የከበሩ ማዕድናትን ለጌጣጌጦች ማስጌጫ

በኢትዮጵያ ለጌጣጌጥ መስሪያ የሚያገልግሉ የከበሩ ማእድናት በስፋት ይገኛሉ። እነዚህ ማእድናት በአለም አቀፍ ደረጃ በእጅጉ ተፋላጊ በመሆናቸውም በስፋት ወደ ውጭ ይላካሉ። ለውጭ ገበያ የሚቀርቡት በሁለት መንገዶች ነው። አንዱ መንገድ ምንም እሴት ሳይጨመርባቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ እሴት ተጨምሮባቸው ወይም ወደ ጌጣጌጥነት ተቀይረው የሚላኩበት ነው።

በኢትዮጵያ የጌጣጌጥ ማእድናትን በመጠቀም ጌጣጌጦችን በማምረት ለገበያ የማቅረብ ስራ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ አንደመጣ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ይገልጻሉ። ማእድናቱ ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን በጠበቀ መልኩ እንዲሁም በተለያየ መንገድ ቅርጽ ወጥቶላቸው ወደ ጌጣጌጥነት ተቀይረው በየጌጣጌጥ መሸጫ ሱቆች ውስጥ እየቀረቡ ናቸው ።

ከእነዚህ ጌጣጌጥ አምራቾች መካከል ሀና ደምሰውና እናቷ ወይዘሮ ሳባ ታፈሰ ይጠቀሳሉ። ሀና የፋርማሲ ተማሪ ብትሆንም፣ ከእናቷ ጋር በመሆን ‹‹ ኤልቤቴል ጂምስቶን ›› የተሰኘ ድርጅት ከፍተው ጌጣጌጦቹን በማምረት ለገበያ ያቀርባሉ።

ሀና ሙያውን የተማረችው ከእናቷ መሆኑን ትናገራለች። ወይዘሮ ሳባ ሙያውን በጥቃቅንና አነስተኛ ስር ሆነው በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ስልጠናውን ተከታትለዋል ።ከልጅነታቸው አንስቶ ለሙያው ፍላጎቱ የነበራቸው ሲሆን፣ ይህን ፍላጎታቸውን በእውቀት አዳብረው ወደ ገበያ እንዲያወጡት እና የሙሉ ጊዜ ስራቸው እንዲደርጉት ያደረጋቸው ደግሞ በአካባቢያቸው የሚገኙት እነዚህን ማዕድናት በተለያየ መንገድ ሰርተው እና አስጊጠው የሚያወጡ አካላት ናቸው።

በከበሩ ድንጋዮች የተጌጡ ጌጣጌጦች በሌላው አለም እጅግ ተፈላጊ መሆናቸውን ወይዘሮ ሳባ ይገልጻሉ። ጌጣጌጦቹ ኢትዮጵያ ውስጥ በጌጣጌጥ መሸጫ ሱቆች ውስጥ ብዙም ባይለመዱም፣ የከበሩ ድንጋዮች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎች ያውቋቸዋል፤ ለማጌጫነትም ይጠቀሙባቸዋል ሲሉም ያብራራሉ።

በኢትዮጵያ የሚገኙት ጌጣጌጦችን ለመስራት የሚያገለግሉት የከበሩ ማዕድናት እንደ ኦፓል ፣ ዲስፐር ፣ አጌት ፣ ኦፕሲዳል ፣ ሩቢ ፣ ሙንስቶን ፣ ኤመራልድ ያሉት ናቸው ። ‹‹ በሰዎች ዘንድ የሚታወቀው እና የሚወደደው ግን ኦፓል ነው ። ›› ሲሉ ወይዘሮ ሳባ ይገልጻሉ ። ሳፋየር በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በትግራይ ፣ ኦፓል በደቡብ ወሎ ደላንታ ላይ በሻኪሶ ደግሞ ኤመራልድ እና ሌሎች የከበሩ ድንጋዮች በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም እንደሚገኙ ይናገራሉ ።

የከበሩ ማዕደናት የራሳቸው ቀለም እና ውበት እንዳላቸው ጠቁመው፣ ወደ ጌጣጌጥ መልክ እና ቅርጽ ለማውጣት በሚያልፉት ሒደት ውስጥ የራሳቸውን ቀለም ይዘው የሚወጡ እንጂ ተጨማሪ ማስዋቢያ ቀለምን አይፈልጉም ሲሉም ያብራራሉ።

የከበረ ድንጋይን ወደጌጣጌጥ ለመቀየር ከሚያልፈው ሒደት በመጀመሪያ አብሮት ያለው አፈር እንዲራገፍ በውሀ ውስጥ መዘፍዘፍ ይሆናል። ለማለስለስ ደግሞ የተለያዩ ስድስት ደረጃዎችን ያልፋል ፤ ማእድኑ ከለሰለሰ ቅርጽ ለማውጣት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፤ ለማአድኑ የራሱ መቁረጫ ያለው ሲሆን፣ ለዚህ ተብሎ በተዘጋጀ ፌሲንግ ማሽን ላይ በማስቀመጥ ባለሙያው የራሱን ዲዛይን ያወጣል። ባለሙያዎቹ አብዛኛውን ዲዛይን በአዕሯቸው ካሰላሰሉ በኋላ ነው በማሽን ዲዛይን ወደማውጣት የሚገቡት። ጌጣጌጦቹም በቀለበት ፣ በብራስሌት ፣ በአንገት ሀብል መልክ ተሰርው ለገበያ ይቀርባሉ።

እነዚህ የከበሩ ማዕድናት በመሬት ላይ ሲገኙ ለሚያውቃቸው ሰው አልያም በአካባቢው ላለ ሰው ካልሆነ በቀር ለሌላው ሰው ተመሳስለው ሊታዩ ይችላሉ። እንደ ኤልቤቴል ጂምስቶን ያሉ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች እጅ ሲገባ እና የተለየ ቅርጽ ሲይዝ የሚኖረው ውበት ግን ልዩ ነው።

በሀገራችን በስፋት የሚገኙትን እነዚህን ማዕድናት የሌሎች ሀገር ዜጎች ለጉብኝትና ለመሳሰሉት ሲመጡ ወደ ሀገራቸው ይዘው ይሄዳሉ። ሀና እና እናቷም እነዚህን በከበሩ ማዕድናት የተጌጡ ስራዎቻቸውን ወደሌሎች ሀገራት ይልካሉ ።

ወጣት ሀና ‹‹ኢትዮጵያውያን በከበሩ ማዕድናት ስለተጌጡ መዋቢያዎች ያላቸው ምልከታ ብዙም  አይደለም›› ትላለች። ይህን ምልከታ ለመቀየር እንደሚሰሩም ጠቅሳ፣ መጀመሪያ ጌጣጌጦቹ በሰዎች ዘንድ ተገቢው እውቅና እንዲኖራቸው ማድረግ እና በጣም ቀለል ባለ መልኩ ሰዎች የሚያጌጡበትን ሁኔታ መፍጠር ላይ የመስራት ሀሳብ አለን ። ›› ስትል ታብራራለች።

በከበሩ ማእድናት የተጌጡት ጌጣጌጦች በሀገር ውስጥ በይበልጥ ተቀባይነት እንዲኖራቸው እንደምትፈልግ ጠቅሳ፣ ማዕድናቱ በተለያየ መንገድ ተጊጠው ወደ ገበያ ሲቀርቡ በግራም የሚሸጡበት ዋጋ ከፍተኛ መሆኑን አስታውቃለች። አብዛኛዎቹ ሰዎች ለራሳቸው ከመግዛት ይልቅ ለወዳጆቻቸው በስጦታ መልክ ለማበርከት የከበሩ ማዕድናትን የያዙ ጌጦችን ይመርጣሉ ስትል አብራርታ፣ ማዕድናቱ በብር ሀብል፣ በወርቅ እንዲሁም በክር ተደርገው ለገበያ ይቀርባሉ በማለት ገልጻለች ።

ወይዘሮ ሳባ የዘርፉን ተግዳሮትም ጠቁመዋል። በጂምስቶን ስራ ውስጥ አስቸጋሪ የሚባለው ግብዓቶቹን እንደልብ ማግኘት አለመቻል መሆኑን ያመለክታሉ። ኤልቤቴል ጂምስቶን ግን የራሱን ፍቃድ ይዞ ግብዓቶቹን እየተቀበለ በጌጣጌጥ ዘርፍ እንደሚሰራ ተናግረዋል። ስራውን በሀገራችን ለመስራት እንደ ተግዳሮት የሚታየው ዘመናዊ የሆኑ ማሽኖችን ማግኘት አለመቻል፣ ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቅ መሆኑ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ያለው ተቀባይነት አናሳ መሆንና ማሰልጠኛ አለመኖር እንደ ምክንያት እንደሚነሱ በስራው ላይ ያላቸውን የረጅም አመት ተሞክሮ ይዘው ወይዘሮ ሳባ አመልክተዋል።

የከበሩ ማዕድናት በተለየ መንገድ ተጊጠው ወደ ገበያ ሲቀርቡ በግራም ከሁለት ሺህ ብር ጀምሮ እንደሚያወጡ ጠቅሰው፣ ዋጋው እንደ ማዕድኑ አይነት ይለያያል ይላሉ።

እነ ወይዘሮ ሳባ እንዳሉት፤ ኤልቤቴል ጂምስቶን ከተመሰረተ ረጅም አመት ያስቆጠረ ሲሆን፣ አሁን ላይ በተለያዩ የማህበራዊ ገጾች ላይ በማስተዋወቅ ስራዎቹን ለገበያ ያቀርባል።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You