የገበያ ድርሻው እያደገ የመጣው የሀገር ውስጥ የሕክምና ግብዓት ምርት

መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁን ወቅት አምራች ኢንደስትሪዎችን በማበረታታት ተኪ ምርቶች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ ትርጉም ያለው ሥራ እየሰራ ነው። በመሆኑም በአምራች ኢንደስትሪው ዘርፍ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች እየታየ ነው። ‹‹የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ›› እንዲሉ አልባሳትን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን የሚያመርቱ በርካታ አምራች እጆች እዚህም እዚያም ተፈጥረዋል። በአሁኑ ወቅትም ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በአገር ውስጥ ምርት የመተካታቸው ዕድል እየሰፋ መጥቷል። ለዚህም መንግሥት ለአምራች ኢንደስትሪው የሰጠው ትኩረት ድጋፍና ክትትል ላቅ ያለና የሚበረታታ መሆኑ እየተጠቆመ ይገኛል።

መንግሥት ትኩረት ከሰጣቸው አምራች ኢንደስትሪዎች መካከልም የሕክምና ግብዓት አምራች ኢንደስትሪዎች። በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት “ጤናችን በምርታችን” በሚል መሪ ሃሳብ የሀገር ውስጥ የሕክምና ግብዓት ምርት ኢኖቬሽን ኤግዚቢሽን ተካሂዷል። በኤግዚቢሽኑ ላይም በሕክምና ግብዓት ምርት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ በርካታ አነስተኛና መካከለኛ አምራቾች ተገኝተዋል።

አምራቾቹ እንደሚሉት፤ ኤግዚቢሽኑ በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾች በአንድ ቦታ መሰባሰባቸው ምርቶቻቸውን የማሳየትና እርስ በእርስ የመተዋወቅ ዕድል ፈጥሮላቸዋል። ይህም መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ያመላከተ ከመሆኑም በላይ ምርታማነት እንዲጨምር፣ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርና የውጭ ምንዛሪ ግኝት እንዲያድግ በማድረግ ትልቅ አበርክቶ እንደነበረውም ተናግረዋል።

መንግሥት ለአነስተኛና መካከለኛ አምራቾች የሰጠው ትኩረት የዘርፉን ተዋንያን የሚያበረታታ እንደሆነ የገለጸችው ወይዘሪት ፌርዶስ ስሩር፤ የዳና ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለድርሻና የማኔጅመንት ባለሙያ ናት። እሷ እንዳለችው ድርጅቱ ለሕክምና አገልግሎት የሚውል ጥጥ ያመርታል። ጥሬውን ጥጥ በመዳመጥ ለሕክምና አገልግሎቶች ምቹ በማድረግ ነው የሚያመርተው። ለአጠቃቀም ምቹ ተደርጎ የሚዘጋጀው ጥጥ ከሕክምና አገልግሎት ውጭ ለኮስሞቲክስ ማለትም ለፊት መጠራረጊያም የሚያገለግልና በውበት ሳሎኖችም የሚፈለግ ነው።

ድርጅቱ ወደ ሥራ ከገባ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠር ሲሆን፤ የሚያመርተው ጥጥም ለቁስል መጠራረጊያና ማሸጊያ የሚያገለግልና መቶ በመቶ የአገር ውስጥ ጥጥን የሚጠቀም ነው። በመቶ እና በአምስት መቶ ግራም የሚዘጋጅ ሲሆን፤ ምርቶቹ በዋናነት ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉ በመሆናቸው አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ከተሞች ጭምር ይፈለጋሉ።

ምርቶቹ ገበያ ውስጥ የሚገቡት በጅምላ አከፋፋዮች አማካኝነት እንደሆነ ጠቅሳ፤ ምርቱ ለውጭ ገበያ ጭምር እንደሚፈለግ ነው ያስረዳችው። ዳና ትሬዲንግ የገበያ ችግር እንደሌለበት ጠቅሳ፣ ኤግዚቢሽኑ ከሌሎች አምራች ድርጅቶች ጋር የመተዋወቅና ልምድ የመለዋወጥ ዕድል እንደፈጠረለት ተናግራለች።

አብዛኛው ሰው ጥጥን ጨምሮ ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ ግብዓቶች በአገር ውስጥ እንደሚመረቱ አያውቅም ስትል ጠቅሳ፣ ለአብነትም ለቁስል መጠራረጊያና ማሸጊያ የሚያገለግለው ጥጥ አገር ውስጥ እንደሚመረት የማያውቁና ከውጭ የሚያስገቡ እንዳሉም ጠቅሳለች። ስለዚህ መድረኩ ምርቶቹን ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር እንዲተዋወቁና የገበያ ትስስር እንዲፈጠር ማስቻሉን አስታውቃ፣ ኤግዚቢሽኑ መዘጋጀቱ በተለይም በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ ሆነው የሚያመርቱ አምራች ኢንዱስትሪዎችን እንደሚያበረታታ ገልጻለች። በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ጥራት ያለው ጥጥ እንደሚመረት ወጣት ፌርዶስ አመልክታ፣ በአገር ውስጥ ያለውን እምቅ ሃብት በመጠቀም በርካታ አምራቾች ሊፈጠሩና የተለያዩ ተኪ ምርቶች በአገር ውስጥ ሊመረት እንደሚገባም ጠቁማለች።

ሌላኛው አምራች ድርጅት የሕክምና አልባሳትን በአገር ውስጥ የሚያመርተው አዲላስ ሜዲካል ዩኒፎርም ነው። የድርጅቱ ሼርና ማርኬቲንግ ማናጀር ወይዘሪት አለውያ ሀሰን ድርጅቱ የሕክምና አልባሳትን የሚያመርት/ ጋርመንት/ መሆኑን ገልጻ፣ ድርጅቱ ከዚህ ቀደም የተማሪዎች ዩኒፎርምን ጨምሮ ልዩ ልዩ አልባሳትን በማምረት ይታወቅ እንደነበርም አስታውሳ፣ ከአራት ዓመት ወዲህ ግን የሕክምና አልባሳት ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል ብላለች።

እሷ እንዳብራራቸው፤ ድርጅቱ ሐኪሞች በቀዶ ሕክምና ጊዜ የሚለብሱትን ሙሉ አልባሳት እያመረተ ሲሆን፤ በሕክምናው ውስጥ ለሚገኙ የቀዶ ሕክምና ክፍሎች አስፈላጊዎቹን አልባሳት በሙሉ አዘጋጅቶ ያቀርባል። ድርጅቱ አንድ የጤና ተቋም የሚስፈልጉትን አልበሳት ማለትም ከጥበቃ ጀምሮ እስከ ቀዶ ሕክምናው ሐኪም ድረስ አስፈላጊ የተባሉ አልባሳትን በሙሉ በጥራት እያመረተ ይገኛል። በተለይም የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ለሚሰጡ ዶክተሮች ሙሉ ልብስ ላይ ትኩረት ያደርጋል።

የሕክምና አልባሳቱ ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ ግብዓቶች እንደሚመረቱ የጠቀሰችው አለውያ፤ ብትን ጨርቆቹን ጨምሮ የተለያየ ግብአቶቹ ከአገር ውስጥ አምራቾች እንደሚገኙ ነው የገለጸችው። ገበያውን በተመለከተም የድርጅቱን ምርቶች በግልና በመንግሥት ሆስፒታሎች እንዲሁም በተለያዩ ተቋማት ተፈላጊ መሆናቸውን አስታውቃለች።

በተለይ በኤግዚቢሽንና ባዛሮች ላይ በመሳተፍ የገበያ ትስስር በመፍጠር በርካታ ደንበኞችን ማፍራት መቻሉን ጠቅሳ፣ በጨረታዎች ላይ እንደሚሳተፍም ነው የጠቆመችው። በአሁኑ ወቅት አልባሳቱን ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ በሚገኙ የክልል ከተሞች ጭምር ተደራሽ እያረገ መሆኑን ተናግራ፣ ለአብነትም ሐረር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረብርሃንና ወላይታ ላይ መድረስ መቻሉን አመልክታለች። በግለሰብ ደረጃ ለሚፈልጉ ቡልጋርያ አካባቢ በሚገኘው የመሸጫ ሱቃቸው ምርቶቹን ለገበያ ማቅረቡን ጠቁማለች።

አቶ ኃይሉ ከበደ በኢትዮጵያ መድሐኒት ፋብሪካ የምርምርና ስርጸት ምክትል ኃላፊ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ መድሃኒት ፋብሪካ አሁን ላይ በርካታ የመዳህኒት አይነቶችን በስፋት እያመረተ ይገኛል። መዳሀኒቶቹ በአብዛኛው ማኅበረሰብ ዘንድም እየደረሱ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በብዙዎች ዘንድ እንደሚመረጡም ነው ያመለከቱት። ከውጭ የሚገቡት መድሃኒቶች ዋጋቸው ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ተናግረው፣ የሀገር ውስጥ ምርቱ ጥራትና ፈዋሽነቱም ተመራጭ እያደረገው እንደሚኝ አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ መድሃኒት ፋብሪካ የመድሃኒት ምርቶቹን የማኅበረሰቡን አቅም ባገናዘበ መንገድ ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። ለዚህም የመዳሀኒቱን ቀመር /ፎርሙላ/ ወይም ውህድ ብቻ ከውጭ በማስመጣት በራሱ የምርምር ማዕከል መድሃኒቶችን በአገር ውስጥ ያቀናብራል። በምርምር ማዕከሉም የመድሃኒቶቹን የቆይታ ጊዜ፣ የጎንዮሽ ጉዳትና የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ ጥራት ያላቸውና ፈዋሽነታቸው የተረጋገጠ መድሃኒቶችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ እያደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ መድሃኒት ፋብሪካ አንጋፋ እንደመሆኑ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ሌሎችም ለሚያደርጉት የምርምር ሥራ ሙያዊ ድጋፍ የሚሰጥ አንጋፋ ተቋምም ነው ያሉት አቶ ኃይሉ፤ በዘርፉ ለተሰማሩ ሌሎች ፋብሪካዎችም ድጋፎችን እንደሚያደርግም አስታውቀዋል። የመድሃኒት ምርቶቹንም በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራም አመልክተዋል። ኤግዚቢሽኑም የኢትዮጵያ መድሃኒት ፋብሪካ እየሰራቸው ያሉ ሥራዎችን ለማስተዋወቅና በዘርፉ ከተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር የገበያ ትስስር ለመፍጠርና ልምድ ለመለዋወጥ ትልቅ እገዛ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

መድረኩ በተለይም የምርምር ማዕከላት፣ የቁጥጥር አካላትና አምራቾች በጋራ በመሆን የባህል ሐኪሞችንና በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ አምራቾችን ለመደገፍ የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠርም እንደሚረዳ የጠቀሱት አቶ ኃይሉ፤ እነዚህ አካላት በጋራ ሕክምናውን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ መድሃኒት ፋብሪካ የሚያመርታቸው የመድሃኒት አይነቶች ከ120 በላይ ናቸው። አብዛኞቹም በማህበረሰቡ ዘንድ ይታወቃሉ። አሁን ላይ አዳዲስ መድሃኒቶችን ወደ ገበያው እያስገባ ሲሆን፤ ለአብነትም ከዚህ ቀደም ብቻውን ሲሸጥ የነበረው ኦ አር ኤስ የተባለ መድሃኒት አሁን ላይ ዚንክ በመጨመር እያመረተ ይገኛል። የስኳር መድሃኒትንም እንዲሁ እያመረተ ነው፤ ፋብሪካው የመድሃኒት ማሸጊያዎቹን ጭምር በአዲስ መልክ በማዘጋጀት እያቀረበ ይገኛል።

ከሰኔ 15 እስከ 20 ቀን 2016 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ቆይታውን ያደረገው በዚህ የሀገር ውስጥ የህክምና ግብዓት ምርትና ኢኖቬሽን አውደ ርዕይ በተጠናቀቀበት ወቅት የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ አውደ ርዕዩ የህክምና ግብዓት ምርት ላይ የተሰማሩ አምራቾችን ከማጠናከር ባለፈ በዘርፉ ያሉትን የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎች በሚገባ ማስተዋወቅ ማስቻሉን ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ አውደ ርዕዩ መንግስት የህክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት ነው። ለዘርፉ ውጤታማነት አመቺ ፖሊሲ አውጥቶ እየሠራ ባለበት በዚህ ወቅት ለዘርፉ ኢንቨስትመንት ማደግ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ ድጋፎች ማቅረቡንም አጠናክሮ ይቀጥላል።

አውደ ርዕዩ የህክምና ግብዓት ምርቶችን በማምረት ላይ የተሰማሩ አምራቾችን ከማጠናከርና የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን ከማስተዋወቅ ባለፈ የሀገር ውስጥ ምርት ላይ በስፋት በመስራት ከውጭ ጥገኝነት ለመላቀቅ የተያዘውን ጥረትም ያግዛል። ለዜጎች የጤና ስርዓት መሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦም ይኖረዋል። የጤናውን ዘርፍ ማጠናከር ለሀገርና ለትውልድ ደህንነት የማሰብ ጉዳይ ነው።

የሀገር ውስጥ የህክምና ስርዓትን ማሻሻል መንግስት ጤናማና አምራች ዜጋ በመፍጠር የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ካለው ግብ ጋር የሚተሳሰር ስለመሆኑም የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ እስከ ባለፈው ዓመት ከ92 በመቶ በላይ የህክምና ግብዓቶችን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ ስታስገባ መቆየቷን አመልክተዋል። ይህን ሁኔታ ለመለወጥ መንግስት የሀገር ውስጥ የህክምና ግብዓት ምርት ድርሻን የሚያሳድጉ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ውጤት ማምጣት እንደተቻለ ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህም የሀገር ውስጥ የህክምና ግብዓት ምርቶች የገበያ ድርሻ ከስምንት በመቶ ወደ 36 በመቶ አድጓል ሲሉ ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ለ35 ሀገራት መድሃኒት እያመረተች ትልካለች ብለዋል።

በዘርፉ በየደረጃው የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት በጤናው መስክ ራስን መቻል ምርጫ የሌለው ግዴታ እንደሆነም አመላክተው፣ ለሀገር በቀል እውቀት ባለቤትና መድሃኒቶች ትኩረት መስጠት፣ ከትምህርትና ከምርምር ተቋማት ጋር ማስተሳሰር እንዲሁም የህክምና ግብዓት ምርቶችን ጥራት ማሳደግና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲኖራቸው በትጋት መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል። ለዚህም ውጫዊና ውስጣዊ ፈተናዎችን በመቋቋም ሀገራዊ የጤና ግቦችን ማሳካት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በህክምና ግብዓት ራሷን የምትችልበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ ምርት የመኩራትና የማበረታታት ባህልን እንዲያዳብሩም ጥሪ አቅርበዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው አውደ ርዕዩ የህክምና ኢንዱስትሪ፣ እውቀትና ገበያ ትስስር የተፈጠረበት መሆኑን ገልጸዋል፤ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነው ይህ የሀገር ውስጥ የመድሃኒት እና የህክምና መገልገያ ምርት አውደ ርዕይ የጤና ደህንነት ማረጋገጫችን ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ክብራችንን ማስጠበቂያም ጭምር ነው ብለዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ አውደ ርዕዩ 107 የሚደርሱ የሀገር ውስጥ የህክምና ግብዓት አምራቾች ተሳትፈውበታል፤ ከ100 ሺህ በላይ በሚደርሱ ሰዎችም ተጎብኝቷል። ጎን ለጎንም የሀገር ውስጥ አምራቾችን አቅም ከፍ ማድረግ የሚያስችሉና መግባባት የተፈጠረባቸው መድረኮችም ተካሂደዋል። አውደ ርዕዩ የንግድ ግንኙነቶችን የፈጠረ፣ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን አጉልቶ ያሳየ እንዲሁም የዘርፉ ተዋንያንን ያቀራረበ ነው።

በኤግዚቢሽኑ ላይ እንደተገለጸው፤ ኢትዮጵያ በአሁን ወቅት 36 በመቶውን የመድኃኒትና የሕክምና ግብዓት ፍላጎቷን በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን ችላለች። በመሆኑም እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ዓመት የኢትዮጵያን የሕክምና ግብዓት ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለተኪ ምርት ልማት በተሰጠ ትኩረት ከ50 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ወጪን ማዳን ተችሏል። ኤግዚቢሽኑ በቆየባቸው ስድስት ተከታታይ ቀናት በኢትዮጵያ የሕክምና ኢንቨስትመንት ያሉ ዕድሎችን እንዲሁም የሀገር ውስጥ የሕክምና ምርትና አገልግሎቶችን ማመላከት ተችሏል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You