ቀይ ባሕር፤የኤደን ባሕረ-ሰላጤና የአረቢያ ባህር መገናኛ የሆነችው ጥንታዊቷ ሀገር የመን፣ ከስነ ምህዳራዊ አቀማመጥ አመችነት፤ከዋና ከተማ ኤደን ውበትና ሃብቷ ጋር ተዳምሮ የብዙዎች ቀልብ ማረፊያ ኖራለች።ይህ እንደመሆኑም በተለይ ቀጣናውን በጡንቻቸው ስር ለማስገባት ሌት ተቀን የሚታትሩ አቅም፤ ጉልበትና ቅርበቱ ያላቸው አገራት በየዘመኑ ለመቀራመት ባላቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።
በዚህ ዓይነቱ የመቀራመት ሂደት በእብሪተኞች ሽኩቻ ሰላምና ዜጎችዋን የሚገብሩት የመንና ህዝቦቿም ለዓመታት የከፋ ሰቆቃ ደርሶባቸዋል።በተለይ እ.ኤ.አ ከ2014 ወዲህ በተለያዩ ግንባሮች ተቧድነው በሚፋለሙ አንጃዎች ማዕከላዊ መንግሥቷን ተነጥቃ አስከፊ ቀውስ ውስጥ ገብታለች።
በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የሃውቲ አማፅያን በአንዱ የተቃውሞ ጫፍ፤በደቡብ በኩል ደግሞ የፕሬዚዳንት አብዱራቢ መንሱር ሃዲ መንግሥት ያዋክቧታል። አብድራቢ መንሱር ሃዲ የሚመሩት መንግሥት ከሳዑዲ አረቢያና አባሪዎቿ ጋር ተባድኖ በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉትን የሃውቲ አማፂያን ሌት ተቀን ይፋለማል። የሃውቲ አማፂያን ደግሞ አፀፋ የሚሉትን ማንኛውንም ምላሽ ይሰጣሉ።
በዚህ መሃልም ጥንታዊቷ ከተማ በአገራትና አንጃዎች የፖለቲካ አጀንዳ ምክንያት አሳሯን እያየች ትገኛለች።ወዳጅና ጠላት፣አሸናፊና ተሸናፊ፣ ባልለየበት በዚህ ጦርነትም ህይወት በከንቱ ይገበራል።ህዝቦቿም ጊዜ ባመጣባቸው ፈተና ቀን ጨልሞባቸዋል፡፡
ሚሊዮኖች ከሞቀ ጎጇቸው ተፈናቅለው እግራቸው ወደ መራቸው ተሰደዋል፣በረሃብ አለንጋ ተገርፈዋል። ከህዝቧ አንድ ሦስተኛው ማለትም 22 ሚሊዮኑ የአስችኳይ እርዳታ ያለህ እያለ ነው።እንደ ዓለም አቀፉ የምግብ ፕሮግራም የበላይ ኃላፊ ዴቪድ ቤዝሊ ገለፃ፤ በሀገሪቱ በየ11 ደቂቃው አንድ ህፃን በረሃብ ምክንያት ለሞት እየተዳረገ ነው።
ይህን የየመን ቀውስ ለማስቆም ታዲያ በተፋላሚ ኃይሎቹ ላይ ዓለም አቀፍ ግፊት ከማሳዳር ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶች በተለያዩ ጊዜያት ተካሂደዋል፤ይሁን እንጂ በሀገሪቱ ምንም ዓይነት ለውጥ አይታይባትም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ግፊት የሚፈልግ ቢሆንም፣እስከ አሁን የተደረገው ጫና በሚገባው ልክ ተጽዕኖ መፍጠር አለመቻሉ ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማሙበታል።
እያደር ሰቆቃው የበረታባት የመን ጨርሶ ለመውደም መቃረቧና ዜጎቿም በረሃብ፣ በጤና እጦት መርገፋቸው እያደር መባባሱ ታዲያ ዓለምአቀፉን ማህበረሰብ ማስደንገጥ ጀምሯል። በተለይ ከወራት በፊት በጋዜጠኛው ጀማል ካሾጊ ላይ የተፈጸመው ግድያ ነገሮችን በብዙ መልኩ መቀያየር የጀመረ መስሏል።
ከግድያው ጋር ተያይዞ ምዕራባውያን አገራት ለሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ጀርባቸውን በመስጠት የሪያድ መንግሥት በሰንዓ ተልዕኮ ላይ አትኩሮታቸውን ይበልጥ እንዲያደርጉ ምክንያት ሆኖ ታይቷል።በተለይ ጀርመንን፣ ዴንማርክን፤ ስዊድንን የመሳሰሉ አገራት ከሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ጋር ያላቸውን የጦር መሳሪያ ግብይት ለማቋረጥ መወሰናቸው የሪያድ መንግሥትን ሳያስደነግጠው አልቀረም።
ይህን መሰሉ አገራት ፊታቸውን ያዞሩበት እርምጃ ለየመን ቀውስ እልባት ለመስጠት ተፋላሚ ኃይሎቹ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ የሰላም ድርድር ለማድረግ ጫና ሳያሳርፉ አልቀረም።ሰሞኑን ደግሞ ለአራት ዓመታት የዘለቀውን የሀገሪቱን ጦርነት ማስቆምን ያለመ የሰላም ድርድር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስተባባሪነት ተሰናድቷል። በስዊድን በተካሄደው በዚህ የሰላም ውይይትም ሁለቱ ወገኖች ፊት ለፊት ተገናኝተው በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይተዋል።
ሁለቱን ወገኖች ለማቀራራብ መሰል ውይይት ሲዘጋጅ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።ቀደም ሲልም በሲዊዘርላንድ ውይይት ተካሂዷል፡፡በዚህም የሀውቲ አማፅያን ተደራዳሪዎች ለደህንነታችን ያሰጋናል በሚል ወደ ጄኔቫ ሳያቀኑ ቀርተዋል።ከሁለት ዓመት በፊት በኩዌት የ108 የሰላም ውይይት ቢካሄድም ስኬታማ አልነበረም።
ከእነዚህ የድርድር ሙከራዎች በመነሳትም ከሰሞኑ የሰላም ድርድር ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ውሳኔ አይጠበቅም ሲባል ቆይቷል፡፡እንደተባለው ሳይሆን ቀርቶ ድርድሩ ተስፋ ሰጪ ሆኖ ተገኝቷል፡፡በአገሪቱ የተከሰተውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመፍታት የሚያስችል ውይይት ተደርጓል፡፡ ውይይቱ በተለይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው እርዳታ ማድረስን፣ለዓመታት ተዘግቶ የቆየው የሰንዓ አየር ማረፊያ ማስከፈትን፤እስረኞች መፍታትን ዋንኛዎቹ አጀንዳዎቹ አድርጓል፡፡
በአጀንዳዎቹ ላይ የመከሩት ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎችም ከሁሉ አስቀድሞ ከአምስት ሺ በላይ እስረኞችን ለመለዋወጥ ተስማምተዋል።ይህም በሁለቱ አንጃዎች መካከል እምነት እንዲኖር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተሰምሮበታል።ከቀናት በፊት የሳዑዲ መንግሥትና የተባበሩት አረብ አሜሬትስ በዘመቻቸው በቁጥጥር ስር ያዋሉአቸውን ሃምሳ የሃውቲ አማፅያን ወደ ጎረቤት አገር ኦማን ለህክምና መላካቸውም ለዚህ ውጤት መገኘት ትልቁን ድርሻ ማበርከቱም ተመላክቷል።፡፡
የእስረኞች ልውውጡ በስኬት ደረጃ ቢጠቀስም፣ ፓርቲዎቹ ተስማምተው ለመጨባበጥ ያልቻሉባቸው አጀንዳዎችም አሉ።ከእነዚህም አንዱ የሰንዓ አውሮፕላን ማረፊያ ጉዳይ ነው።በሳዑዲ ጋሻጃግሬዎች እጅ የሚገኘው ይህ አውሮፕላን ማረፊያ በአሁኑ ወቅት ዝግ ሲሆን፤ ለሃውቲዎችም ሆነ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አውሮፕላኖች ክፍት አይደለም።
ተደራዳሪዎቹ የቀይ ባህር ክልል በሆነችው ሁዳይዳህ ወደብ ጉዳይም ሊስማሙ አልቻሉም።በሃውቲ አማፅያን የተያዘችው ይህች ወደብ የአገሪቱ ዋነኛ የኢኮኖሚ ደም ስርና ከፍተኛ ገቢ የምታስገኝ ናት፡፡ ሁለቱም ኃይሎች አንዱ ቦታውን ለማስከበርና ሌላው ለመንጠቅ ሲሉ ሲጠዛጠዙባት ቆይተዋል።
በሳዑዲ መራሹ ቡድን የሚደገፈው አንጃ ወደቡ ከሃውቲዎች ቁጥጥር ውጪ ከሆነ የየመን ሰላም ዋስትና ያገኛል ሲል፤ ሀውቲዎችና ኢራንን ጨምሮ የሀውቲዎች አፍቃሪዎች ወደቧን መስጠት የማይታሰብ ሲሉ ይገልጻሉ።
ይህ የአንጃዎቹ እሳቤ በሰላም ድርድሩ ለውጥ አልታየበትም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአንፃሩ ሰማንያ በመቶ የምግብና የህክምና ግብዓት ማስገቢያ የሆነችው ይህች ወደብ እስካለተለቀቀች ድረስ ሰብዓዊ እርዳታ የማድረሱ ሥራ ፈፅሞ የማይታሰብ መሆኑን አስታውቋል።
ይህ በሆነበት ታዲያ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች የሰላም ድርድሩ የየመንን ሰቆቃ ለመቋጨት አንድ እርምጃ ወደፊት የተሄደበት ነው ብለው ቢስማሙም ሁለቱ አንጃዎች መስማማት ያልቻሉባቸው ዋነኛ አጀንዳዎች እልባት እስካልተሰጣቸው ግን ነገሮች ታጥቦ ጨቃ እንደሚሆኑ አስረግጠው እየገለጹ ናቸው።
በዚህ ረገድ ትንታኔውን ያሰፈረው የዘዊክ ዘገባም፤የሰላም ድርድሩ ለአራት ዓመታት ለዘለቀው የየመን ቀውስ እልባት ለመስጠት ትልቅ እርምጃ መሆኑን ጠቅሶ፣አሁንም ከባድ የቤት ሥራዎች በጠረጴዛ ላይ መከማቸታቸውን አስምረውበታል።
የሴቭ ዘ ቺልድረንን ዘገባ ዋቢ በማድረግ ላለፉት አራት ዓመታት በቆየው ቀውስ 85 ሺ ህፃናት በረሃብ ምክንያት መሞታቸውን ያገለፀው ዘገባው፤በተለይ በሁዳይዳ ከተማ የሚካሄደው ጦርነት እልባት ካላገኘ የህፃናቱ ሞት እንደሚቀጥልና ሰብዓዊ ቀውሱም እንደሚባባስ መጠራጠር እንደማያስፈልግ አመልክቷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም በሁለቱ ወገኖች የሰላም እርምጃ ደስተኛ ሆኗል።ስምምነቱ ለአገሪቱ ዜጎች በመጠኑም ቢሆን ተስፋ እንደሚፈነጥቅ አምኖበታል።
የተባበሩት አረብ አሜሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንዋር ጋርጋሽ የሰላም ውይይቱ ትስፋ ሰጪና ቀውሱን ለማብረድ እንዲሁም ፖለቲካዊ መፍትሄ ለማበጀት ትልቅ እርምጃ መሆኑን በመጥቀስ፤በውጤትም ቀጣናዊ ሰላምን ለማረጋገጥ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው መናገራቸውን የሮይተርሱ ፀሐፊ አዚዝ ኤልያኮቢ ዘገባ አመላክቷል።
አንዳንድ የመናውያንም ውይይቱ ለአራት ዓመታት ለዘለቀው ቀውስ አፋጣኝ እልባት በመስጠት እቅሙ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልጸው፣ የሰላም ተስፋ ያመላከተ ጭላንጭል ይዞ መምጣቱን ግን አልካዱም።በርካታ ወገኖች ግን አሁንም በሰላም ድርድሩ ተጨባጭ ውጤት ተገኝቷል ብሎ ለመናገር አልደፈሩም።
አንዳንዶች ደግሞ መጪውን ጊዜ ካላየን አላምንም በማለት አሁንም ስጋት እንዳላቸው አስገንዝበዋል። የውይይቱን ስኬት ከመግለፅ ይልቅ ነገን መጠበቅ ግድ እንደሚል ይናገራሉ።መሰል የሰላም ድርድር አማራጮች የሚያስገኙት ውጤት እጅጉን ደካማ መሆኑን በመግለፅም፤ ለየመን ቀውስ ሁነኛው መፍትሄ የአገራት ጣልቃ ገብነትን ማስወገድ መሆኑን አስምረውበታል።
ነባራዊ ሁኔታዎች እንደሚያመላክቱትና የ2011 የኖቤል ሽልማት አሸናፊዋ የመናዊት አክቲቪስት ታዋክሎክ ካርማን እንዳለችው፤የየመን ሰላም እውን የሚሆነው በሌሎች አማራጭ አይደለም፤ሳኡዲ አረቢያ፤የተባበሩት አረብ አሜሬትስና ኢራን በአገሪቱ ጓዳ እጃቸውን መሰብሰብ ሲያቆሙ ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 2/2011
ታምራት ተስፋዬ