የትናንቱ የገጠር ተማሪ የዛሬው ተባባሪ ፕሮፌሰር እና ተመራማሪ ዶ/ር መሣይ ሙሉጌታ የተወለዱት፤ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ኩዩ ወረዳ ከገርበ ጉራቻ ከተማ በ5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሃሌሉ ጫሪ በምትባል የገጠር ቀበሌ ነው:: በገርበ ጉራቻ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን የተከታተሉት መሣይ ሙሉጌታ (ዶ/ር)፤ እናት እና አባታቸው ከእርሳቸው በታች አሥራ አንድ ልጆችን ወልደዉ፣ አሳድገዋል፣ አስተምረዋልም::
አቶ ሙሉጌታ ለልጃቸው ባላቸው አቅም የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላት ጥረት አድርገዋል:: መሣይ (ዶ/ር) ወላጆቻቸው ድጋፍ የሚያደርጉላቸው ባላቸው ልክ በመሆኑ ቅያሪ ልብስም ሆነ ጫማ የማይኖርበት አንዳንዴም የተቀደደ ልብስ መልበስ እና የተገነጠለ ጫማ ማድረግ ግዴታ ሆኖባቸው በማይመች ሁኔታም ቢሆንም ትምህርታቸውን ተከታትለዋል:: የዶ/ር መሣይ አባት አቶ ሙሉጌታ ደግሞ ራሳቸው ሳይማሩ ልጃቸውን ትምህርት ቤት ሔደው ከማስመዝገብ ባሻገር፤ በተለይ የገበያ ቀን ሐሙስ ሐሙስ ልጃቸው ትምህርት እየተማረ መሆኑን ቦታው ድረስ ሄደው ይከታተሉ ነበር:: ክትትላቸው እስከ ስድስተኛ ክፍል የቀጠለ ሲሆን፤ ዶ/ር መሣይ መስመር መያዛቸውን ሲያረጋግጡ አባት ክትትል ማቆማቸውን ዶ/ር መሣይ ይናገራሉ::
በእርሳቸው እምነት ገጠር መወለድ ትምህርት ለመማር ያለውን ፈተና ከፍ ቢያደርገውም፤ ጥሩ የሚሆንበት አጋጣሚም አለ:: ገጠር ተወልዶ በቀላሉ ተስፋ መቁረጥ የሚታሰብ አይደለም:: ችግሮችን መጋፈጥ የተለመደ ነው:: በሌላ በኩል መጥፎ ሁኔታው ከልብስ እና ከመማሪያ ቁሳቁስ ጀምሮ ለትምህርት የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮችን ማግኘት ቀላል አይደለም:: ቁሳቁስ ብቻ ሳይሆን፤ ትምህርትን የመከታተያ ጊዜ እጥረትም ያጋጥማል:: ሙሉ ቀን መማር እና በፈለጉት ጊዜ ማጥናት አይቻልም:: ቀን የግብርና ሥራ ማለትም ማረስ፣ አረም ማረምና እና ሰብል መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን፣ ከብት መጠበቅም ግዴታ ነበር:: ስለዚህ ትምህርት በፈረቃ ነው:: ትምህርት ከመሄድ በፊት ወይም ከትምህርት ቤት ከመጡ በኋላ የግብርና ሥራውን ማጠናቀቅ ግዴታ ነው::
አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአገር ልማት ኮሌጅ በምግብ ዋስትና እና የአደጋ ስጋትን በተመለከተ እያስተማሩ እና እየተመራመሩ የሚገኙት የዛሬው የዘመን እንግዳችን መሣይ ሙሉጌታ (ዶ/ር)፤ ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው:: በትምህርት ዘርፍ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ለመድረስ የቀራቸው አንድ ደረጃ ወይም ሙሉ ፕሮፌሰርነት ብቻ ነው:: ከእርሳቸው ጋር ከግል ሕይወታቸው ጀምረን አሁን እያስተማሩ እና እየተመራመሩበት ስላሉበት ዘርፍ በተመለከተ ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል:: መልካም ንባብ፡-
አዲስ ዘመን፡- የገጠር ሕይወት ለትምህርት ምን ያህል ምቹ ነው?
ዶ/ር መሳይ፡- ገጠር መወለድ ለትምህርት ሕይወት ጥሩ ጎንም አለው:: ጥሩ የሚያስብለው የገጠር ልጅ በብዙ ፈተና ውስጥ ስለሚያልፍ በትምህርት ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙትን የተለያዩ ፈተናዎች ለማለፍ አይቸገርም:: መጥፎ ነገሩ ግን በእኛ ጊዜ የገጠር ሕይወት በእጥረት የተሞላ ነው:: የትምህርት ቁሳቁስ እና ጊዜ ማግኘት ፈተና ነው:: ነገር ግን ለግማሽ ቀን እየሠራሁ፤ ግማሽ ቀን እየተማርኩ ባሳልፍም አሁን ያለሁበት ደረጃ ላይ መድረስ ችያለሁ::
አዲስ ዘመን፡- የገጠር ሰው በተለይ በዛ ጊዜ አንዳንድ የተሻለ ግንዛቤ ያለው ሰው ካልሆነ ልጁን ለማስተማር ዝግጁ አይደለም:: እርሶ እንዴት ወላጆችዎ ፈቅደው አስተማርዎት?
ዶ/ር መሳይ፡- ይሔ እኔንም በጣም የሚገርመኝ ጉዳይ ነው:: በቅርብ የተማረ ዘመድ አልነበረኝም:: አባቴ እንዴት ደርሶ መልስ ሃያ ኪሎ ሜትር እየሄድኩ ወንዙን፣ ተራራውን፣ ሜዳውን፣ መንደሩን እያቆራረጥኩ እንድማር እንደፈቀደልኝ አላውቅም:: ትምህርት ቤት መላክ ብቻ ሳይሆን፤ ባለው አቅም ሙሉ ድጋፍ አድርጎልኛል:: አልፎ ተርፎ ትምህርት እየተማርኩ መሆኑን ይከታተለኝ ነበር:: በአካባቢው የነበረው አንድ የገርበ ጉራቻ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ብቻ ነበር:: በዚያን ጊዜ በአካባቢውም የተማርነው ጥቂት ሰዎች ብቻ ነበርን:: ስለሆነም የአባቴ ቆራጥነት ይገርመኛል::
አዲስ ዘመን፡- በግማሽ ቀን ትምህርት ለዛውም 20ኪሎ ሜትር ደርሶ መልስ በእግር ሔደው፤ የግድ ማጥናት ያስፈልጋል:: ለዛ ደግሞ ጊዜ የለም:: እንዴት ዩኒቨርሲቲ መግባት ቻሉ?
ዶ/ር መሳይ፡– ብዙም የትምህርት ጥቅም ገብቶኝ ሳይሆን፤ እንዲሁ ገና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ስማር ከብቶችን ስጠብቅ ወይም አረም ሳርም ትንሽ አረፍ ስል አነብ ነበር:: በተለይ እስከ ስድስተኛ ክፍል የትምህርትን ጥቅም ተረድቻለሁ ለማለት አልደፍርም:: ነገር ግን አስተማሪዎች ከገበሬው ሻል ያለ ልብስ ለብሰው ስናይ፤ እኛም አድገን አዲስ ልብስ እና ጫማ እንገዛለን ከማለት ውጪ ብዙም በትምህርት እዚህ ላይ እንደርሳለን አንልም ነበር::
ነገር ግን አንድ ቀን የትጋቴ መነሻ የሆነ ይመስለኛል:: ሁለተኛ ክፍል እየተማርኩ የጠዋት ፈረቃ ተማሪ ነበርኩ:: ወደ ሁለት ሔክታር የስንዴ ማሳ አዝመራችንን ወፎች እምሽክ አድርገው በሉት:: ከላዩ ላይ አንድ ኪሎ እንኳ ማንሳት አልተቻለም:: እናቴ ይዛኝ እርሳው ሔዳ ‹‹ይህንን አዝመራ ወፍ በልቶብናል:: አንተ ትምህርት ቤት ባትሔድ ትጠብቀው ነበር:: አሁን ግን ተበልቶ አልቋል፤ ስለዚህ ከሁለቱም ያጣን እንዳንሆን በትምህርትህ መጠንከር አለብህ::›› ማለቷ ለእኔ ትልቅ የመነሻ ምክንያት ሆኖኛል የሚል ግምት አለኝ::
በተጨማሪ እድሜ እየጨመረ 8ኛ ክፍል አካባቢ ስደርስ ዩኒቨርሲቲ እየገቡ ለእረፍት የሚመጡ ወጣቶችን ማየት ስጀምር፤ የትምህርት ጥቅም ገባኝ:: ከፍ ማለት እንደሚቻል ሳውቅ በደንብ ማጥናት ጀመርኩ:: 8ኛ ክፍል 100 ፐርሰንት በማምጣቴ አስተማሪዎቼ እጅግ ተደሰቱ:: ያ የበለጠ አነቃቃኝ፤ የ12ኛ ክፍልን ብሔራዊ የማጠቃለያ ፈተና ስወስድ የጊዜውን ጥሩ ውጤት 3 ነጥብ 4 አምጥቻለሁ:: የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ነበርኩ:: ዩኒቨርሲቲ ልገባ ስል ቀደም ሲል መንግስት ሥራ ይመድብበት የነበረበት መንገድ ቀርቶ ከአሁን በኋላ ከመምህርነት ውጪ ተመራቂው ራሱ ሥራ ፈልጎ መግባት አለበት የሚል ወሬ መወራት ጀመረ:: ስለዚህ ኮተቤ መምህራን ኮሌጅን አንደኛ ምርጫዬ አድርጌ ሞልቼ እዛ ገባሁ::
በባህሪዬ ምንም ነገር አያታልለኝም:: በአብዛኛው ጊዜዬን የማጠፋው በማንበብ ነበር:: ስለዚህ ኮተቤ በጣም ጥሩ ውጤት በማምጣቴ በ1989 ዓ.ም ዲግሬዬን የወርቅ ተሸላሚ ሆኜ አጠናቀቅኩ:: ትምህርቴ በጂኦግራፊ እና አካባቢ ጥናት ላይ የተመሠረተ ሲሆን፤ ወዲያው ጅማ መምህራን ኮሌጅ ማስታወቂያ ሲያወጣ ተወዳድሬ ከብዙ አመልካቾች መካከል አልፌ በረዳት ሌክቸረርነት ተቀጠርኩ::
በ1992 ዓ.ም እና በ1993 ዓ.ም ሁለተኛ ዲግሪ ለመማር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጂኦግራፊ እና በአካባቢ ጥናት ት/ት ክፍል አጠናቀቅኩ:: በመመረቂያ ፅሁፍ ካገኘሁት የA+ ውጤት በተጨማሪ አጠቃላይ ውጤቴ እጅግ በጣም ምርጥ የሚባል ነበር::
አዲስ ዘመን፡- መጀመሪያ ጂኦግራፊ በድጋሚ ጂኦግራፊ በአጠቃላይ የመልከአ ምድር ጉዳይ ላይ ያተኮሩበት ጉዳይ ምንድን ነው?
ዶ/ር መሳይ፡- በአጋጣሚ ነው:: ምክንያቱም ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ስገባ የነበሩት የትምህርት ክፍሎች አማርኛ፣ ሒሳብ፣ እንግሊዘኛ፣ ስፖርት ሳይንስ፣ ታሪክ እና ጂኦግራፊ ብቻ ነበሩ:: ለእኔ የተሻለ ይሆናል ብዬ የገመትኩት ጂኦግራፊ ነው:: ሌሎች እንደ ኢኮኖሚክስ ያሉ የት/ት ክፍሎች ቢኖሩ ኖሮ ምናልባት ወደ ሌሎች እሳብ ነበር:: በእርግጥ ገጠር በማደጌ የመሬት አቀማመጥ ያስደስተኛል:: ምናልባት ያ ትንሽ ስቦኛል ብዬ እገምታለሁ:: ዋናው ጉዳይ ግን አማርኛ እንዳልማር አፌን የፈታሁት በአፋን ኦሮሞ በመሆኑ ትንሽ ያስቸግረኝ ነበር:: እንግሊዘኛም ያው ገጠር አድጌ ከከተማ ልጆች ጋር መወዳደር ይከብደኛል ብዬ አሰብኩና ተውኩት:: በምንም መልኩ የተሻለ የሚሆነው ጂኦግራፊ ነበር ብዬ አሰብኩና ገባሁ:: በዚህም አልከፋኝም:: ምክንያቱም በጥሩ መምህራን በጥሩ ሁኔታ መማር ብቻ ሳይሆን መድረስ የምፈልገው ቦታ ሁሉ ደርሻለ ሁ::
የሁለተኛ ድግሪዬን ከጨረስኩ በኋላ ወደ ጅማ አልተመለስኩም:: የግል ተቋማት ጋር አዲስ አበባ ውስጥ መስራት ጀመርኩ:: ነገር ግን ብዙም ሳልቆይ መልሼ ወደ ዩኒቨርሲቲ መምህርነት መመለስ ፈለግኩ:: ስለዚህ አዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተወዳድሬ ተቀጠርኩ:: በዛ ጊዜ ዩኒቨርሲቲው እንደ አሁኑ ኢንጂነሪንግ እና ቴክኖሎጂ ብቻ አልነበረም:: የማህበረሰብ (ሶሻል) ሳይንስ ትምህርቶች ነበሩት:: ለአንድ ዓመት ካስተማርኩ በኋላ የ3ኛ ዲግሪ የ(ፒ ኤች ዲ) ዕድል መጣ:: በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጆኢግራፊ እና ጥናት ትምህርት ክፍል ሶሽዮ- ኢኮኖሚ ዴቨሎፕመንት ፕላንግ (specialization in Socioeconomic Development Planning) ተማርኩ::
የማስትሬትና የዶክትሬት ዲግሪ የመመረቂያ ፅሁፌን የሰራሁት የምግብ ዋስትና ላይ አተኩሬ ነው:: በተጨማሪ የአካባቢ ሳይንስ ላይ በማተኮር አ/አ/ዩ ሳይንስ ፋኩሊቲ ተጨማሪ ሁለተኛ ዲግሪ ኮርሶችን ወስጃለሁ:: እንዲሁ የተለያዩ መስሪያ ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች እየሠራሁ ከ10 ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአገር ልማት ኮሌጅ በእኔ ሙያ የሰው ኃይል ይፈልጉ ስለነበር፤ በተባባሪ ፕሮፌሰርነት ተቀጠርኩኝ::
አሁን በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ አስተምራለሁ፣ የድህረ ምረቃ ተማሪዎችን አማክራለሁ፣ የምርምር ሥራን እሠራለሁ:: እነዚህም በሀገር ልማት ኮሌጅ ሁለት ፕሮግራሞች (ማለትም የምግብ ዋስትና ጥናት እና የአደጋ ስጋት ፕሮግራሞች) እና በሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ ውስጥ ኮርስ አስተምራለሁ፣ ተማሪዎችን አማክራለሁ:: የአደጋ ስጋት ፕሮግራም ላይ ፕሮግራሙን ከመቅረፅ ጀምሮ፣ ከማስተማር እንዲሁም ከመመራመር ጀምሮ ተማሪዎችን በማማከር ላይ እሠራለሁ::
አዲስ ዘመን፡- ከኢትዮጵያ ውጭ የት ሀገር ተማሩ ወይንም ሠሩ?
ዶ/ር መሣይ፡– አዎ! ውጪ ሀገር ከትምህርት፣ ሥልጠና እና ምርምር ጋር በተያያዘ የተለያዩ አገራት ሄጃለሁ:: በውጪው ዓለም እንደተማሪ፣ እንደ አስተማሪም ሆነ እንደ ተመራማሪ ሠርቻለሁ:: ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ ጁሁዋንስበርግ ዩኒቨርሲቲ በተደጋጋሚ ተመላልሼ ሰርቻለሁ:: ኬኒያ ሞህ ዩኒቨርሲቲም እንደ ተመላላሽ ምሁር (Visiting Scholar) አገልግያለሁ:: ደቡብ ኮሪያ፣ ቻይና፣ ኡጋንዳ፣ ሱዳን እና ሌሎች ሀገሮች ከማስተማርና ከምርምር ጋር በተያያዘ የተጋበዝኩባቸው ቦታዎች ናቸው:: የእኛ አገር ብቻ ሳይሆን የሌሎች አገሮችንም የትምህርት እንቅስቃሴ እና የማህበረሰቡን እንቅስቃሴ ማየት አስፈላጊ በመሆኑ፤ የተለያዩ አካባቢዎች ከማስተማር በተጨማሪ የምርምር ፅሁፎችን ማቅረብ አስፈላጊ ነው:: በዑጋንዳ እና በኬኒያ ጉዳዮች ላይ አርቲክሎችን አሳትሜያለሁ::
አዲስ ዘመን፡- የአደጋ ስጋት ፕሮግራምን በት/ት ክፍላችው እንዴት ተቀረፀ?
ዶ/ር መሳይ፡– የአደጋ ስጋት ፕሮግራም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊትም በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ነበር:: ለምሳሌ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲን እና ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲን እንዲሁም ሰመራ ዩኒቨርሲቲን መጥቀስ ይቻላል:: አዳማም እያለሁ ከዚህ ጋር ተቀራራቢ የሆነ ትምህርት አስተምር ነበር:: አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስመጣ እኔ ያለሁበት ኮሌጅ በፍላጎቱ የአደጋ ስጋት ፕሮግራም እንዲቀረፅ ሃሳብ አቀረበ:: በአጋጣሚ እኔ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ከዚሁ ጉዳይ ጋር የተያያዘ የማስተማር ሥራ እሰራ ስለነበር የፕሮግራሙ ቀረፃ ሲከናወን የኮሚቴው አባል ሆንኩኝ:: አንዱ ፕሮግራም ላይ ሰብሳቢም ነበርኩ:: ከተለያዩ ድርጅቶች ድጋፍ ተደርጎልን ፕሮግራሙን ቀረፅን:: አሁን በእዚሁ ዘርፍ የሶስተኛ ዲግሪያቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች ሁለተኛ ዓመት ላይ ደርሰዋል::
የሁለተኛ ዲግሪ ላይ ደግሞ ፕሮግራሙ ተቀርፆ አልቆ ለሚመለከተው አካል ካስገባን በኋላ፤ እየተጠባበቅን ነው:: እንደሚታወቀው አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ሆኗል:: ትንሽ ከእርሱ ጋር በተያያዘ አንዳንድ የምናስተካክላቸው ነገሮች ይኖራሉ እንጂ ፕሮግራሞቹ ይኖራሉ::
አዲስ ዘመን፡- የአደጋ ስጋት ዙሪያ ከማስተማር ባሻገር ምን ሠራችሁ?
ዶ/ር መሳይ፡- በተለይ የራሴን ሥራ ስገልፅ፤ ከላይ እንደገለፅኩት መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የምርምር ሥራዎችን አከናውኛለሁ:: በአደጋ ስጋት ላይ ብቻ ሳይሆን፤ በምግብ ዋስትና እና በአገር ልማት ዙሪያ ሰፊ ጥናት እድርጌያለሁ:: ተማሪዎቻችንም ትኩረታቸው በእነዚሁ ጉዳይ ላይ ሲሆን፤ በተለይ እኔ የማማክራቸው ተማሪዎች በአገር ልማት፣ በአደጋ ስጋት በምግብ ዋስትና እና በማህበራዊ ሳይንስ ጉዳዮች ዙሪያ የሚሠሩ ናቸው::
አዲስ ዘመን፡- የትምህርት ክፍሉ መከፈቱ ምን ጥቅም አስገኘ ?
ዶ/ር መሳይ፡- ብዙ ጥቅም ያስገኛል:: እኛ ኢትዮጵያውያን ምስራቅ አፍሪካ ውስጥ በመኖራችን ከአቀማመጣችን አንፃር በርከት ያሉ የአደጋ ስጋቶች የሚያንዣብቡብን ነን:: ስለዚህ በአደጋ ስጋት ዙሪያ በ2ኛ እና በ3ኛ ዲግሪ ደረጃ ማስተማሩ ሀገርን ከአደጋ ሥጋት ለመታደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው:: እንደውም ሊያጋጥም ከሚችለው እና ካለው ችግር አንፃር ከዚህ በፊትም በሰፊው መሠራት ነበረበት የሚል እምነት አለኝ::
ምስራቅ አፍሪካ የተለያዩ ችግሮች ያሉበት ቀጠና ነው:: ከተፈጥሮ ብንጀምር ከመካከለኛው ምስራቅ ተነስቶ እስከ ሞዛምቢክ የተዘረጋው ትልቁ ስምጥ ሸለቆ አንዱ አሳሳቢ ቦታ ነው:: እንደ አዳማ እና አርባምንጭ ያሉ አንዳንድ ትልልቅ ከተሞቻችንም እዚህ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ ይገኛሉ :: ይህ ስምጥ ሸለቆ የመሬት መንቀጥቀጥ ችግር የሚያሰጋበት አካባቢ ነው:: ሁለተኛው ይህ አካባቢ ከሌላው ዓለም በተለየ መልኩ በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጎዳ ነው:: ከዚህም አንፃር ድርቅ ሲከሰት መጠነ ሰፊ ጉዳት ያመጣል:: በሕዝብ ላይ፣ በእንስሳት እና በአጠቃላይ በአካባቢ እንዲሁም በተፈጥሮ ሃብት ላይ ችግር ስለሚያስከትል በአደጋ ስጋት ጉዳይ ላይ የሚመራመሩ ምሁራንን በጥራት ማፍራትአስፈላጊው ነው::
ሌላው እንደሚታወቀው አካባቢው በግጭት የሚታወቅ ነው:: ሶማሊያ፣ ሱዳን እና ሌሎቹም አገሮች የእርስ በእርስ ግጭት ያለባቸው እና አካባቢውም ባለመረጋጋት የሚታወቅ ነው:: በተጨማሪ በድርቁ እና በግጭቱ እንዲሁም በተለያዩ ውጫዊ ምክንያቶች የአካባቢው ኢኮኖሚም ብዙም የተረጋጋ አይደለም:: የሶማሊያም፣ የጅቡቲም፣ የኤርትራም የሌሎቹም ኢኮኖሚ የተረጋጋ አይደለም:: ስለዚህ ይህንን መረዳት፣ ተፅዕኖ መፍጠር፣ መገምገም እና መከታተል የሚችል ባለሞያ ያስፈልጋል:: እነዚህ ጉዳዮች ፕሮግራሙን በጣም አስፈላጊ ያደርጉታል::
አዲስ ዘመን፡- አደጋዎችን ቀድሞ መከላከል ይቻላል?
ዶ/ር መሳይ፡– ቀድሞ መከላከል የሚቻልበትም የማይቻልበትም ሁኔታ አለ:: ለምሳሌ የመሬት መንቀጥቀጥን ቀድሞ በትክክል መተንበይ አስቸጋሪ ነው:: በተቃራኒ ግን የግጭት አደጋንን መተንበይና መከላከል ይቻላል:: ድርቅንም ለመከላከል አሁን እየተደረገ እንዳለው አይነት የአረንጓዴ አሻራ ኢንሼቲቭን በማስፋት መከላከል ይቻላል:: ተፅዕኖውንም መቀነስ ይቻላል:: ለእንደዚህ ዓይነት ቀድሞ መከላከል ለሚቻሉ አደጋዎች ደግሞ የሰለጠነ የሰው ኃይል በጣም አስፈላጊ ነው::
አዲስ ዘመን፡- የአደጋ ስጋት ዙሪያ ከሚደርጉት ጥናት አኳያ ዓለም አደጋን እየተከላከለ ያለው በምን ያህል መጠን ነው? ኢትዮጵያስ በምን ደረጃ ላይ ናት?
ዶ/ር መሳይ፡- መጀመሪያ በዓለም ደረጃ ያለውን እንመልከት:: ዓለምን የአደጋ ስጋትን ከመቀነስ አንፃር በሁለት መንገድ ማየት ይቻላል:: አንደኛው የሳይንስ ግኝቶችን በመጠቀም የተፈጥሮ አደጋዎችን ከሞላ ጎደል መተንበይ እና መቆጣጠር እየቻለ ነው:: ለምሳሌ የጎርፍ አደጋ ወይም የድርቅ አደጋን መተንበይና ጉዳቱን መቀነስ ይቻላል:: በሰው ልጅ ሕይወት ላይ የከፋ አደጋ እንዳያስከትሉ ማድረግ ይቻላል:: በአደጋው ልክ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረግ ይቻላል:: አንዳንድ የተፈጥሮ አደጋዎች ግን አውዳሚነታቸው ቀጥለዋል:: ለምሳሌ በቅርብ ጊዜ በቱርክ እና አካባቢው የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በጣም አውዳሚ ነበር:: ሰሜን አፍሪካ የተከሰተውን የተራራ መንቀጥቀጥና መደርመስ አደጋንም ማንሳት ይቻላል:: እነዚህ አልፎ አልፎ የሚከሰቱት አውዳሚ አደጋዎችን አስቀድሞ መተንበይ ከባድ ነዉ::
አሁን ዓለም መከላከል ያቃተው ሰው ሰራሽ አደጋውን ነው:: ማለትም ሰው ሰራሽ አደጋ ከሌላው ጊዜ በላይ እየከፋ መጥቷል:: ስጋቱም ቀላል አይደለም:: ለምሳሌ በራሺያ እና ዩክሬን መካከል እየተካሔደ ያለው ጦርነት ሰው ሰራሽ አደጋ ነው:: አስቀድሞ መከላከል ይቻል ነበር:: ነገር ግን አስቀድመው አልተከላከሉም:: ይኸው እስከዛሬ ድረስ የሰው ሕይወት እየቀሰፈ እና የዓለም ኢኮኖሚን እያናጋ የእነርሱንም ኢኮኖሚ እየበላ ነው:: በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል እየተደረገ ያለው ግጭትም በተመሳሳይ መልኩ በርካታ ወራትን አስቆጥሯል:: ወደ 35ሺህ ሰው አልቋል:: ይህንንም አስቀድሞ መከላከል ይቻል ነበር:: ነገር ግን መከላከል አልተቻለም:: ሌሎች በርካታ ቦታዎች ላይ አሁንም የቀጠሉ ጦርነቶች/ግጥቶች አሉ::
ጎረቤታችን ሱዳን ውስጥ የእርስ በእርስ ግጭት የከፋ ደረጃ ላይ ይገኛል፡:፡ ሶማሊያ ሀገር ውስጥም ችግር አለ:: ታይዋን አካባቢ ያለው ሁኔታ አስጊ ነው:: በዚህ አካባቢ ምናልባት የአሜሪካ እና የቻይና ጉዳይ በጣም ያሳስባል:: ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ መካከል ያለውም ሁኔታ ተጨማሪ ሥጋት ነው፣ መርገብ አልቻለም:: ኒኩሌር የታጠቁ እነ ራሺያ እና ሰሜን ኮሪያ ከተፈጥሮ አደጋ በላይ ስጋት ሆነዋል:: ዓለም ወይም ፖለቲከኞቻችን እነዚህን ሰው ሰራሽ አደጋዎችን በተገቢው ሁኔታ እየተከላከሉ ወይንም በድርድር እየፈቱ አይደለም::
ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ድርቅ ካደረሰው ጉዳት በላይ አስቀድመን ልንከላከላቸው የምንችላቸው ሰው ሰራሽ ችግሮቻችን የከፋ ችግር ውስጥ ጥለውን አልፈዋል:: ለምሳሌ ቀርበን መነጋገር ባለመቻላችን የአንድ ሀገር ልጆች ተከፋፍለን እየተገዳደልን ኖረናል:: መከላከል አይቻልም ወይ? ከተባለ መከላከል ይቻል ነበር:: አንዱ ወገን ለዘብ ብሎ ቀርቦ ቢነጋገር መፍታት እና መከላከል ይቻል ነበር:: በሰው ሰራሽ ግጭቶች ምክንያት ኢኮኖሚያችን ምን ያህል እየተጎዳ እንደኖረ ይታወቃል:: እንዲህ ዓይነቶቹ በአጠቃላይ በዓለም ያለው በደንብ ሲታዩ ከተፈጥሮ ይልቅ ሰው ሰራሽ አደጋዎች እየጎዱን ነው::
ልማትን በዘላቂነት ለማምጣት አደጋን መከላከል የግድ ነው:: አደጋን ሳንከላከል እና ሳንቆጣጠር ወደ ልማት ብቻ ካተኮርን ልማቱ ይወድማል፤ የሰው ልጅ አውዳሚ እንስሳ ነው:: በብዙ ዓመት የለማ ሃብት፤ በሰው ልጅ በጥቂት ቀናት ይጠፋል:: ስለዚህ አደጋ መከላከል ከልማት ጋር የተገናኘ ነው:: አደጋን መከላከል ብቻውን አይበቃም:: ልማትም ብቻውን አይበቃም:: አደጋን እየተከላከልን ማልማት፤ እያለማን አደጋን መከላከል የግድ ነው:: አደጋ መከላከል ሲባል ደግሞ ሰው ሰራሹን ወይም የተፈጥሮውን ብቻ ሳይሆን ሁለቱም ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን፡- በተፈጥሮ ሃብት እና አጠቃቀም ዙሪያ ጥናቶችን አጥንተዋል:: ጥናቶት ላይ በመመርኮዝ ስለኢትዮጵያ ተፈጥሮ ሃብት እና አጠቃቀም ዙሪያ ምን ይላሉ?
ዶ/ር መሳይ፡- ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ከሃምሳ እና ከስድሳ በመቶ በላይ በደን የተሸፈነች መሆኗን ጥናቶች ያመለክታሉ:: ነገር ግን በተለይ ከ1950ዎቹ እና ከ1960ዎቹ ጀምሮ ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት አልተሰጠም:: ትኩረታችን ሌላ ነበር:: በደርግ ጊዜ ጦርነት ነበር:: ከዛ በኋላም ቢሆን ትኩረት ስላልተሰጠው ደኑ ተመናምኖ ራቁታቸውን ከሆኑ አገራት ተርታ ለመሰለፍ ጥቂት ቀርቶን ነበር::
ኢትዮጵያ በውሃ ሃብት የተሻለች ነበረች:: ሃይቆች አሉን፤ አንዳንዶቹ መጠናቸው በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል:: ለምሳሌ አቢጃታ ሃይቅ በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል:: ሐረማያ ሃይቅ ጠፍቶ ነበር፤ አሁን ትንሽ እያገገመ ነው:: ሌሎች ደግሞ ብዙም የማይታወቁ ትንንሽ ሃይቆች፣ ወንዞች፣ ምንጮች ደርቀዋል:: ከገጠር ወጥቼ ተመርቄ አንድ ወቅት ወደ ተወለድኩበት አካባቢ ከአምስት ዓመት በኋላ ስሔድ ለመፋቂያ እንኳ የሚሆን እንጨት አልነበረም:: አሁን በቅርቡ ከአረንጓዴ ልማት ጋር ተያይዞ የሚሠራው ኢንሼቲቭ ጥሩ ውጤት እያስገኘ ነው:: አሁን ደኑ እየተመለሰ፣ የውሃ ሃብቶችም እያገገሙ ነው::
የጂኦግራፊክ ኢንፎርሜሽን ሲስተም (GIS/RS) ቴክኖሎጂን በመጠቀም በምናደርጋቸው ጥናቶች የመሬት አጠቃቀም እና የመሬት ሽፋን በምን ያህል መጠን እየጨመረ እንደሚገኝ ማወቅ ይቻላል:: የአረንጓዴ አሻራ ኢንሸቲቭ በእውነት ለመናገር ያመጣው ለውጥ በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም:: ሰዎች ዛፍ እንዲተክሉ እና እንዲንከባከቡ እያነሳሳ ይገኛል:: ዛፍ ለቤት መስሪያ ብቻ ሳይሆን አየር ሙቀትን እንደሚቆጣጠር፣ የውሃ አካላትን እንደሚያጎለብት ሁሉም እየተረዳ መጥቷል:: ስለዚህ የችግኝ የተከላ እንቅስቃሴው ሰፍቷል:: ይህ እንቅስቃሴ እስከ ግለሰብ ድረስ ወርዶ ከተሰራበት ከ100 ዓመት በፊት ወደ ነበርንበት ቦታ መመለስ ይቻላል:: በደን ሽፋን እና ሌሎች የተፈጥሮ ሃብት ፣ በአፈር እና ውሃ ሃብት ወደ ነበርንበት መመለስ እንችላለን::
አዲስ ዘመን፡- እርሶ የገበሬ ልጅ ነዎት:: መነሻዎ ገጠር ነው:: ጂኦግራፊ ተምረዋል:: እርሶ ብቻ ሳይሆኑ ብዙዎች ተምረዋል:: ነገር ግን በሌላ በኩል ምሁራን ለገጠሩ ሕዝብ በተለይ ለአርሶ አደሩ ምን አደረጉ ይላሉ? ምን ማድረግስ ነበረባቸው?
ዶ/ር መሣይ፡– እኔን ጨምሮ ሌሎች የተማሩ ሰዎች ታች ወርደን ከገበሬው ከገበሬዉ በመሥራት ላይ ችግር ያለ ይመስለኛል:: ለገበሬው ችግሮቹን በተገቢዉ ሁኔታ አላቃለልንለትም:: ገበሬው ዛሬም ድረስ ከሺህ ዓመታት በፊት በተፈጠረ በሞፈር እና ቀንበር እያረሰ ነው:: ምርታማነቱ ዛሬም ዝቅተኛ ነው:: አሁንም በተለያዩ እጥረቶች እና ፈተናዎች ውስጥ ይገኛል:: የግብዓት አቅርቦት እጥረቱ ቀላል አይደለም:: ከዓመት ዓመት ከጎተራው የሚበላ የገበሬ ቤተሰብ ጥቂት ነው:: በአካባቢ ጥበቃ፣ በግብርና እና ሌሎችም ከገበሬው ጋር ቀጥታ በሚገናኝ ዘርፎች ላይ ሶስተኛ ዲግሪ ይዘን ዶክተር የተሰኘን ብዙ ነን:: ነገር ግን እንደ ብዛታችን ገበሬውን አልጠቀምነውም:: ለወደፊቱ ብዙ መሥራት ያለብን ይመስለኛል::
ሆኖም ምንም አላደረግንም ማለት አይደለም:: ቢያንስ ገጠር ያለው ሰው የተሻለ ንፁህ ውሃ ማግኘት እንዲችል በተወሰነ ደረጃ ረድተነዋል:: በአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ላይም ጥሩ ግንዛቤ ተፈጥሯል:: ማዳበሪያ ኬሚካል ቢሆንም ይቀርባል፤ ፀረ-ዓረም ፀረ-ተባይ ይቀርብለታል:: ምን ያህል ጠቀመ የሚለው እንዳለ ሆኖ ማለት ነው:: የምሁራን እና የመንግስት ድጋፍ ባይኖር ኖሮ፤ ገበሬው ከዚህም በከፋ ችግር ውስጥ ሊኖር እንደሚችል አያጠራጥርም:: ማድረግ የምንችለውን ያህል አድርገናል ወይ የሚለው ግን ያጠያይቃል::
አዲስ ዘመን፡- ለእዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው?
ዶ/ር መሣይ፡- ሌሎች ምክንያቶች እንዳሉ ሆኖ የት/ት ሥርኣት ላይ የተሻለ ሥራ መሠራት ያለበት ይመስለኛል:: የትምህርት ሥርኣታችን የአገራችንን ችግር ለይቶ የሚሳይ እና ችግር እንድንፈታ የሚያስችለን መሆን አለበት:: ተመልሰን ሕዝባችንን እንድናገለግል፣ እንድናከብር እና እንድናግዝ መሆን አለበት:: ካሪኩለሙን ከእኛ አገር ችግር ፈቺነት አንፃር ማስተካከል ያስፈልጋል:: የኛን ባህል፣ ታሪክ እና ችግርን ማዕከል ያደረገ መሆን አለበት:: ይህ ማለት ጭራሽ የትኛውንም ሀገር ተሞክሮ አንውሰድ ማለት አይደለም::
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ሌላውንም ዓለም አይተዋል:: ምን ማድረግ አለብን ይላሉ?
ዶ/ር መሣይ፡- በጣም የምቀናው እና ወደ እኛ አገር መምጣት አለበት የምለው የተሻለ የሥራ ባህል ነው:: ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች ናት:: ነገር ግን የሥራ ባህል ላይ ትልቅ ክፍተት ያለ ይመስለኛል:: ያንን ማስተካከል ያስፈልጋል:: በጣም ታታሪ መሆን አለብን:: ሕጋዊ እና ሥነ-ምግባራዊ ባልሆነ አ ቋራጭ መንገድ ሃብት ለማጋበስ መሞከርን መተው መቻል አለብንም:: በሥራ የሚያምን (meritorious) ሕዝብ ለመፍጠር መጣር ያስፈልጋል:: የሥራ ባህላችን እና የትምህርት ሥርዓታችን ላይ በጥሩ ሁኔታ ከሠራን ሌላው ከባድ አይደለም::
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ሥም እጅግ አመሰግናለሁ::
ዶ/ር መሣይ፡- እኔም አመሰግናለሁ::
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም