በጂቡቲ ሁለት ጀልባዎች ተገልብጠው 45 ሰዎች ሲሞቱ 61 ደግሞ መጥፋታቸው ተገለጸ

ከጂቡቲ የባሕር ዳርቻ አቅራቢ ሁለት የስደተኞች ጀልባዎች ተገልብጠው ቢያንስ 45 ሰዎች መሞታቸው ሲረጋገጥ 61 ሰዎች ደግሞ የደረሱበት ባለመታወቁ ፍለጋ እየተካሄደ መሆኑን ባለሥልጣናት ገለጹ።310 ሰዎችን ይዘው ከየመን የተነሱት ሁለቱ ጀልባዎች በአፍሪካ ቀንዷ ሀገር ጂቡቲ አቅራቢያ ባለው ቀይ ባሕር ላይ ተገልብጠው አደጋው መድረሱን የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ተቋም (አይኦኤም) አረጋግጧል።

የጂቡቲ የባሕር ጠረፍ ጥበቃ አባላት “እስካሁን ባለን መረጃ መሠረት 61 ሰዎች የገቡበት አልታወቀም። ሰዎቹን ለማግኘት የምናደርገው ፍለጋ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል። በዓለማችን በርካታ ስደተኞች በሕገወጥ መንገድ የሚጓጓዙባቸው ናቸው ከሚባሉ አስፈሪ የባሕር መተላለፊያዎች አንዱ የሆነው ይህ ሥፍራ በርካታ አፍሪካውያን ስደተኞች አህጉሪቱን ጥለው ለመውጣት ይጠቀሙበታል።

ከሰኞ ጠዋት ጀምሮ በአደጋው ደብዛቸው የጠፋውን ሰዎች ለማግኘት “መጠነ-ሰፊ ፍለጋ” እየተደረገ መሆኑን ያሳወቀው የጂቡቲ ባሕር ጠረፍ ጥበቃ፣ ከአይኦኤም ጋር በመተባበር እስካሁን 115 ሰዎችን ማዳን መቻሉን ገልጿል። የባሕር ጠረፍ ጥበቃው አክሎ እንዳስታወቀው ጀልባዎቹ ተገልብጠው የሰመጡት ሰሜን ምዕራብ ጂቡቲ ከምትገኘው ኾር አንጋር ግዛት 150 ሜትር ርቀት ላይ ነው።

በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ስደተኞች ቀይ ባሕርን ተጠቅመው በነዳጅ ሀብት ወደ በለፀጉ የባሕረ ሰላጤ ሀገራት ይጓዛሉ። ስደተኞቹ በሀገሮቻቸው ያሉ ግጭቶችን፣ ተፈጥዊ አደጋዎችን እና የኑሮ ውድነትን በመሸሽ ነው የሚሰደዱት።

ባለፈው ዓመት ሰኔ በተመሳሳይ የመን ድንበር አቅራቢያ ቀይ ባሕር ላይ አንዲት ጀልባ ተገልብጣ 56 ሰዎች መሞታቸውን 140 ሰዎች መጥፋታቸው ይታወሳል። የአደጋው ሰለባ የነበሩት ስደተኞች ከኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ የመጡ ነበሩ። ከሟቾቹ መካከል 31 ሴቶች እና ስድስት ሕፃናት ይገኙበታል።

ቀይ ባሕርን ተጠቅመው ከአፍሪካ ቀንድ ወደ የመን የሚጓዙ ስደተኞች ቁጥር በአውሮፓውያኑ 2022 ከነበረው 73 ሺህ ወደ 97 ሺህ 200 ማደጉን አይኦኤም አስታውቋል። አብዛኞቹ ስደተኞች በሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች አማካይነት ነው ይህን ባሕር መስመር ለማቋረጥ የሚሞክሩት። ስደተኞቹ ብዙውን ጊዜ ለአደጋ የሚጋለጡት በአነስተኛ ጀልባ በከፍተኛ ቁጥር ታጭቀው በአደገኛው ባሕር ላይ ለመጓዝ ሲሞክሩ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You