ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ለሰላማዊ ፖለቲካ ተገዥ መሆን ይጠበቅባቸዋል!

የሰላም ጥያቄ የሠብዓዊነት ጥያቄ ነው። ያለ ሰላም የሰው ልጅ የዕለት ተለት ሕይወቱን በአግባቡ መምራት አይችልም ፣ ዛሬን ከትናንት ፣ ትናንትን ከነገ የተሻለ አድርጎ ኑሮውን አሸንፎ ለመውጣት የሚያደርገው ማኅበረሰባዊ ጥረትም ትርጉም የሚኖረው በሰላም ነው ።

ሠላም ከግለሰብ ስብዕና ውስጥ የሚመነጭ ፣ እያደገ የቡድን፣ የማኅበረሰብ ፣ እያለ ለሰው ልጆች ብሩህ ነገዎች ተስፋ ትልቅ አቅም እንደሆነ ይታመናል። ሰው የዕውቀቱ ፍሬ እንደ መሆኑ መጠንም መንፈሳዊ ፣ ባህላዊ ሆነ ዘመናዊ አስተምሮዎች ሰላምን በማስፈን ሂደት ውስጥ ወሳኝ ናቸው።

ስለ ሰላም ከፍ ያለ መነቃቃት ውስጥ ያለ ማኅበረሰብ በአንድም ይሁን በሌላ ፣ ስለ ሰላም ያለው እውቀት ውጤት ነው። ከትናንት ሰላም ማጣቱ መማር የቻለ፣ ሰላም ማጣቱ ካስከተለበት ሁለንተናዊ ጥፋት በቀጣይ ራሱን ለመታደግ ከራሱ ጋር ቃል መግባት የቻለ ነው።

ከሰላም እጦት ከሚፈጠር ሠብዓዊና ቁሳዊ ጥፋት ፣ የታሪክ እና የሥነ ልቦና ጠባሳ በአግባቡ መማር የቻለ ፣ ለመጪ ትውልድ የተሻለ የሕይወት ተሞክሮ በመተው ፣ ትውልዶች በተሻለ የሕይወት የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ እንዲያልፉ የመፈለግ ሠብዓዊና እና ትውልዳዊ ኃላፊነትን በአግባቡ ተረድቶ መወጣት የቻለ ማኅበረሰብ መገለጫ ነው ።

ስለ ሰላም አብዝቶ ማሰብ ፣ በዚህም ሰላምን የግለሰባዊ ፣ የቡድናዊ እና የማኅበረሰባዊ ማንነት መገለጫ አድርጎ መንቀሳቀስ ፤ ራስንም ማኅበረሰብንም የመታደግ ፣ ነገዎች ከዛሬ የተሻሉ ብሩህ ሆነው እንዲታሰቡ ፣ ጤናማ ማኅበረሰብ ፣ ሀገር እና ዓለም ለመፍጠር በሚደረግ ጥረት ውስጥ መተኪያ የሌለው አቅም ነው።

እኛ ኢትዮጵያውያን በዘመናት መካከል በሰላም እጦት ምክንያት እየከፈልን ከመጣነው ውድ ዋጋ አንጻር ፣ የሰላም ጉዳይ አሁናዊ ሀገራዊ አጀንዳችን ነው። በተለይም ድህነትን ታሪክ በማድረግ ወደቀደመው የከፍታ እርከናችን ለመመለስ በዚህ ትውልድ ውስጥ የተፈጠረውን መነቃቃት ተጨባጭ ለማድረግ የሰላም ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ አጀንዳችን ነው።

በቀደመው ዘመን የሰላም እጦት ከነበርንበት ከፍታ አውርዶን የድህነት እና የኋላቀርነት ተምሳሌት አድርጎን ኖሯል። በየዘመኑ ለከፋ ሠብዓዊና ቁሳዊ ውድቀት ዳርጎናል ። ታሪካችንን የግጭት እና የጦርነት ከማድረግ ባለፈ ፣ ግጭቶችን እና ጦርነቶችን ለምደን ከጥፋት አቅማቸው ይልቅ ለሚፈጥሩት የአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት የተሰጠን ሆነን ዘመናት አስቆጥረናል።

የታሪካችን ሰፊ አካል ከሆነው ግጭት እና ጦርነት የመውጣት ፍላጎት በሕዝባችን ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ቢኖረውም ፣ የግጭት እና የጦርነት ታሪኮቻችን ከፈጠሩት የአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት መውጣት ባለመቻላችን ፤ ዛሬም በአዲስ የለውጥ መነቃቃት ባለንበት የታሪክ ምእራፍ ውስጥ ሀገራዊ ፈተና ሆኖ ዋጋ እያስከፈለን ነው።

ለዚህም በቅርቡ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተደረገው ጦርነት ፤ ከዚያም በኋላ ከጽንፈኛ ታጣቂ ኃይሎች ጋር የሚካሄዱ ግጭቶች የመላውን ሕዝባችንን የዕለት ተለት ሕይወት እየተፈታተኑት ነው። ሀገራዊ የለውጥ ተስፋዎቻችን ላይም እየፈጠሩት ያለው ጥቁር ጠባሳም በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ይህ እንደ ጥላ በየዘመኑ እየተከተለን ሕዝባችን ወደሚፈልገው ልማት እና ብልጽግና እንዳይጓዝ ተግዳሮት ከሆነብን ግጭት እና ጦርነት ለዘለቄታው በተሻለ የአስተሳሰብ ልእልና መውጣት አሁናዊ ትልቁ የቤት ሥራችን ነው። ይህ ደግሞ የተወሰነ አካል ወይም ተቋም ኃላፊነት ሳይሆን ነገን ብሩህ በሆነ ተስፋ የሚጠብቅ ዜጋ ሁሉ ኃላፊነት ነው ።

የሕዝባችን አሁናዊ ፍላጎት እንደ ትናንቱ እና ትንናንት ወዲያው ሰላም እና ሰላም ነው። የጦርነት ድምጽ መስማት ፤ ሰልችቶታል አይፈልግም። ጦርነት በቀደመው ዘመንም ሆነ ዛሬ ላይ ካስከፈለው ያልተገባ ዋጋ ፣ ከፈጠረበት የልብ ስብራት ፣ ካሳጣው ትውልድ ፤ ከፈጠረበት የሀብት ውድመት እና ካመከነበት ተስፋ አኳያ ለጦርነት የሚሆን እንጥፍጣፊ አዕምሮ ፣ ልብ እና መንፈስ የለውም ።

አሁን ያለው ትውልድ ብቻ ሳይሆን በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች ዋነኛ ፍላጎት የሆነውን ሰላም ዘላቂ አድርጎ ለማስቀጠል ፣ ሰላምን መሸከም የሚችል የፖለቲካ አስተሳሰብ እና የአስተሳሰብ መዋቅር መፍጠር ፤ ዘመኑን እና የሕዝብን ፍላጎት የሚዋጅ የሠላም አስተሳሰብ መላበስ ያስፈልጋል አዕምሮ ልብ እና መንፈስ መፍጠር ያስፈልጋል ።

ከግጭትና የጦርነት ትርክት ለመውጣት ከሁሉም በላይ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ከስሜታዊነት እና ከእልህ ወጥተው፤ ለሕዝባችን የሰላም መሻት ተገዥ ለሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ራሳቸውን አሳልፈው መስጠት ፤ በዚህም ምክንያት ሊመጣ ለሚችል ሀገራዊ ድል ራሳቸውን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል!

አዲስ ዘመን ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

 

Recommended For You