ሄዝቦላህ የተገደሉ መሪውን ሞት ለመበቀል 200 ሮኬቶች እና ድሮኖችን ወደ እስራኤል ተኮሰ

የሌባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ከ200 በላይ ሮኬቶች እና ድሮኖችን ወደ ሰሜናዊ እስራኤል መተኮሱ ተሰምቷል። ቡድኑ ይህን ጥቃት ያደረሰው እስራኤል ከሄዝቦላህ ነባር አመራሮች መካከል አንዱን ከገደለች በኋላ ነው።

እስራኤል በጥቃቱ ምክንያት አንድ የጦር መኮንን መገደሉን ስታሳውቅ በተለያዩ ቦታዎች እሣት መነሳቱን ገልጣለች። የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል እንደለገጸው ለጥቃቱ ምላሽ ለመስጠት በደቡባዊ ሌባኖስ የሚገኙ የሄዝቦላህ “ወታደራዊ መሠረተ-ልማቶች” ላይ እርምጃ ወስዷል።

የሌባኖስ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት በእስራኤል የድሮን ጥቃት ምክንያት በሁላ ከተማ አንድ ሰው ተገድሏል።

ረቡዕ ከሰዓት የመጀመሪያውን ጥቃት የሰነዘረው ሄዝቦላህ አስቀድሞ 100 ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ተኩሷል። ይህ ጥቃት ባለፉት 9 ወራት ከታዩት እጅግ ከፍተኛው ሲሆን፣ በእስራኤል እና በታጣቂው ቡድን መካከል የለየለት ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ተሰግቷል።

በደቡባዊ ሌባኖስ ታየር ከተማ የተገደሉት የሔዝቦላ አዛዥ ሞሐመድ ኒማህ ናስር የቡድኑ ነባር አመራር የነበሩ ሲሆን፣ በእስራኤል መገደላቸው ሄዝቦላህን አስቆጥቷል።

የእስራኤል ጦር ሠራዊት እንደሚለው ናስር የሄዝቦላህን አዚዝ የተባለ ክንፍ ይመሩ የነበሩና ከደቡብ ምዕራብ ሌባኖስ ለሚደረጉ የሮኬት ጥቃቶች ተጠያቂ ናቸው። እስራኤል ነባሩ የጦር አዛዥ “በርካታ የሽብር ጥቃቶችን ፈፅመዋል” ስትል ትከሳለች።

እስራኤል፤ ናስር የሄዝቦላህ ሌላኛው ክንፍ መሪ የሆኑት ታሌብ ሳሚ አብዱላህ አጋር ናቸው የምትል ሲሆን፣ ታሌብ ባለፈው ወር መገደላቸውን ተከትሎ ሄዝቦላህ ከ200 በላይ ሮኬቶች እና ሚሳዔሎችን ወደ ሰሜናዊ እስራኤል ማስወንጨፉ ይታወሳል።

መስከረም 26 የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በእስራኤል እና ሐማስ መካከል ጋዛ ውስጥ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ በእስራኤል እና በሊባኖስ ድንበር አቅራቢያ በየቀኑ በሚባል ደረጃ የተኩስ ልውውጥ ይካሄዳል።

ሄዝቦላህ ጥቃቱን የሚፈጽመው የፍልስጤሙን ቡድን ሐማስን ለመደገፍ እንደሆነ የሚገልጥ ሲሆን፣ ይህ ቡድን በኢራን እንሚደገፍ ይታወቃል። ሄዝቦላህ እና ሐማስ በእስራኤል፣ በዩናይትድ ኪንግደም እና በሌሎች ሀገራት ሽብርተኛ ቡድኖች ተብለው ተፈርጀዋል።

እስካሁን ድረስ 400 ሰዎች ሊባኖስ ውስጥ መገደላቸው የተሰማ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ የሄዝቦላህ ተዋጊዎች ናቸው። እስራኤል ውስጥ ደግሞ 25 ሰዎች ሲገደሉ አብዛኛዎቹ ወታደሮች እንደሆኑ ተነግሯል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በሰሜናዊ እስራኤል በኩል መረጋጋትን ለማስፈን እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

“የትኛውም እኛን ሊጎዳ የመጣ መጨረሻው ሞት ነው። ይህንን በተግባር እያሳየን ነው” ሲሉ ሐሙስ ዕለት ተናግረዋል።

በእስራኤል እና ሄዝቦላህ መካከል ባለው ግጭት ምክንያት በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ በሰሜናዊ እስራኤል እና ደቡባዊ ሊባኖስ የሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎች ቀያቸው ጥለው ለመሸሽ ተገደዋል።

“የመሪያችን የተወዳጁ ሐጅ አቡ ኒማህ [ናስር] ግድያን ለመበቀል የምናደርገው እርምጃ ዛሬ በቅፅበታዊ መንገድ ተጀምሯል” ሲሉ የሄዝቦላህ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሐሺም ሳፊዲን ሐሙስ በተካሄደው የናስር ቀብር ላይ ተናግረዋል።

“ይህ ጥቃት ጠላታችን አስቧቸው በማያውቃቸው ሥፍራዎች ላይ ጭምር የሚካሄድ ነው” ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የሌባኖስ ሰላም ማስከበር ኃይል ቃል አቀባይ እንደሚሉት ከሁለቱም ወገኖች የተሰነዘሩ ጥቃቶች እየከፉ ነው ብለው እስራኤል እና ሄዝቦላህ ከዚህ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

“በጣም አሳስቦናል. . . ምክንያቱም አለመግባባት ካለ ግጭቱ ከፍ ወዳለ ደረጃ ሊሸጋገር ይችላል” ሲሉ ቃል-አቀባዩ ካንዲስ አድሪየል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት እና ዩናይትድ ስቴትስ ግጭቱ ከተስፋፋ ኢራን እና ሌሎች የቀጣናው ቡድኖች ሊቀላቀሉ ይችላሉ የሚል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የእስራኤል ባለሥልጣናት ዲፕሎማሲያዊ ድርድሮች ከከሸፉ ለጦርነት ዝግጁ መሆናቸውን በተደጋጋሚ አሳውቀዋል። የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮዋቭ ጋላንት ወታደራዊ ኃይሉ “ሊባኖስ ውስጥ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅቷል፤ አሊያም ድርድር ልናደርግ እንችላለን” ብለዋል።

ከሐማስ እጅግ የላቀ ኃይል እንዳለው የሚነገርለት ሄዝቦላህ ከእስራኤል ጋር የለየለት ጦርነት ውስጥ መግባት እንደማይፈልግ አሳውቆ፤ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የሚደረገውን ድርድር እንደሚታዘብ ገልጿል። ነገር ግን ጦርነት የሚነሳ ከሆነ “ያለምንም ሕግ” እንደሚዋጋ አስጠንቅቋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You