ተመራቂዎች እንኳን ደስ አላችሁ!

ይህ ወቅት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለዓመታት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ተማሪዎች በብዛት የሚመረቁበት ነው፡፡ ከዓመታት በፊት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የተቀላቀሉ ተማሪዎች በየትምህርት ተቋማቱ የተሰጣቸውን ትምህርት አጠናቀው እየተመረቁ ናቸው፡፡ በሀገሪቱ በርካታ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎች እንደሚመረቁም ይጠበቃል፡፡

ተመራቂዎች ለእዚህ ታላቅ ክብር የበቃችሁት በብዙ ድካም ውስጥ አልፋችሁ እንደመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ! አስመራቂ ተቋማትና የተማሪዎች ቤተሰቦችም እንዲሁ ተማሪዎች የሚያስፈልጓቻውን በማድረግ አብራችሁ ዓመታትን ለፍታችሁ ይህን ፍሬ ለማየት በቅታችኋልና እንኳን ደስ አላችሁ!

ተመራቂዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ ዓመታትን ስታሳልፉ ለቀጣይ ህይወታችሁ የሚውል ብዙ ዕውቀት ጨብጣችኋል፡፡ ከቤተሰብ ተለይታችሁ በአዲስ አካባቢ ፣ በአዲስ ማኅበረሰብ፣ በአዲስ የአየር ሁኔታ ውስጥ አልፋችኋል፡፡

ለጥናታችሁ የሚውል መረጃ ፍለጋ ስትወጡ ስትወርዱም እንዲሁ ከብዙዎች ጋር ተቀራርባችኋል፡፡ ከመጻሕፍት፣ ከድረ ገጽ፣ ከማኅበረሰቡ፣ ወዘተ አምባ ውስጥ ጠልቃችሁ በመግባትም ብዙ እውቀት ጨብጣችኋል፡፡ እድሜም ትምህርት ቤት ነው እንዲሉ እድሜም ጨምራችኋል፡፡ ሁሉም በሕይወታችሁ ውስጥ ትልቅ ትርጉም አላቸው፡፡

ቀጣዩ ሕይወት ወደ ሥራው ዓለም መግባት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ የሥራውን ዓለም ለመቀላቀል ደግሞ በቂ ዝግጁነት እንዳላችሁ ይታመናል፤ ሀገሪቱም በተለያዩ መስኮች እናንተን ለመቀበል ዝግጁ ናት፡፡ የመንግሥት ተቋማት እንዲሁም በሀገሪቱ በእጅጉ እየተስፋፋ የመጣው የግሉ ዘርፍም እንዲሁ በእጅጉ ይጠብቋችኋል፡፡ እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች ለመጠቀምም አሁኑኑ ዝግጁነታችሁን ማጠናከር የግድ ይላል፡፡

ወቅቱ የውድድር ነው፡፡ ዘመኑ ተቀይሯል፤ የሥራውን ዓለም መቀላቀል ውድድርን በሚፈልግበት ዘመን ላይ ትገኛለሁ፡፡ በእዚህ ውድድር ውስጥ አሸናፊ ሆናችሁ ሥራ ለመያዝ በትምህርት ወቅት ታደርጉ ከነበረውም በላይ ዝግጁነታችሁን ማጠናከርን ሊጠይቅ ይችላል፡፡

በሀገሪቱ ሰፊ የሥራ እድል ቢኖርም፣ የተመራቂዎች ቁጥርም ከዚህ በእጅጉ የላቀ እንደመሆኑ ለሁሉም ሥራ ላይገኝ ይችላል፡፡ ይህ ሳይሆን ሲቀር የሚሞከሩ ሌሎች አማራጮችም እንዳሉ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ አንዱ አማራጭ ሥራ ፈጣሪ መሆን ነው፤ ለእዚህ መዘጋጀት ይገባል፡፡

በሀገሪቱ ተቀጥሮ ከመሥራት ይልቅ የራስን ሥራ ፈጥሮ መሥራት ውጤታማ እያደረገ ያለበት ሁኔታ እንደመኖሩ የእናንተም ዝግጁነት ተቀጥሮ መሥራትን ከመሻት ባሻገር የራስን ሥራ ፈጥሮ እስከመሥራት ሊዘልቅ ይገባል፡፡ ዘመኑም፣ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ የሚጠይቀውም ይህንኑ ነው፡፡

በመሠረቱ ሥራ መምረጥ ሆኖ እንጂ በሀገሪቱ ሥራ አልጠፋም፤ የተገኘውን ሥራ ለመሥራት ግን ዝግጁ መሆን ነው የጠፋው፡፡ ይህ ዝግጁነት ሊኖር ይገባል፡፡ ከሥራ ሥራ እየተሸጋገሩ፣ ትምህርትን እያሻሻሉ፣ የራስን ሥራ እየፈጠሩ በሥራው ዓለም እንዳሻው መሆን ይቻላል፡፡

ከመንግሥት ብቻ ሥራ የሚጠበቅበት ዘመን አልፏል፤ በቀደሙት ዘመናት ተመራቂዎችን በሙሉ በመንግሥት ሥራ የማሰማራት አቅጣጫ ነበር፡፡ ይህ ይደረግ ከነበረበት መንገድ አንዱ በወቅቱ የተማረ ሰው እጥረት ስለነበር ነው፤ ይህ እጥረት በተፈታበት ሁኔታም ግን ሥራና ሠራተኛ የሚገናኙ ባልሆኑበት ሁኔታም ጭምር ተመራቂዎች በየመሥሪያ ቤቱ ይመደቡ ነበር፤ ይህ ደግሞ የተሳሳተ መንገድ ነበር፡፡

እነዚህ መንገዶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ጥለው ያለፉት መጥፎ ጠባሳ እስከ አሁንም ድረስ አብዛኞቹን ተመራቂዎች ሥራ ጠባቂ አርጓቸዋል፡፡ ይህ አመለካከት መሰበር ይኖርበታል፤ መሰበርም ጀምሯል፡፡ ተመራቂዎች በራሳቸው ሥራ እየፈለጉና እየፈጠሩም ነው፤ የተገኘውን ሥራ ሳይንቁ ሲሰሩም ይታያሉ፡፡ በቀጣይም ይሄው ነው ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት፡፡

ተመራቂዎች ማድረግ ያለባቸው ለተወዳዳሪነት ራሳቸውን ማዘጋጀት፣ ሥራ መፍጠር፣ ሥራ ሳይመርጡ መሥራት መጀመር ነው፡፡ ይህን ማድረግ ከቻሉ ከሥራና ከሀብት ጋር መገናኘቱ አልጋ ባልጋ ይሆንላቸዋል፡፡ የዘንድሮ ተመራቂዎችም ይህንን በማድረግ የሥራውን ዓለም የመቀላቀያውን አዲስ መንገድ ተያያዙት፡፡

ሌሎች ሥራ የምትፈጥሩ ተቋማት፣ በኢንተርፕረነርሽፕ ላይ የምትሠሩ አካላት ደግሞ ተማሪዎች የሥራውን ዓለም ሊቀላቀሉባቸው የሚችሉባቸውን መንገዶች በማመላከት፣ ተመራቂዎች በራሳቸው ሥራ ለመያዝ የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍ ትኩረት ሰጥታችሁ መሥራት ይኖርባችኋል፡፡ ተቋማት ሥራዎች በባለሙያ የሚሠሩበትን ሁኔታ በመፍጠር ላይ በትኩረት መሥራት ይኖባቸዋል፡፡ ሀገሪቱ ልጆቿን የምታስተምረው ሥራዎች በተማረ የሰው ኃይል እንዲከናወኑ ለማድረግ ነው፡፡ ይህን የሚመጥን ተግባር መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ዜጎች በትምህርቱ ዓለም የሚያልፉት ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ብቻ ከድህነት ለማውጣት አይደለም፡፡ ሀገርን ከድህነት ለማውጣትና በብልጽግና ጎዳና እንድትጓዝ ለማድረግም ጭምር እንጂ፡፡ ይህም በሚገባ ታውቆ ተመራቂዎች የሥራውን ዓለም የሚቀላቀሉባቸውን መንገዶች በማሳየት፣ እንዲላመዱ በማድረግ ላይ በትኩረት መሥራት ይኖርባችኋል፡፡ በድጋሚ ተመራቂዎች እንኳን አደረሳችሁ፤ እንኳን ደስ ያላችሁም!

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You