በወጣት ውድድሮች ላይ መፍትሔ ያልተገኘለት የእድሜ ተገቢነት ጉዳይ

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ለ5 ቀናት በሀዋሳ ሲካሄድ ቆይቶ ከትናንት በስትያ ተጠናቋል። በቻምፒዮናው በርካታ ተስፋ ሰጪ ጉዳዮች ቢስተዋሉም የአትሌቶች የእድሜ ተገቢነት ጉዳይ መፍትሄ ያልተገኘለት ችግር ሆኖ ቀጥሏል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራ ችግሩ እንዳልተፈታና በቀጣይ እዚህ ላይ በትኩረት ለመስራት መታቀዱን ገልጿል።

ከሰኔ 25-2016 ጀምሮ ለ12ኛ ጊዜ በተካሄደው ቻምፒዮና ከመጀመሪያ ቀን አንስቶ በሁሉም የሩጫና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች አሸናፊ አትሌቶች የተለዩባቸው የፍፃሜ ፉክክሮች ሲከናወኑ ቆይተዋል። ባለፈው አርብና ቅዳሜ በተካሄዱ የፍፃሜ ውድድሮች ትኩረት የሳቡና ጠንካራ ፉክክሮችን በማስተናገድ የተጠናቀቁ ነበሩ። ቅዳሜ እለት ፍፃሜ ካገኙ ፉክክሮች አንዱ በሆነው የ10ሺ ሜትር የርምጃ ውድድር በሁለቱም ጾታ ጥሩ ፉክክር ታይቷል።

በወንዶች መካከል በተካሄደው ውድድር ይደግ ማሩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ርቀቱን በ41:47.37 በማጠናቀቅ ቀዳሚ ሲሆን፣ ምትኩ ቻሌ ከመቻል በ41:50.46 ሰአት ሁለተኛ ሆኖ ፈፅሟል። አህመድ ሀሰን ከፌዴራል ማረምያ 43:39.51 በማጠናቀቅ ሶስተኛ ሆኗል።

በተመሳሳይ በሴቶች ውድድር ህይወት አምባው ከፌዴራል ማረሚያ በ46:30.20 ሰአት አንደኛ ሆና ስታጠናቅቅ፤ ብርሃን ሙሉ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ46:35.10 ሁለተኛ፣ አባቡ አያሌው ከመቻል በ46:19.08 ሶስተኛ ሆና ፈፅማለች።

ጠንካራ ፉክክር በታየበት በወንዶች 5ሺ ሜትር ውድድር ንብረት ክንዱ ከጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ ማዕከል አንደኛ፣ ሰውመሆን አንተነህ ከሸገር ከተማ ሁለተኛ እና ኦያንስ አለሙ ከኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል። በ1500 ሜትር በሁለቱም ጾታ በተደረገዉ ድንቅ ፉክክር ሃዊ አበራ እና ጽጌ ተሾመ ከኦሮሚያ ክልል አንደኛና ሁለተኛ በመሆን ሲያጠናቅቁ፣ ሳሮን በረሀ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች። በወንዶች ደግሞ ዳዊት ቢተው ከፀደይ ባንክ፣ እንደሻው ረታ ከኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እና ሰንደል ሙሳ ከጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። በድብልቅ ሪሌይ በተደረገው ፉክክር ኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የወርቅ፣ ሲዳማ ፖሊስ የብር እና ጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ የነሐስ ሜዳሊያ በመውሰድ ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

በቡድን ጥሩነሽ ዲባባ 217 ነጥቦችን በመያዝ የአጠቃላይ የውድድሩ አሸናፊና የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ177፣ መቻል በ168 ነጥቦች 2ኛ እና 3ኛ በመሆን ፈፅመዋል።

የውድድሩ አላማ በክልሎችና ክለቦች ውስጥ ለሚገኙ ታዳጊና ወጣት አትሌቶች የውድድር እድልን በመፍጠር ሀገርን የሚወክሉና ውጤታማና ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት ነው። በተጨማሪም እአአ በነሐሴ ወር መጨረሻ በፔሩ ዋና ከተማ ሊማ በሚካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ወጣቶች ቻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች እንደሚመረጡበት ነው። ያምሆኖ ከእድሜ ተገቢነት ጋር ተያይዞ ሁሌም የሚስተዋለው ችግር ሊቀረፍ አልቻለም። ክልሎችና ክለቦች ወደ ውድድሩ ሲመጡ የአትሌቶችን እድሜ አስመርምረው እንዲመጡ ጠንካራ ማሳሰቢያ ቢደርሳቸውም በአብዛኞቹ ተግባራዊ ማድረግ አልቻሉም።

የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራ፤ ከ20 ዓመት በታች ያሉ ውድድሮች ላይ የእድሜ ችግሮች አሁንም ድረስ አለመፈታታቸውን ይናገራል። እድሜ ማጭበርበር እንደ ባህል መወሰዱን የሚናገረው ገዛኸኝ፤ ችግሩን ለመቅረፍ ክለቦች እና ፕሮጀክቶች ላይ መስራት እንደሚያስፈልግም ጠቁሟል። በስፖርት እንከን የለሽ ነገር እንደማይኖር የሚያብራራው የቀድሞው የኦሊምፒክና የአለም ቻምፒዮና የማራቶን ባለድል፤ በፌዴሬሽኑ በኩል የእድሜ ተገቢነትን በተመለከተ ምልከታ መደረጉን እና ከዚህ በፊት የተወዳደሩ ከ20 በታች አትሌቶች ተመልሰው የማይወዳደሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር ዝርዝር መረጃ እየተያዘ መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ ገዛኸኝ ገለፃ፣ ከአካዳሚዎችና ፕሮጀክቶች የሚመጡ አትሌቶች ላይ በመስራት አዳዲስ ሥርዓቶችን ለመዘርጋት ጥረት እየተደረገ ይገኛል። በዚህ ውድድር ከእድሜ ከፍ ያሉ አትሌቶች እንደተስተዋሉና ክለቦችና ፕሮጀክቶችም ተገቢ ያልሆኑ አትሌቶችን ሲያወዳድሩ ነበር። ይህ ደግሞ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ትልቅ ችግር በመሆኑ ይሄንን ከግንዛቤ ውስጥ አስገብቶና ኃላፊነት ወስዶ መስራት ይጠበቅባቸዋል።

በፌዴሬሽኑ በኩል የዓመቱ መጠናቀቂያ ውድድር በሆነው የወጣቶች ቻምፒዮና 10 ክልሎች፣ 2 ከተማ አስተዳደሮች፣ 32 ክለቦች እና ፕሮጀክቶች ተሳትፈዋል።በዚህም ቻምፒዮናው ከፍተኛ ቁጥር ያለው አትሌቶችን ያፎካከረ ሲሆን 422 ሴት እና 549 ወንድ በድምሩ 971 አትሌቶች በተለያዩ ውድድሮች ፉክክሮችን አድርገዋል።

አለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You