋጀ ነው።

ከአቃቂ ቃሊቲ ውጭ ያሉት የገበያ ማዕከላትም በተመሳሳይ መሰረተ ልማት የተሟላላቸው መሆኑን የጠቀሱት አቶ ፍስሃ፤ ማህበረሰቡ እነዚህን የገበያ ማዕከላት አውቆ ሊጠቀምባቸው እንደሚገባ አስረድተዋል። በእነዚህ መጋዘኖች ተጨማሪ ምርቶችን ለማስገባት በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ክልሎች ያሉ አርሶ አደሮችን በማነጋገርና በማወያየት ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ ማዕከላቱ እንዲያቀርቡ መግባባት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት። በዚህ መሰረት አሁን ላይ የተለያዩ የአትክልትና የፍራፍሬ ምርቶች ወደ ገበያ ማዕከሉ እየገቡ ሲሆን፤ የሰብል ምርትም በስፋት እየቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።

የገበያ ማዕከላቱ በቂና አስተማማኝ ቦታ ያላቸው በመሆኑ ምርት በስፋት እየገባ እንደሆነ ያነሱት አቶ ፍስሃ፤ በገበያ ማዕከሉ ከሚሸጠው በተጨማሪ ከእነዚሁ ማዕከላት የተለያዩ ምርቶች ለእሁድ ገበያ ጭምር ተደራሽ እየሆነ ነው ብለዋል። ከገበያ ማዕከላቱ በተጨማሪ ሸማቹ በእሁድ ገበያ ትኩስና ጥራት ያላቸውን የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች እንዲሁም የሰብል ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያገኘ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ሸማቹ አሁን ላይ የተጫነውን የኑሮ ውድነት ከማቃለል አንጻር ትልቅ ድርሻ ያለው ስለመሆኑ አስረድተዋል።

ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በተጨማሪ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የገበያ ማዕከል ከ273 የሚልቁ ሱቆች አሉ። ያሉት አቶ ፍስሃ፤ ከ100 የሚበልጡ ሱቆች ውስጥ አምራቾችና አከፋፋዮች ገብተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ ነው የገለጹት። እሳቸው እንዳሉት፤ የገበያ ማዕከላቱ አምራችና ሸማችን በቀጥታ በማገናኘት ቀልጣፋ የግብይት ስርዓት እንዲከናወን ሆኗል። ኮልፌ የገበያ ማዕከለም እንዲሁ አምራችና ሸማችና በቀጥታ ማገናኘት የቻለ ሲሆን፤ ከ189 የሚልቁ ሱቆች ተገንብተው አሁን ላይ 100 ያህል ሱቆች ውስጥ አምራቾች ገብተው ምርቶቻቸውን በቀጥታ ወደ ሸማቹ እያደረሱ ይገኛሉ።

በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ከተገነቡ የገበያ ማዕከላት ቀዳሚው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ጋርመንት አትክልት ተራ እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ፍስሃ፤ የገበያ ማዕከሉ 554 ሱቆች ያሉት መሆኑን ገልጸው፤ አብዛኞቹ ፒያሳ ከነበረው የቀድሞ አትክልት ተራ የተነሱ ነጋዴዎች የገቡበት እንደሆነ አስረድተዋል። የገበያ ማዕከሉ ከዚህ ቀደም የጽዳት ሁኔታውን ጨምሮ የተለያዩ ቅሬታዎች ይነሱበት የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ችግሮቹን የመቅረፍ ሥራ ተሰርቷል እየተሰራም ነው ብለዋል፡፡

የገበያ ማዕከሉን ዘመናዊ በሆነ መንገድ ለመምራት እየተሰራ ሲሆን፤ በተለይም የአካባቢውን ጽዳት በተመለከተ የቆሻሻ አሰባሰብና አወጋገድ እንዲሁም የጥበቃ ስርዓቱንና አጠቃላይ የአስተዳደር ሥራው በሙሉ ለኤጀንሲ ተሰጥቷል ያሉት አቶ ፍስሃ፤ ኤጀንሲው ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ቢሮው ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል። በቁጥጥርና ክትትሉም የሚነሱ ቅሬታዎችን ቀስ በቀስ መፍታት ተችሏል። ‹‹ጋርመንት የመጀመሪያው የገበያ ማዕከል እንደመሆኑ በርካታ ሰዎች ግብት ይፈጽሙበታል። ነገር ግን ጋርመንት የመጀመሪያው የገበያ ማዕክል እንጂ ብቸኛው አይደለም›› ያሉት አቶ ፍስሃ፤ ማህበረሰቡ በከተማ ውስጥ በአራቱም አቅጣጫ የሚገኙ የገበያ ማዕከላት መኖራቸውን ተገንዝቦ በአቅራቢያው በሚገኝ የገበያ ማዕከላት በመሄድ የተለያዩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የገበያ ማዕከል በአሁን ወቅት በሙሉ አቅሙ እየሰራ ስለመሆኑ ያነሱት አቶ ፍስሃ፤ በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች እንዲሁም በእሁድ ገበያዎች ላይ ግብይት የሚፈጽሙ ነጋዴዎች በሙሉ ከገበያ ማዕከሉ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት የሚችሉ እንደሆነ ገልጸዋል። በለሚ ኩራና በኮልፌ ክፍለ ከተማም እንዲሁ ሸማቹም ሆነ የእሁድ ገበያ ነጋዴው በተመሳሳይ የሚፈልገውን ምርት በሙሉ በተመጣጣኝ ዋጋ ከአምራቾች ማግኘት ይችላል ።

አሁን ላይ በተለምዶ ጋርመንት አትክልት ተራ ተብሎ በሚጠራው የገበያ ማዕከል ከፍተኛ የሆነ የማህበረሰብ እንቅስቃሴ ስለመኖሩ ያነሱት አቶ ፍስሃ፤ ማህበረሰቡ መንግሥት የገበያ ማዕከላትን በየአካባቢው ለማስፋት እያደረገ ያለውን ጥረት ተገንዝቦ ከጋርመንት ውጭ በሚገኙ የገበያ ማዕከላት ግብይት መፈጸም ቢችል የተለያዩ ትኩስ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እንደሚችል ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮም የገበያ ማዕከላቱን ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየሰራ ሲሆን፤ በተለይም የእህል፣ የሰብልና ሌሎች ምርቶች በብዛት፣ በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ጥረት እያደረገ ይገኛል። ለዚህም በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ አምራቾችን በየአካባቢያቸው በመሄድ ማነጋገርና አብዛኞቹም ፈቃደኛ መሆናቸው ተረጋግጧል። በዚህም መሰረት ፈቃደኛ የሆኑ አምራቾችን በመለየት ምርቶቻቸውን ወደ አዲስ አበባ በማምጣት አቅራቢያቸው በሚገኙ የገበያ ማዕከላት እያስገቡ እንደሆነ አመላክተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ የገበያ ማዕከላትን ከመገንባት ጀምሮ መሰረተ ልማቶችን በማሟላትና በማጠናከር እየሰራ ባለው ሥራ አበረታች ለውጥ ተመዝግቧል ያሉት አቶ ፍስሃ፤ በተለይም የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች እንዲሁም የሰብል ምርቶች ዋጋ ቅናሽ እያሳዩ እንደሆነ ነው የገለጹት። እሳቸው እንዳሉት፤ በአሁን ወቅት የሙዝ ምርት በቀጥታ ከአርባ ምንጭ ማስገባት የተቻለ ሲሆን፤ አንድ ኪሎ ሙዝ በ27 ብር ወደ ገበያ ማዕከሉ ገብቶ ለሸማቹ ከ30 እስከ 35 ብር እየቀረበ ይገኛል።

ይህም በመደበኛ ገበያ ከ50 እስከ 60 ብር እየተሸጠ ያለውን የሙዝ ዋጋ ማረጋጋት ችሏል። ለዚህም አርሶ አደሮቹ በተመቻቸላቸው የገበያ ማዕከላት ሙዙን ማቅረብ ችለዋል። በዚህ አጋጣሚ የሙዝ ዋጋ እየቀነሰ ነው። ከሙዝ በተጨማሪም ፓፓያ በብዛት ወደ ገበያ ማዕከሉ በማስገባት አንድ ኪሎ በ13 ብር እየተሸጠ ያለበት ሁኔታ ስለመኖሩ አንስተዋል። ሽንኩርትም በተመሳሳይ ከ35 እስከ 40 ብር በኪሎ እየተሸጠ ሲሆን፤ አጠቃላይ ገበያን የማረጋጋት ሥራ ከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራውና ከፍተኛ ቁጥጥር የሚያደርግበት ሥራ እንደመሆኑ በየጊዜው ለውጦች እየተመዘገቡ ነው።

ይሁንና አልፎ አልፎ ቁጥጥሩ ላላ በሚልባቸው አካባቢዎች ላይ የምርቶች ዋጋ ከፍ የሚልበት ሁኔታ መኖሩን ያልሸሸጉት አቶ ፍስሃ፤ ቢሮው ከማህበረሰቡ በሚደርሰው መረጃ መሰረት በገበያ ማዕከላቱም ሆነ በእሁድ ገበያዎች ላይ በመዘዋወር ጥብቅ የሆነ ቁጥጥር የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም የገበያ ማዕከላቱን ተደራሽነት በማስፋት እንዲሁም በማጠናከር የተሻለ አገልግሎት ለማህበረሰቡ ለማቅረብ ይሰራል ያሉት አቶ ፍስሃ፤ በሂደት ገበያው እየተረጋጋ እንደሚሄድ ጠቅሰው፤ ሸማቹ አማካኝ በሚባል ዋጋ ምርቶችን መሸመት የሚችልበትና የኑሮ ጫናው የሚቃለልበት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል በማለት ገልፀዋል። በተለይም አርሶ አደሩ ሳይጎዳ ምርቱን መሸጥ የሚችልበት፤ ሸማቹም ባልተጋነነ ዋጋ መሸመት የሚችልበት እና የማህበረሰቡን ኢኮኖሚ ያገናዘበ ጤናማ የግብይት ስርዓት በከተማው መፍጠር እንደሚቻል ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 3/2016

 

 

Recommended For You