የቀድሞ የአፍሪካ እግር ኳስ ከዋክብት በሸነን አፍሪካ ፌስቲቫል

በዓለም ላይ እያደጉ ካሉ ሃገራትም በእጅጉ ተጠቃሚ እየሆኑ ካሉባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የስፖርት ቱሪዝም ነው። በጅማሬ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት አበረታች ስራዎችን በማከናወን ላይ ትገኛለች። ከዚሁ ጋር ከሚጠቀሱ ክንውኖች መካከልም ከሰሞኑ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ያሳተፈው ″ሸነን አፍሪካ ፌስቲቫል አንዱ ነው። ለሶስት ቀናት የተካሄደው ይኸው አህጉር አቀፉ የፋሽን፣ የቱሪዝም እና ስፖርት ፌስቲቫልም የስፖርት ቱሪዝምን ከማነቃቃት አኳያ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡

በፌስቲቫሉ ከተከናወኑ መርሃ ግብሮች መካከል አንዱ ስፖርታዊ ክንውን ሲሆን፤ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተሳተፉበት የወዳጅነት ጨዋታ ከቀድሞ የእግር ኳስ ከዋክብቱ ጋር በወዳጅነት ፓርክ ቁጥር ሁለት ተደርጓል። አንጋፋዎቹ የናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች ኑዋንኮ ካኑ፣ ዳንኤል አሞካቺ፣ ታሪቦ ዌስት እንዲሁም በአውሮፓ ሊጎች የተጫወተው ሴኔጋላዊው ሄንሪ ካማራ ደግሞ በፌስቲቫሉ ላይ የተገኙ ስፖርተኞች ናቸው።

የእግር ኳስ ጨዋታውን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ጥያቄ ማቅረቧን አመላክተዋል። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ዋንጫ መስራች ሃገራት መካከል አንዷ ናት። ይሁንና በመድረኩ ያላት የተሳትፎም ሆነ የአዘጋጅነት ታሪክ በሂደት እየደበዘዘ በመምጣቱ የእግር ኳስ ቤተሰቡ በትዝታ እንዲገደብ ሆኗል።

የአህጉሪቱን ትልቁን የእግር ኳስ ውድድር በማስተናገድ የስፖርት ቤተሰቡን ምኞት ዕውን ለማድረግ መንግስት ጥያቄ አቅርቦ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

የአፍሪካ ዋንጫን ማስተናገድ ውስብስብ ሂደቶችን እንደሚጠይቅ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከወቅቱ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ጋርም በጉዳዩ ላይ ውይይት መደረጉን ጠቁመዋል። የአፍሪካ ዋንጫ በኢትዮጵያ መካሄዱ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ከማነቃቃት ባሻገር ለገጽታ ግንባታ እና ቱሪዝም ዘርፍ መነቃቃት ትልቅ ፋይዳ አለው። ከዚህ አኳያ የአፍሪካ ታላላቅ የቀድሞ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ይህንን የኢትዮጵያ ውጥን ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል ይፈጥራል። ″ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የኢትዮጵያን ገጽታ በማሳየት የነበረውን ጉልህ ሚና በመጥቀስም በቀጣይ የፈረስ ጉግስን ጨምሮ በተለያዩ ስፖርት ዘርፎች የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

የቀድሞዎቹ የአፍሪካ እግር ኳስ ከዋክብቱ ከእግር ኳስ ጨዋታው ባለፈ በችግኝ ተከላ አረንጓዴ አሻራቸውን ያሳረፉ ሲሆን፤ የተለያዩ የልማት ስራዎችንም ጎብኝተዋል። ይህንን ተከትሎም አርሰናልን ጨምሮ በአያክስ፣ ኢንተርሚላን፣ ዌስትብሮሚች እና ፖርትስማውዝ ክለቦች የተጫወተው ኑዋንኮ ካኑ፤ ኢትዮጵያ እጅግ ውብና የሚያስደንቅ ባህል ያላት ሀገር መሆኗን ገልፀዋል። በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ የነበረው አቀባበልና እንክብካቤ ቤታቸው ያሉ ያህል እንዲሰማቸው በማድረጉ በቀጣይም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ እንደሚመጣ፤ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ ያላቸውን ራዕይ መሰረት አድርገው እያከናወኗቸው ያሉ የልማት ስራዎችን ስለመጎብኘታቸውም ተናግሯል፡፡

ሌላኛው ናይጄሪያዊና የቀድሞ የኢንተር ሚላን እና ኤሲ ሚላን ተጫዋች ታሪቦ ዌስት በበኩሉ፤ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሀገር ባለፈ ለአፍሪካ ያላቸውን ራዕይ እንደሚያሳዩ መገንዘቡን አመላክቷል። የጠቅላይ ሚኒስትሩን የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ በማድረግ የሀገሪቱን እግር ኳስ የማነቃቃት እቅድ እውን እንደሚሆን ያለውን መልካም ምኞት ገልጿል። የቀድሞ የአህጉሪቱ ታላላቅ ተጫዋቾች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ከኢትዮጵያውያን ጋር ትስስር በመፍጠር የእግር ኳስ ባህል እንዲሻሻል ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። የናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድን አባል የነበረው ሌላኛው ተጫዋች ዳንኤል አሞካቺ በቆይታቸው ኢትዮጵያውያን በክብርና በፍቅር አቀባበል እንዳደረጉላቸው ተናግሯል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You