መቼም የሰው ልጅ ፍላጎቱን እንጂ የሕይወት መንገድ የት እንደሚያደርሰው አይታወቅም። ሕይወት ራሷ መርታ ያልታሰበና ያልታለመ ቦታ ላይ ስታኖረን አሜን ብሎ ከመቀበል በቀር ምን ይባላል። የሕይወት መስመር ከራስ ፍላጎት ወጥቶ በእድል መመራቱን ማሳያ የሆነችን ሴት ታሪክ ለዛሬ የሴቶች አምድ ይዘንላችሁ ቀርበናል። የዛሬ ባለታሪካችን እንደ አብዛኞቹ የአርሲ አካባቢ ልጆች የሩጫ ፍላጎትም ክህሎትም የነበራት ነበርች። በትምህርት ቤት ውድድር አያያዟን የተመለከቱ መምህራን ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ከሚያስጠሩት አትሌቶቻችን አንዷ ልትሆን አንደምትችል ይናገሩ ነበር። ነገር ግን የሕይወት መስመር ተቀይሮ ባላሰበችው መንገድ ውስጥ እንደቆመች የምትናገረውን ሴት ታሪክ በዚህ መልኩ አቅርበነዋል።
ኮማንደር በሻዱ ደበሌ ከእናቷ ወይዘሮ ሙሉ መልካ ከአባቷ አቶ ደበሌ አሸኖ በ1961 ዓ.ም ነበር የተወለደችው። ኮማንደሯም የተወለደቸው አርሲ ዞን ሊሙና ቡሉቡሌ ወረዳ ኡሉሌ ሀሳ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ነው። በሻዱ ከተወለድችባት ቀዬ ትምህርት ቤት ለመድረስ ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ የሚወስደውን መንገድ እየሮጠች ትደርስ ነበር። በዘጠኝ ዓመቷ የአስኳላን ደጅ የረገጠችው ይቺ ልጅ ትምህርት በጣም የምትወድ ስለነበረች ወላጆቿ ከትምህርት ቤት እንዳያስቀሯት በማለት በጥዋት ተነስታ ውሃ ቀድታ ቤት ውስጥ የሚጠበቅባትን ስራ ሰርታ በሩጫ ወደ ትምህርት ቤት ትሄድ እንደነበር ታስታውሳለች።
ከትምህርት ቤትም በሩጫ ተመልሳ እናቷን የምትረዳ በመሆኗ አያያዟን ያዩ መምህራኖቿ በትምህርት ቤት ደረጃ እየተወዳደረች ውጤት እንድታስመዘግብ ያበረታቷት ነበር። ከትምህርት ቤት የተጀመረው ውድድር ወደ ወረዳ ከፍ ሲል፤ ከዛም ወደ አውራጃ ሲያድግ አርሲ ክፍለ ሀገር በሚባል በመወዳደር ከዛ ወደ ማረሚያ ቤት ክለብ ተቀላቀለች።
ማረሚያ ስፖርት ክለብ ውስጥ ለሁለት ዓመት በስልጠናና በውድደር ካሳለፈች በኋላ ወደ ውትድርና ማሰልጠኛ ገባች። በወቅቱ መቶ ሜትር ሁለት መቶና አራት በመቶ ሪሌ ሁልጊዜም አንደኛና ሁለተኛ ትወጣ ነበር።
በወቅቱ አጠራር ከአርሲ ክፍለ ሀገር ከሊሙና ቡልቡሌ ወረዳ ከመራሮ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መጥተው ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ከፋጡማ ሮባ ጋር አድርገው በመውሰድ ቤተሰቦቻቸውን አስፈቅደው፤ ከአሰላ ከተጨመሩ ወደ ስምንት ከሚጠጉ ልጆች ጋር በ 1979 ዓ.ም ነበር ማረሚያ ቤት የስፖርት ክለብን የተቀላቀለችው። የማረሚያ ቤት ስፖርት ክለብን እንድትቀላቀል ያደረጓት ሀጂ ቡልቡላና መቶ አለቃ ተገኝ አለማየሁ የተበሉ ሰዎች እንደነበሩ ትናገራለች።
ይህች ታዳጊ ወጣት በሻዱ ደበሌ አሸኑ ስትባል ከተወለደችባት ቀዬ ውስጥ ሯጭ መሆን ከሚችሉ ወጣቶች መካከል አንዷ መሆኗ ተነግሯት ነበር ከቤቷ የወጣችው። ሯጭ የመሆን ሕልሟን በልቧ ሰንቃ እንደሷ ተመርጠው ከመጡ ወጣቶች ጋር በመሆን ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ስፖርት ክለብ ውስጥ ማረፊያቸው ሆነ። ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ስፖርት ክለብ ካምፕ ውስጥ እየኖሩ ልምምድ እያደረጉና የተለያዩ ውድድሮችን እየተወዳደሩ እያለ ነበር ሯጭ ለመሆን ተፈጠረኩ የምትለወ ወጣት በ1980 ዓ.ም ወደ ሚሊተሪ ክፍል እንድትዘዋወር የተደረገው።
ወደ ውትድርና ክፍል የመዘዋወሪዋ ምክንያት ያልተገለጠላት ይህች ሴት “ እኔ ከእናት ከአባቴ ተለይቼ የወጣሁት ሯጭ ለመሆን እንጂ ወታደር ለመሆን አይደለም»። በማለት ለምን ወደዚያ ክፍል ተዛወርኩ ? “ ብላ በምትጠይቅበት ጊዜ፤ የመስሪያ ቤቱ ሕግ መሆኑንና ከስፖርቱ እኩል ውትድርና መሰልጠን የግድ መሆኑ ይነገራታል።
በወቅቱ አሁን ታዋቂ ሯጭ የሆነቸው ጌጤ ዋሚና ሌሎች አትሌቶች አንድ ላይ ሆነው ወደ ወታደር ማሰልጠኛ ከገቡ በኋላ እዛው ባሉበት ኮማንደሯ ቀድማ የምትወዳደርበትን አጭር ርቀት ትታ ወደ ስምንት መቶና አራት መቶ ሜትር የሩጫ ዘርፍ (ፊልድ) በመቀየር የተሻለ ውጤት ለማምጣት ትጥር ጀመር። በወቅቱ አትሌት ጌጤ ዋሚ የነበረችበት ሁኔታ (ኮንዲሽን) በጣም ጥሩ ስለነበር የማሰልጠኛውን ስልጠና አቋርጣ በውድድር እንድትሳተፍ ተደረገ። በተሳተፈችበት ውደድርም ውጤታማ ሆነች።
ሌሎች ማሰልጠኛ የገቡ አትሌቶች ግን ስልጠናቸውን አጠናቀው ሲወጡ ወደ ስፖርት ክለቡ እንቀላቀላለን ብለው ቢጠብቁም የሆነው ግን ወደ ስፖርታዊ ወድድርና ወደ ወታደራዊ አገልግሎት የሚሄዱትን በእጣ የመለየት ሁኔታ ነበር። ወጣቷ በሻዱም እጣዋ በውትድርና እንድታገለግል የሚል ሆነና ፍቼ ማሪሚያ ቤት ደርሷት እዛ ስድስት ወራት አገለገለች። የውትድርና ሕይወትን በግድም ቢሆን ተቀብላ በስራዋ ውጤታማ ለመሆን የምትጥረው ኮማንደር በፍቼ ማሪሚያ ቤት ስድስት ወራትን ካገለገለች በኋላ በዝውውር መርሃ ቤቴ አውራጃ ዓለም ከተማ ተልካ አንድ ዓመት አገለገለች።
በወቅቱ የደርግ መገርሰስና ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሊመጣ ያለበት የሽግግር ጊዜ ላይ ነበር ዓለም ከተማ ውስጥ የውትድርና ስራ ላይ ተሰማርታ የነበረው። ያኔ ወያኔ ጠንክሮ ዓለም ከተማን ሲቆጣጠር በወቅቱ የነበሩት ወታደሮች ስራቸውን ትተው ወደ ትውልድ ቀያቸው ለመመለስ ተንቀሳቀሱ። ሁሉም ወታደር ተነስቶ ጉዞ ሲጀምር ገና በአፍላው የወጣትነት እድሜዋ ሊያውም ሳትፈልግ የተቀላቀለችውን የውትድርና ሕይወት ጥላ ለመሄድ እሷም ተነሳች።
የተመደበችበትን ስራ ትታ ወደ እናትና አባቷ ቤት ለመሄድ የተነሳችው ኮማንደር እደርሳለው ብላ ካሰበችበት ሳትደርስ መሀል ሜዳ የተባለ ቦታ ለቀናት መታሰራቸውን ታስታውሳለች። ወታደር በመሆናቸው የተነሳ ጥቃት ሊያደርስባቸው ላለ ሁሉ አፀፋ መልስ እየሰጡ ጉዞ ላይ የነበሩት ወታደሮች በሰፊው ተጠቅተው ጉዳት ደረሰባቸው። እሷም እግሯን ተመታች። ቤተሰቧ ጋር ለመሄድ የወጣችው ወታደርም በመቁሰሏ የተነሳ ደብረ ብርሃን ሆስፒታል ገብታ ቆየች።
ቀደም ሲል አባቷ ከስፖርተኞች ክለብ ወጥታ ውትድርና ማሰልጠኛ መግባቷን ሲሰሙ ከሷ ቀድሞ ልጆቻቸውን ለውትደርና ሰጥተው አለመመለሳቸውን አንሰተው “ ይህች ለአቅመ ሄዋን ያልደረሰች ብርቅዬ ልጄን ድጋሚ ለጦርነት አልማግድም “ በማለት አሌልቱ ማሰልጠኛ ድረስ በመሄድ ልጄን ስጡኝ ብለው እንደነበር ታስታውሳለች።
ያኔ የመከላከያ ክለብ ስፖርተኞች በሙሉ የውትድርና ስልጠና እንደሚወስዱ ተነግሯቸው ተረጋግተው ቤታቸው ተመልሰው እንደነበር ታስረዳለች። ደርግ ተገርስሶ ኢህአዴግ ሲገባ መራቤቴ የነበሩ ወታደሮች ሞቱ፤ ተማረኩ ቆሰሉ መባሉን የሰሙት አባት በፊት ሳያምኑበት ልጃቸው ወታደር መሆኗም ሲያሳዝናቸው ስለኖሩ፤ በድንጋጤ ግፊታቸው ጨምሮ ሕይወታቸውን ሊያጡ ቻሉ። ከሞት የተረፈች አንድ ልጃቸውን መልሼ ልውሰድ እያሉ ተከልክለው ለሞት አሳልፈው መስጠታቸው ከአእምሮ በላይ ሆኖባቸው ሞቱ።
ኮማንደርም በአባቷ ሞት ምክንያትና፤ ከቁስሏ እስክታገግም ድረስ ወደ ትውልድ ቀዬዋ ተመለሰች። ኮማንደር ሀዘኑ ከሆዷም ባይወጣ፤ ለሀገር ግዳጅ ተጠርታለችና ከቁስሏም እንዳገገመች ወደ ማረሚያ ቤት ተመለሰች። በደብረ ብርሃን ማረሚያ ቤት ተመድባ እንድትሰራ ቢነገራትም የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ጋር ቀርባ በወቅቱ የነበረባት ተደራራቢ ችግር በማስረዳቷ የተነሳ ከደብረ ብርሃን ወደ አሰላ ማረሚያ ቤት ተዛውራ እንድትሰራ ተወሰነላት። ከዛ በኋላ የተመደበችበትን ግዳጅ እየተወጣች ጎን ጎን ልትሆን ለምትፈልገው አትሌትነት የሚያግዛትን ልምምድ ታደርግ ጀመር።
ያለፍላጎቷ ወታደር የሆነችው ኮማንደር ሕልሟን እውን ለማድረግ ሌት ተቀን ብትለፋም፤ አሸንፋ ለመታየት ብትጥርም ሳይሳካላት ቀረ። የእድሜ መጨመር፤ ጉዳትና ሌሎች ምክንያቶች ተጨማምረው ሯጭ ለመሆን ከቤቷ የወጣችውን ወጣት እድል በመራት መንገድ እንድትጓዝ አስገደዳት።
በፍላጎቷ ያለመችበት ያልደረሰችው ኮማንደር የተሰጣትን በመውደድ ኃላፊነቷን በአግባቡ መወጣት ጀመረች። ሕልሟ እውን ሊሆን እንደማይችል ስትረዳ በተሰማራችበት ሀገሯን ለማገልገል የተሻለ ስራ ለመስራት መጣር ጀመረች። ከልብ የሆነው ጥረትም ፍሬ አፍርቶ ኃላፊነት ቦታ ላይ እየተመደበች ስታገለግል መቆየቷን ትናገራለች።
በሰለጠነችበት የውትድርና ሙያ የተለያዩ የውትደርና ደረጃዎች ላይ በመመደብ የተለያዩ ክልሎችንና ወረዳዎችን እየተዘዋወረች ማገልገል ጀመረች። በዚሁ በውትድርና ሙያዋ ጡረታ እስክትወጣ ድረስ ስታገለግል ቆየች።
ኮማንደር በሻዱ እንደምትለው “በወቅቱ ታዋቂ ስፖርተኛ ከነበሩት ከአትሌት ጌጤ ዋሚ፤ ከአትሌት ፋጡማ ሮባና ከአትሌት ደራረቱ ቱሉ ጋር የተወዳደርኩ፤ ውጤት ማምጣት እየቻልኩ በግድ ወታደር የሆንኩ በመሆኔ ከልብ አዝናለሁ” ትላለች።
አሁን ጡረተኛ የሁለት ወንድ ልጆች እናት ናት፤ ትምህርቷን አቋርጣ ራጭ የሆነችው ልጅ ስራ ላይ ሆና ትምህርቷን በመከታተል ውጤታማ ሆናለች። አሁን ሰው ሃብት አስተዳደር በዲፕሎማ ተመርቃለች።
እድል ምን ጊዜም የራሷ የሆነ መንገድ አላት። አንዳንዶች በለፉት ልክ የእድል መንገዳቸውን አግኝተው ስኬታማ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ ምን ቢጥሩ ሕልማቸውን መኖር ላይችሉ ይችላሉ። ይህ የሚጠበቅና የትም ያለ ሃቅ መሆኑን መረዳት ግን እጅግ አስፈላጊ ነው።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም