ሰዎች ሥራዎቻቸውን ለማካሄድ በሚያደርጉት ጥረት ችግሮች ሊገጥሟቸው ይችላሉ፤ ችግሮቹን ለማሸነፍ ደግሞ ከችግር መውጫዎችን ያበጃሉ። ከእነዚህ መውጫዎች መካከል የፈጠራ ሃሳቦች ይጠቀሳሉ። አብዛኛዎቹ የፈጠራ ሃሳቦችም ለችግሮች መፍትሄ ለመፈለግ በሚል የሚመነጩ መሆናቸው ይገለጻል። በተለያዩ የሙያ ዘርፎች እውቀቱ ያላቸው ባለሙያዎች የህብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታት በሚያደርጉት ጥናትና ምርምር ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራዎችን ያፈልቃሉ።
ቴክኖሎጂ በፍጥነት እያደገና እየተለዋወጠ ባለበት በዚህ ዘመን ደግሞ ከዚህም በላይ መሄድ የግድ ይላል፤ ከዘመኑ ጋር የሚሄዱ የሰው ልጅን የዕለት ተዕለት ሕይወት ሊያቀሉ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል፤ እየተሠሩም ይገኛሉ። አንድ አዲስ ሥራ ወይም ሃሳብ ሲነሳ በሃሳቡ ተመስጠው በጥልቀት አስበው፣ ይሆናል ብለው ያሰቡትን ቴክኖሎጂ ፈጥረው የሚያቀርቡ ባለሙያዎች እየተበረከቱ መጥተዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረውን የኮሪደር ልማት ተመልክተውና እሰየው! ይበል! ብለው ከልማቱ ጎን ከመቆም ባሻገር እኛስ ምን ማድረግ እንችላለን ሲሉ አውጥተው አውርደው በሙያቸው የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ የሚተጉ ግለሰቦች እና ተቋማት ብቅ ማለት ጀምረዋል። በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው 14ኛው ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ላይም ይህንኑ ሃሳብ የሚደግፉ የፈጠራ ሥራዎችን ይዘው የቀረቡ ተቋማትንና የፈጠራ ሃሳብ ባለቤቶችን ተመልክተናል።
ከእነዚህ መካከል የአዲስ ከተማ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ አንዱ ነው፤ የኮሌጁ አሠልጣኞች በኮሪደር ልማቱ የኛ ድርሻ ምንድነው? ምንስ ማበርከት እንችላለን? በማለት የፈጠራ ሥራ ሠርተዋል። አቶ ሰለሞን መንግሥቴ እና ሦስት የሥራ ባልደረቦቻቸው የአዲስ ከተማ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ አሠልጣኞች ናቸው። ከዚህ በፊት ከተለመደው የሞተር ሳይክል አይነት ለየት ያለ የሞተር ሳይክል ሠርተዋል። አዲሱ ሞተር ሳይክል በአንድ ጊዜ አምስት ሰዎችን የሚጭን ነው።
ለእነ አቶ ሰለሞን በኮሪደር ልማቱ ለሳይክል ለብቻ ተብሎ መንገድ መሠራቱ በሞተር ሳይክል ላይ የፈጠራ ስሥራ መሥራትን እንዲያሰቡና ለመሥራት እንዲችሉ መነሻ ሆኖቸዋል። መንግሥት ይህን ከሠራ ከእኛስ ምን ይጠበቃል። በሙያችን ምን መሥራት እንችላለን፤ በምንስ እናግዝ በሚል ሃሳቡን ለማመንጨት እንደቻሉ ይናገራሉ።
‹ከአዲስ ከተማ እንደመሆናችን ለየት ያለና አዲስ ሥራ መሥራት አለብን›› በሚል ሃሳብም ተስማምተን ለዚህች ውበና ማራኪ ከተማ ‹‹አዲስ ኮሪደር፣ አዲስ ቱሪዝም ፤ አዲስ ትራንስፖርት›› ያስፈልጋል ብለን በማመን ይህን የፈጠራ ሥራ መሥራት ችለናል›› ይላሉ።
አቶ ሰለሞን ቀደም ሲል በከተማዋ ያለው በመደበኛነት የሚታወቀው የሞተር ሳይክል ትራንስፖርት አይነት ቢበዛ ሁለት ሰው መያዝ የሚችል ነው ሲሉ ይጠቅሳሉ። ‹‹እኛ ይህንን ከሹፌሩ ጋር አምስት ሰዎችን እንዲይዝ አድርገን ብናሳደገው የሚል ሃሳብ ይዘን ተነሳን›› ይላሉ።
ሞተር ሳይክሉ ለትራንስፖርት አገልግሎት ብቻ የሚውል አይደለም፤ ለመዝናኛነትም እንዲውል ታሰቦ የተሠራ ነው። በአንድነት ሆነው መዝናናት የሚፈልጉ ሰዎች እየተዝናኑ ሊጓዙበትም ይችላሉ። ለምሳሌ አንድ ባጃጅ ነዳጅ ተጠቅሞ ከሹፌሩ ሌላ ሦስት ሰዎችን ነው የሚይዘው። እኛ ደግሞ ከዚህ በተሻለ ሞተር ሳይክሉን አራት ሰዎች እንዲያጓጉዝ አድርገን ሠርተነዋል በማለት ይገልጻሉ።
አዲሱን ሞተር ሳይክል አራት ኤሌክትሪካልና መካኒካል ባለሙያዎች አንድ ላይ በመሆን ነው የሠሩት። አሠልጣኞቹ ባመነጩት ሃሳብ ለመስማማት ጊዜ አልፈጀባቸውም፤ ይልቁንም አስፈላጊውን ቁሳቁስ አሰባስበው በአጭር ጊዜ ተግባር ላይ መዋል አለብን የሚለው ሃሳብ ሚዛኑ ደፍቶ ከ15ቀናት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለመሥራት ችለዋል።
ሞተር ሳይክሉ ለየት ባለ መልኩ የተሠራም ነው። አብኛዎቹ ተሽከርካሪዎች የሚጠቀሙት ነዳጅ ሲሆን፣ ይህ ሞተር ሳይክል ግን በሶላር ሲሰተምም እንዲሠራ ተደርጓል። ይህም ሁለት ጠቀሜታ አለው። አንደኛው ጠቀሜታው የአየር ብክለትን አለማስከተሉ ፣ ሁለተኛው ደግሞ በቀላል ወጪ ሊሠራ የሚችል መሆኑ ነው። ወደ ገንዘብ መቀየር ከተፈለገም ለትራንስፖርት አገልግሎት መዋል ይቻላል።
‹‹ሞተር ሳይክሉን ለመሥራት የሚያስፈልጉ ቁሳቁስን በቀላሉ ነው ያገኘነው›› ሲሉ አቶ ሰለሞን ይናገራሉ። ለሥራውም የሞተር ሳይክል ሞተር ፣ ሶላር፣ ባትሪዎች እና ብረቶች ጥቅም ላይ ውለዋል። በመደበኛነት የሚታወቁት ሞተር ሳይክሎች ያላቸው አይነት ሞተር ተገዝቶ ነው በቀላሉ በኮሌጁ የተገጣጠመው። ሞተሩ የተገዛ ሲሆን፣ ሌሎቹ በኮሌጁ ከሚገኙ ቁሳቁስ በቀላሉ የተሠሩ ናቸው። ሞተሩ የሰዓት መቆጣጠሪያም ተገጥሞለታል። በሶላር መሥራቱም በፍጥነት ከሌሎች ሞተሮች ምንም የሚለየው ነገር የለም። ማንኛውም ሞተር በሰዓት የሚጓዘውን ያህል ርቀት መጓዝ ይችላል።
ይህ የፈጠራ ሥራ በሀገር ውስጥ ምንአልባት አልተለመደም እንጂ እንደ ህንድ ባሉ ሀገራት ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚውሉ ረጃጅም ሞተር ሳይክሎች አሉ ያሉት አሠልጣኙ፤ እነዚህ ሀገራት የሰሯቸው ሞተር ሳይክሎች መነሻ እንደሆናቸው ይገልጻሉ።
‹‹ዋና የሃሳባችን መነሻ ግን እኛ ምን እናበርክት ከሚለው የመጣ ነው። ይህ ሞተር ሳይክል በሀገር ውስጥ ሲሠራ ከውጭ ካለው አንጻር እዚህ ቢሠራ አዋጭ ነው ወይ የሚለው ታይቶና ይህም አዋጭነቱ ተረጋግጦ ነው። ሞተር ሳይክሉ በሀገር ውስጥ መሠራቱ ብቻ አንድ ውጤት ነው። ምክንያቱም ከውጭ እናስመጣን ብንል በዶላር ነው የምናስመጣው። በሌላ በኩል ሀገር ውስጥ መሠራቱ የሥራ እድል ይፈጠራል›› ይላሉ ።
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ችግሮችን በመለየት የአዋጭነት ጥናት በመሥራት ወደ ፈጠራ ሥራ እንደሚገቡ ጠቅሰው፤ የፈጠራው ሥራው ለህብረተሰቡ እይታ እንዲቀርብና አስተያየቶች እንዲሰበሰቡ እንደሚደርግም ተናግረዋል። በዚህ ደረጃ የዳበረውን ይህን ቴክኖሎጂ የሚያመርተው አካል እንደሚለይና ማምረት በሚፈልገው ኢንተርፕራይዝም ሆነ ሌላ አካል ተምርቶ ለገበያ እንዲቀርብ ይደረጋል ሲሉ ያብራራሉ።
ሞተር ሳይክሉ በዋጋም ቢሆን ከውጭ ከሚመጣው አንጻር በጣም ቅናሽ እንዳለውም ያመለክታሉ። ሞተር ሳይክሉ ሲሠራ የተገዙና የጥቅም ላይ የዋሉ ቁሳቁስ ዋጋ ከቦታ ቦታ ልዩነት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ አምራቹም እንደሚገዛው ቁሳቁስ አይነትና ዋጋ የሞተር ሳይክሉ ዋጋ እንደሚወሰን ያስረዳሉ።
ሞተር ሳይክሉን በኮሌጁ ያሉ ኤሌክትሪካልና መካኒካል የትምህርት ክፍል ባለሙያዎች በአንድነት እንደሠሩት አቶ ሰለሞን ገልጸው፤ ይህ የፈጠራ ሥራ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በሚያዘጋጁት አውደርዕይ ላይ እንዲቀርብ መደረጉ ሰዎች ሃሳብ እንዲሰጡበት ለማድረግ ታሰቦ መሆኑንም ያብራራሉ። ‹‹ይህንን ቴክኖሎጂ ከሌላው ቴክኖሎጂ ጋር የሚያወዳደሩ አካላት አሉ፤ እኛ አሁንም ይህ የፈጠራ ሥራ ያለቀለት ነው ብለን አናስብም›› ያሉት አቶ ሰለሞን፤ መስተካከል ወይም መካተት አለባቸው የሚሉ በርካታ ሃሳቦች በአውደ ርዕዩ ላይ መሰጠታቸውንም ይናገራሉ። ‹‹እኛ ይህን ሞተር ሳይክል በገባን ልክ ሠርተን አቅርበናል፤ እኛ ያላየነው እና ሌሎች ባለሙያዎች የሚያዩዋቸው በርካታ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ሰዎች የተለያየ አስተያየቶች እየሰጡ፤ አምራቾች ሃሳባቸውን እየሰጡን ነው›› በማለትም ተናግረዋል።
አምራቾች እንዲህ ተደርጎ ቢሠራልን በሚል በሚያቀርቡት ሃሳብ መሠረት ዲዛይን አድርገን ሠርተን ለሚፈልገው ኢንተርፕራይዝ እናስተላልፋለን›› ይላሉ። በእነዚህ አስተያየቶች መሠረት የጎደሉትን በማሟላትና የሚሻሻሉትን በማሻሻል ቴክኖሎጂውን ባለቀለት ደረጃ ለማቅረብ ሃሳቡ እንዳላቸውም ይገልጻሉ። ኢንተርፕራይዞቹ ሞተር ሳይክሉን በሚፈልጉት ዲዛይን ከሠሩ በኋላ በሚያወጣቸው ዋጋ አምርተው ለተጠቃሚው ህብረተሰብ እንደሚያቀርቡም ይገልጻሉ።
‹‹ልክ እንደ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት የህብረተሰቡን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችሉ በርካታ ቴክኖሎጂዎችንና የፈጠራ ውጤቶችን መሥራት ይጠበቅብናል፤ ለዚህ ደግሞ እውቀቱም አቅሙም አለን›› የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ ሥራዎቹን ለመሥራት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች አቅርቦት ችግር እንዳለም ይጠቁማሉ። እነዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች ታልፈው ሥራዎች እንደሚሠሩ ጠቅሰው፣ ቴክኖሎጂዎቹን በማምረት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ላይም ክፍተቶች ይስተዋላሉ ይላሉ፤ ህብረተሰቡም በሀገር ውስጥ ቴክኖሎጂ አምኖ የመጠቀም ልምዱ እምብዛም እንደሌለው ይጠቁማሉ።
እርሳቸው እንዳሉት፤ እንደዚህ አይነት ቴክኖሎጂዎች ሲሠሩ ማበረታቻ ቢደረግ የበለጠ ለሥራው ተነሳሽነት ይፈጥራል፤ ጉልተው የሚወጡ ሥራዎች መሥራት ያስችላል። ምናልባት አሁን ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ የሚወጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማበረታቻ ሊያገኙ ይችላሉ። ሌሎች ቴክኖሎጂዎች እንዲሁ ማበረታቻ ከመስጠት በላይ ህብረተሰቡ ዘንድ ደርሰው ጥቅም ላይ ሲውሉ አይታየም። ለቴክኖሎጂው እውቅናና ማበረታቻዎች መስጠት ቴክኖሎጂውን እያሳደጉ ለመሄድ ያስችላል።
‹‹ሌሎች ያደጉ ሀገራትን ተሞክሮ ወስደን ስንመለከት እድገታቸው እውን ሊሆን የቻለው ይህንኑ መንገድ ይዘው ጠንክረው በመሥራታቸው ነው›› ያሉት አቶ ሰለሞን፤ በሀገሪቱ ህብረተሰቡም የፈጠራ ሥራዎችን በማድነቅ የማበረታታት ባህሉ ዝቅተኛ መሆኑን ያስረዳሉ። ‹‹ይህ ሞተር ሳይክል ካዩት አብዛኞቹ ፎቶ ከመነሳት በዘለለ ሲያደንቁና ሲያበረታቱ አልታዩም። ይህ ደግሞ ቴክኖሎጂ ቶሎ እውቅና አግኝቶ ጥቅም ላይ እንዲውል አያስችልም›› ሲሉ ያመለክታሉ።
ቀደም ሲልም በሀገር ውስጥ የሚሠሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጥራት የላቸውም የሚል አመለካከት እንደነበረ ጠቅሰው፣ አሁን ይህንን አመለካከት የሚያራምዱ ጥቂት እንዳልሆኑ ጠቁመዋል። ይሁንና አሁን በሀገር ውስጥ እየተሠሩ ያሉ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶች ከውጭ ከሚገቡት በተሻለ መልኩ የሚሠሩበት ሁኔታ መኖሩን ይገልጻሉ።
‹‹እኛ የፈጠራ ሃሳቡን ከማመንጨት አንስተን ሁሉንም ሠርተን ካጠናቀቅን በኋላ ለኢንተርፕራይዞች ሰጥተን እንዲያመርቱ ብናደርግ ምንም ወጭ አናስወጣቸውም፤ ሲያመርቱም ምርታቸው ቦታ ድረስ ሄደን እንደግፋለን፤ ይህ ሁሉ ሆኖም ግን አምራቾቹ ተጠቀሙበት ሲባሉ ይጠራጠራሉ›› ሲሉ አቶ ሰለሞን ያስገነዝባሉ። ‹‹በፍጥነት ገቢ የሚያስገኝላቸውን የቴክኖሎጂ ውጤት ነው እንጂ እንደዚህ አይነት ቴክኖሎጂዎችን ለመውሰድ፣ ለማለማመድና ለማስተዋወቅ ድፍረቱም የላቸውም፤ ለዚህ ሁሉ ዋናው ምክንያት የሚመስለኝ ድህነታችን ነው›› በማለት ያክላሉ።
እንደ አቶ ሰለሞን ማብራሪያ፤ በአብዛኛው ኢንተርፕራይዞች ይህ ቴክኖሎጂ ገበያ ይኖረዋል ወይም አይኖረውም ለማለት ጥርጣሬ ያድርባቸዋል። እነዚህ ኢንተርፕራይዞች የተወሰነ ጊዜ ገበያ ላይ አውጥተው፣ ገበያውንም በትክክል እስከሚገያገኙ ድረስ የሚደገፉበት ሁኔታ መኖር አለበት። ይህ ቢደረግ ወደ ገበያውን ደፍረው ለመግባት አይቸገሩም፣ ይህ ቢደረግ ቴክኖሎጂውን በሚፈለገው ልክ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ይቻል ነበር።
በአሁኑ ወቅትም እባካችሁ ወስዳችው አምርታቸው አትርፉበት ፤ ተጠቀሙበት፤ እደጉበት፤ ተለወጡበት የሚል ጥያቄ እየቀረበላቸው መሆኑን ያመለክታሉ። ‹‹እኛ ከዚህ ፈጠራ ውጤት ከውስጣዊ እርካታ ውጪ ምንም የምናገኝበት የለም። ለእነርሱ አስተላልፈን ገበያ ላይ ወጥቶ ተሸጦ ሀብት እንዲያፈሩ ግን እንፈልጋለን›› ይላሉ።
‹‹ይህ የሞተር ሳይክል ለሚፈለገው ዓላማ ውሎ በከተማዋ ሕዝቡ ሲገለገልበትና ሲጠቀምበት መመልከት ውስጣዊ እርካታ ይሰጠናል›› ይላሉ፤ በቀጣይም ህብረተሰቡን ሊጠቀሙ የሚችሉ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት ሙያዊ ግዴታቸውን እንደሚወጡ ነው ያስታወቁት።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 2/2016 ዓ.ም