የታላቁ አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ መታሰቢያ የሆነው የማራቶን ውድድር ነገ ለ40ኛ ጊዜ በሃዋሳ ከተማ ይካሄዳል። ስመጥር እና ጀማሪ አትሌቶች በሚሳተፉበት ውድድር ለአሸናፊነት የሚደረገው ትንቅንቅ ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሚመሩ ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው የታሪካዊው አትሌት ሻምበል አበበ በቂላ የማራቶን ውድድር በየዓመቱ የጀግንነትና አሸናፊነት ታሪኩን ለመዘከር ታስቦ ይካሄዳል። ውድድሩ ነገ ሰኔ 30/2016 ዓ.ም ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ ለ40ኛ ጊዜ በርካታ አትሌቶችን በማሳተፍ ይካሄዳል። ውድድሩን ለማካሄድ የሚያስችለው ቅድመ ዝግጅት የተጠናቀቀ ሲሆን፤ መነሻውንና መድረሻውን ሃዋሳ ፒያሳ ገብርኤል አደባባይ በማድረግ 42 ነጥብ 195 ኪሎ ሜትሩ በሁለት ዙር የሚሸፈን ይሆናል።
አበበ ቢቂላ በዓለም መድረክ በባዶ እግሩ ሮጦ በአፍሪካ ደረጃ ፈር ቀዳጅ ድልን በመቀዳጀት ለአፍሪካውያን ስፖርተኞች ተምሳሌት መሆኑ ይታወቃል። አርዓያነቱን በመከተልም እልፍ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ታሪኩን ደጋግሞ በመጻፍ ስሙ እንዲታወስ አድርገዋል። መነሻቸውን ከጀግናውና አይበገሬው አትሌት የመታሰቢያ ውድድር ላይ ያደረጉትም ቀላል የማይባሉ ናቸው:: አንጋፋ የማራቶን ውድድር እንደመሆኑ ለዓመታት ለተተኪ አትሌቶች የሀገር ውስጥ የውድድር እድልን ከመፍጠርም በላይ የአንጋፋውን አትሌት ወኔ በማላበስም ወደር አይገኝለትም።
ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚደረጉ ውድድሮች በትልቅነቱ ከቀዳሚዎቹ አንዱና በአትሌቶች መካከል ጠንካራ ፉክክርን ከሚያስመለክቱት ተርታም የሚመደብ ነው። ዘንድሮም ትልልቅና ልምድ ያላቸውን አትሌቶች ከማሳተፉም በላይ ቀጣይ ሀገርን የሚወክሉ አትሌቶችን በፉክክር አጅቦ እንደሚያስመለክትም ይጠበቃል። ከታዋቂ አትሌቶችም መካከል በሴቶች በማራቶን እና 30 ኪሎ ሜትር ሩጫ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ሩቲ አጋ እና በሻንቄ ሙሼ ከሲዳማ ፖሊስ፣ ትዕግስት አባይቸው እና ሔቨን ኃይሉ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የሺ ካላዕዩ እና ጽጌ ኃይለስላሴ ከአትዮ ኤሌክትሪክ ይካፈላሉ። በወንዶች ደግሞ በላይ ጥላሁን እና ኃይለማርያም ኪሮስ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ጽዳት አበጀ እና ጸጋዬ ጌታቸው ከኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ጫሉ ዴሶ፣ ለሚ ብርሃኑ እና ጸጋዬ መኮንን ከኦሮሚያ ፖሊስ፣ ካሌብ ካሼቦ ከመቻል፣ ደባቦ ደቃሞ ከሲዳማ ፖሊስ እንዲሁም አዲሱ ጎበና ከፌዴራል ፖሊስ ከሚሳተፉ ወንድ አትሌቶች ጥቂቶቹ ናቸው።
ከአንድ ክልል፣ አንድ ከተማ አስተዳደር እና 17 ክለቦች የተውጣጡ አትሌቶችን ጨምሮ አንጋፋ አትሌቶችና በርካታ የግል ተወዳዳሪዎችም ይሳተፉበታል። በሴቶች 91 እና በወንድ 283 በድምሩ 374 አትሌቶች ለአሸናፊት እንደሚፎካከሩም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል:: በውድድሩ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ለሚያጠናቅቁ አትሌቶች ከሜዳሊያ በተጨማሪ እንደየደረጃቸው የገንዘብ ሽልማት የተዘጋጀላቸው ሲሆን በሁለቱም ጾታ አንደኛ ሆኖ የሚያጠናቅቅ 50 ሺ ብር፣ ሁለተኛ 25 ሺ ብር እና ሶስተኛ ደረጃ የሚወጣ አትሌት ደግሞ 20 ሺ ብር ይበረከትላቸዋል። ሽልማቱ እስከ ስምንተኛ ደረጃ የሚሰጥ ሲሆን ከ18 ሺ ብር እስከ 10ሺ ብር በቅደም ተከተሉ መሠረት የሚሸለሙም ይሆናል።
በአንጋፋ አትሌቶች መካከል የሚደረገው ፉክክር ደግሞ ከ50 ዓመት በላይ እና በታች በወንዶች፣ ከ50 ዓመት በታች በሴቶች መካከል ይካሄዳል። ሽልማቱ በዚህ ዘርፍም የተዘጋጀ ሲሆን፤ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ደረጃ ለሚወጡ አትሌቶች ከ12 ሺ ብር እስከ 2 ሺ ብር በቅደም ተከተል ያገኛሉ:: በአጠቃላይ ለሽልማት የተመደበው ገንዘብም 426 ሺ ብር እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።
የኦሊምፒክ ጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ የማራቶን መታሰቢያ ውድድር ማካሄድ የጀመረው በ1974 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ሲሆን በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞችም እየተካሄደ ዘንድሮ 40ኛው ላይ መድረስ ችሏል። ለመጀመርያ ጊዜ በተካሄደው ውድድር ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶስት ሀገራት (ኢትዮጵያ፣ ሶቭየት ህብረት እና ጂቡቲ) ተካፍለው ነበር። ውድድሩ የአበበ ቢቂላ ዓለም አቀፍ ማራቶን የሚል ስያሜን በመያዝ የውጭ ሀገራት አትሌቶችን እያሳተፈ የቆየ ቢሆንም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሀገራዊ ስያሜን በመያዝ የሻምበል አበበ ቢቂላ ማራቶን ተብሎ እየተካሄደ ይገኛል። በመጀመርያው ውድድር 51 አትሌቶች ተሳትፈው 27ቱ ብቻ ውድድራቸውን እንዳጠናቀቁም መረጃዎች ይጠቁማሉ። አንጋፋው አትሌት አበበ መኮንን ደግሞ በባዶ እግሩ ሮጦ 5ኛ ደረጃን በመያዝ ጀግናውን አትሌት መዘከር ችሎም ነበር።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም