ክብር ለመምህራን!

መምህርነት የሙያዎች ሁሉ አባት ስለመሆኑ የሚከራከር የለም። ሁሉም ሙያዎች በመምህርነት ድልድይ የተሻገሩ ናቸው። ተማሪዎቻቸውን እንደ ልጆች የሚያዩ አስተማሪዎችም ለሀገር የሚጠቅሙ ዜጎችን በማፍራት በኩል ቀጥተኛ ሚና አላቸው። ብሎም ከሀገር እድገትና ሥልጣኔ አንጻር ያለጥርጥር ከፍተኛ ዋጋ ያለውን ትምህርት የሚያሳልጡ መሆናቸውም ሀገር ያወቀው ጸሐይ የሞቀው ሀቅ ነው።

መምህርነት የሙያዎች ሁሉ ምንጭ ነው። ስለዚህም የሙያዎች አባት ብለው ይጠሩታል። በየትኛውም ዘርፍ የትኛውም ልኅቀት ላይ ቢደረስ፣ እዚያ ስኬት እና ውጤት ላይ ያለመምህር ድጋፍና እገዛ አይደረስምና፤ አንድም በዚህ የተነሳ የተለየ ክብር ይሰጠዋል። በኢትዮጵያም በቀደመው ዘመን ከፍተኛ ዋጋ ከሚሰጣቸው ሙያዎች መካከል መምህርነት አንዱ እንደነበር ምስክር አያሻውም። መምህር መሆንም፣ ከመምህር መዛመድም በማኅበረሰብ ውስጥ ትልቅ ዋጋ እንደነበረው አይዘነጋም፡፡

እንደዛው ሁሉ መምህርነትን ማክበር መምህራንና መምህራትን በማዳመጥ፣ የተሻለ ክፍያን በመክፈልና ቅድሚያ በመስጠት፣ በማበረታታት፣ ተማሪዎች እንደ እናት እና እንደ አባት ቁጣና ምክራቸውን እንዲሰሙ በማድረግ ሲደገፉም ይታይ ነበር።

በተጓዳኝ መምህራንና መምህራትም የሙያውን ክብር አውቀው የበለጠ የሚያስከብሩ ለመሆን የሚጥሩ እንደነበሩ ለበርካታ ዓመታት በመምህርነት የቆዩ ባለሙያዎች ይናገራሉ። መምህራን የተማሪዎቻቸው ነገር አብዝቶ የሚጨንቃቸው፣ ጥሩ ደረጃ እንዲደርሱም የሚጥሩና የሚደክሙ ናቸው። ከዚያም አልፈው በሀገር ጉዳይ ላይም በአንድነት ሆነው ድምጽ ያሰሙበት ጊዜ በርካታ ነው። በአጠቃላይ መምህር እሱ እየቀለጠ ነገር ግን ብርሃን እየሰጠ ሀገርን የሚያበራ ሙያ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡

እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ተስፋ ላይ ያሉ ሀገራት ቀርቶ የበለጸጉ ሀገራትም እንኳ መምህር ከሚደክመው ድካም ጋር የሚመጣጠን ጥቅም ሰጥቼዋለሁ ብለው አፋቸውም ሞልተው ፣ መናጋር አይችሉም፡፡ ምክንያቱም የመመህርነት ዋጋ በምድራዊ ከፍያና ጥቅማጥቅም ብቻ ተከፍሎ የሚያልቅ አይደለምና ነው፡፡

በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አሁን ላይ ከኑሮ ውደነት ጋር በተያያዘ እንደማንኛውም ማኅበረሰብ ክፍል መምህራንም ጫና ውስጥ መሆናቸው የሚታበል ሀቅ አይደለም፡፡ ስለሆነም መምህራን የኑሮ ደረጃቸው እንዲሻሻል የመኖሪያቤት ችግራቸው እንዲቃለል የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ወዘተ ጥያቄ አላቸው፡፡ ይሄንን በተመለከተ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 27/ 2016 ዓ/ም በነበራቸው የጥያቄና መልስ ፕሮግም ላይ የሚከተለውን ተናግረው ነበር፡፡

“የመምህራን ደመወዝ ከአንዳንድ ክልሎች ጋር ተያይዞ የተነሳው የተከበረው ምክር ቤት እንዲረዳው የሚያስፈልገው፤ ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ካደረጉ ወሳኝ ምሰሶዎች መካከል ሦስቱን ብጠቅስ አርሶ አደር፣ ወታደርና መምህር ናቸው፡፡ አርሶአደር አሁን በሚደረጉ ለውጦች ማዳበሪያም እየደጎምን፣ ኩታ ገጠመም እያልን ማዳበሪያም እያቀረብን ኑሮው ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እያሳየ ነው ያለው፡፡ ወታደርና መምህር ግን ለኢትዮጵያ ደማቸውን ከመስጠት ውጭ እስካሁን ባለው ሁኔታ ከኢትዮጵያ ነገ በልጆቻችን እናየዋለን ከሚል ተስፋ ውጪ በቂ ነገር አግኝተው አያውቁም፡፡

ከማንም በላይ እውቀታቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ ሕይወታቸውን የሚገብሩ የሥራ መስኮች ሆነው ሲያበቁ በቂ ክፍያ የማያገኙ ናቸው፡፡ መምህራንና ወታደሮች ምሰሶ ሆነው ተርበው ባያስተምሩ ኖሮ አንደ ሀገርስ መቀጠል እንችል ነበር ወይ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ የተከበረው ምክር ቤት ከይቅርታ ጋር ለኢትዮጵያ መምህራንና ወታደሮች ክብር እንዲሰጥልኝ በታላቅ ትህትና እጠይቃለሁ፡፡ አመሰግናለሁ! በዚህ የሚያበቃ አይደለም፤ ብዙ እየሰጡ ስለሆነ በሚገባቸው ልክም ባይሆን በመጠኑ ማሻሻል አስፈላጊ ስለሆነ ተጨማሪ ርምጃዎች መንግሥት ይወስዳል፡፡ ” ብለዋል፡፡

ርግጥ ነው ሀገር የዜጎቿን ፍላጎት ማሟላት የምትችለው ባላት ኢኮኖሚያዊ አቅም ልክ ነው። ከዚህ የተነሳም የሀገር ምሰሶ እና ማገር የሆኑት መምህራን በሚገባቸው ልክ ተጠቃሚ አልሆኑም። ይሁንና የሀገር አቅም በፈቀደ መጠን በፌዴራል መንግሥትም ሆነ በክልሎች በትራንስፖርት አገልግሎት፣ የመኖሪያ ቤት በመክፈል አንጋፋና አርአያ ለሆኑ መምህራን ዕውቅናና ሽልማት በመስጠት የማበረታታት ተግባር ተከናውኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት መንግሥት አቅም በፈቀደ መጠን የመምህራን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቀጣይም ይሠራል። ይሁንና ይኸ ዕውን የሚሆነው ሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሲረጋገጥ መሆኑ ሊሠመርበት ይገባል።

ይሄንን ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ አሁን በተስፋ ሰጪ የዕድገት ጎዳና ላይ ትገኛለች። ለማሳያም ያህል በለውጡ ዘመን የኢትዮጵያ ጂዲፒ በእጥፍ ማደጉና የስድስት ጎረቤት ሀገራት ጂዲፒ ተደምሮ የኢትዮጵያን ያህል አለመሆኑ፤ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በኃይል ልማት በግብርና ምርቶች በተለይም በስንዴ ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን ማንሳት ይቻላል።

በአጠቃላይ የሁሉም ዜጎች ጥቅም የሚረጋገጠው ኢትዮጵያ ስትበለጽግና ሙሉ በሙሉ ከድህነት ስትላቀቅ እንደ መሆኑ ሀገር የሚለውጥ እና ብልጽግናዋን የሚያረጋግጥ ዜጋን በማፍራት ሀገራችንን ከሚመጥናት ደረጃ ላይ ለማድረስ መምህራን በከፍተኛ ጽናት ሊንቀሳቀሱ ይገባል!

አዲስ ዘመን  ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You