
ሐዋሳ፦ በሲዳማ ክልል ለ2016 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ከ285 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለተከላ መድረሱን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ የመስክ ምልከታ ላደረጉ የጋዜጠኞች ቡድን የቢሮው ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ እንደተናገሩት፤ በ2016 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በክልሉ 300 ሚሊዮን ችግኝ አዘጋጅቶ ለመትከል ታቅዶ፤ ከዚህ ውስጥ ከ285 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለተከላ ደርሷል።
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት የግድ ይላል ያሉት ኃላፊው፤ ይህ እውን የሚሆነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ወይም የደን ልማት ሥራው ተጠናክሮ ሲቀጥል እንደሆነ ይናገራሉ።
እንደክልል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በ2011 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብሩ ከተበሰረ ጊዜ ጀምሮ ልማቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን አመላክተው፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በክልሉ 850 ሚሊዮን ችግኝ ተተክሏል። የፅድቀት መጠኑም በዓመት በአማካኝ ከ85 በመቶ በላይ ነው ብለዋል።
ክልሉ በዓመት ችግኝ የማዘጋጀት አቅሙ ከ57 ወደ 300 ሚሊዮን መድረሱን የቢሮ ኃላፊው አቶ መምሩ ጠቁመው፤ ክልሉ ከ350 እና 400 ሚሊዮን ችግኝ የማዘጋጀት አቅም ቢኖረውም፤ በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 300 ሚሊዮን ችግኝ አዘጋጅቶ ለመትከል ነው የታቀደው ብለዋል። ምክንያቱም በተለይ በሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ጥራትን መሠረት ያደረገ ልማት ለማካሄድና የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ የፍራፍሬ ችግኞችን አዘጋጅቶ በስፋት ለመትከል በመታቀዱ፤ ለተከላ የሚዘጋጁ ችግኞችን ቁጥር በ300 ሚሊዮን መገደቡን ያስረዳሉ።
አቶ መምሩ በዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አዘጋጅቶ ለመትከል ከታቀደው 300 ሚሊዮን ችግኝ ውስጥ ከ285 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለተከላ መድረሱን ጠቅሰው፤ ለተከላ ከደረሰው ውስጥ ወደ 22 ሚሊዮን የሚጠጋ ችግኝ ቀድሞ መተከሉን ተናግረዋል።
ለ2016 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ከወዲሁ በትኩረት ተከናውኗል ያሉት ኃላፊው፤ ለችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ “በኤክስ ዋይ ከርድኔት” በተለየ 11 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ የፍራፍሬ ችግኞችን በብዛት በማፍላት፣ ዘራቸውን በማሻሻልና በስፋት በመትከል አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የሚናገሩት አቶ መምሩ፤ በ2015 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አምስት ሚሊዮን የአቮካዶ ችግኝ መተከሉንና በተመሳሳይ ለዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ የልማት ሥራ ከሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን በላይ የፍራፍሬ (አቮካዶ) ችግኝ ለተከላ መዘጋጀቱን አክለው ገልጸዋል። በክልሉ በ2016 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር 300 ሚሊዮን ችግኝ ይተከላል ተብሎ ይጠበቃል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2016 ዓ.ም