የቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶች – በቴክኒክና ሙያ ተቋማት

እንደሀገር ችግር ፈቺና ተኪ የሆኑ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶች በማፍለቅ ረገድ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የማይተካ ሚና አላቸው። ተቋማቱ የሰለጠነ ብቁ የሰው ኃይል ከማፍራት ባሻገር የኅብረተሰቡን ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶች በመስራት ለኅብረተሰቡ እያበረከቱ ይገኛሉ። እነዚህ ስራዎችም ኅብረተሰቡ እንዲያውቅ እና እንዲጠቀምበት ለማድረግ በየዓመቱ በሚዘጋጅ አውደርዕይ ላይ ለእይታ ያቀርባሉ።

በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት በየዓመቱ ሥራቸውን የሚያቀርቡበት የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ይካሄዳል። ዘንድሮም 14ኛው ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ሳምንት ከሰኔ 15 እስከ 20 ድረስ ተካሂዷል። በአውደርዕዩ በርካታ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶች የቀረቡ ሲሆን ሥራዎቹ ተባዝተው የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዙና ተኪ ምርቶችን በስፋት ለማምረት ተነሳሽነትን የሚፈጥሩ እንደሆኑ ታምኖባቸዋል። ይህም ኅብረተሰቡ የተሰሩ ሥራዎችን በመገንዘብ እንዲጠቀም ለማድረግ ያስችላል።

በከተማው የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሰራቸውን ሥራዎች በአውደ ርዕዩ ይዘው ቀርበዋል። ከእነዚህ መካከል የአቃቂ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አንዱ የአውደርዕዩ ተሳታፊ ነው። ኮሌጁ ለእንስሳት መኖ ማቀናበሪያ የሚውል ፕሌት ማሽን ሰርቷል። አቶ አበራ ደሳለኝ አቃቂ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የቴክኖሎጂ ባለሙያ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ ኮሌጁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚሰራው ኢንተርፕራይዞች ያቀረቡትን ፍላጎት መነሻ አድርጎ ነው። የእንስሳት መኖ ማቀናበሪያ ማሽንም አንድ ኢንተርፕራይዝ ባቀረበው ፍላጎት መሠረት ተደርጎ የተሰራ ነው ‹‹አንድ ኢንተርፕራይዝ እንደዚህ አይነት ቴክኖሎጂ ቢሰራልኝ በዚህ ሰርቼ ሀብት ማፍራት እችላለሁ በሚል ይህንን ቴክኖሎጂ እንድንሰራለት ስለጠየቀን ይህንኑ መነሻ በማድረግ ዲዛይን በመስራት በዚህ መልኩ ተሰርቷል። ፍላጎቱን ያቀረበው ኢንተርፕራይዝ የተሰራውን ማሽን ካየ በኋላ የራሱን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ዲዛይን ሊጨምርም ሆነ መጠኑን በማሳነስ ወይም በማተለቅ ሊጠቀምበት ይችላል›› ይላሉ።

ማሽኑ ከተለያዩ ትምህርት ክፍል በተውጣጡ ስድስት አሰልጣኞች የተሰራ መሆኑን ይናገራሉ። የእንስሳት መኖ ማቀናበሪያ ማሽኑ ለዶሮ፣ ለከብቶችና ለጋማ ከብቶች መኖ ማቀናበሪያነት የሚውል ሲሆን ፍላጎቱን ያቀረበው ኢንተርፕራይዝ ብቻ የሚጠቀምበት ሳይሆን፤ ሌሎችም ማሽኑን የሚፈልጉና የሚጠይቁ ኢንተርፕራይዞችም ሆነ ኀብረተሰቡ ሊጠቀምበት የሚችል የቴክኖሎጂ ውጤት ነው ።

እሳቸው እንደሚሉት፤ ማሽኑ ከውጭ ከሚመጣው ጋር በዲዛይን ይለያያል፤ ከውጭ የሚገባው የመኖ ማቀናበሪያ ማሽን የተያያዘና አንድ ላይ ያለ ሲሆን፤ ይሄኛው ግን ሁለቱንም በአንድ ላይ የሚያገናኝ መሳሪያ የተገጠመለት ነው። ሁለቱንም የሚያገናኝ መሳሪያ መገጠሙ በሰው ኃይል ከአንዱ ወደ አንዱ ማሽን የሚደረገውን ሂደት በማስቀረት ማሽኑ በራሱ ፕሮሰስ እንዲያደርግ ያግዛል። ይህ ማሽኑ ከውጭ ከሚገባ የተሻለ እንዲሆን ያደርጋል።

ማሽኑ ከውጭ ከሚገባው ጋር ሲነጻጸር በዋጋ ተመጣጣኝ እንዲሆን ተደርጎ የተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከውጭ የሚገባው በገበያ ላይ እስከ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ሲሆን በሀገር ውስጥ የተሰራው አዲሱ ማሽን ግን 580 ሺ ብር እንደፈጀ ይናገራሉ።

ማሽኑ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ ነው የሚሉት አሰልጣኙ፤ በቀጣይ በሶላር እና በኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሰራ በማድረግ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ እንደሚሻሻል ይናገራሉ። ማሽኑን ለመስራት ጥቅም ላይ የዋሉት ቁሳቁሶች፤ አብዛኛው ላሜራዎች እንደሆኑም ገልጸዋል።

እንደአሰልጣኙ ማብራሪያ፤ የእንስሳት መኖ ማቀናበሪያ ማሽኑ የተለየያ ለእንስሳት በግብዓትነት የሚውሉት እንስሳት መመገብ የሚችሏቸው መኖ አይነቶች ማዘጋጀት ያስችላል። የዶሮ መኖ ለማዘጋጀትም ፍሩሽካ ከተለያዩ ነገሮች ጋር በማቀላቀል ማዘጋጀት የሚያስችል ነው። በተጨማሪም የዶሮ ኩስን ከመኖ ጋር አቀላቅሎ ያዘጋጃል። ማሽኑ በሦስት ደቂቃ አንድ ኪሎ ግራም መኖ ያመርታል።

ማሽኑ አገልግሎት ላይ ውሎ ፍተሻ ተደርጎ ሀሳቡን ያቀረበው ኢንተርፕራይዝ አይቶ የወደደው ስለሆነ አሁን አውደርዕይ ላይ እንዲቀርብ የተደረገበት ዋና ምክንያት ኅብረተሰቡ አይቶት እንዲጠቀምበት ታስቦ መሆኑን ያመላክታሉ። በአሁኑ ወቅት ማሽኑ ለኢንተርፕራይዝ የተላለፈ በመሆኑ ኮሌጁም ሰነዱን ለኢንተርፕራይዝ የሚያስተላልፍ መሆኑን ያስረዳሉ። ኢንተርፕራይዙ ዲዛይን ለመጨመር ሆነ ሌሎች የድጋፍ አገልግሎት ሲያስፈልገው ኮሌጁ አስፈላጊው ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግለት ነው ያስረዱት።

ይህ የመኖ ማቀናበሪያ ማሽን ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራ ቢሆንም ጥራቱን የጠበቀ ነው ያሉት አሰልጣኙ፤ ይህ ማሽን በድጋሚ ቢሰራ ደግሞ ከዚህ በበለጠ እንዲሻሻል ተደርጎ መስራት የሚችል መሆኑን ይገልጻሉ። ማሽኑን በአውደርዕዩ የተመለከቱት አብዛኞቹ ሰዎች ወደውታል እንዲሰራላቸው የፈለጉም በርካቶች እንደሆኑ ጠቅሰው፤ በተለይ ከብቶች እያደለቡ ያሉ ሰዎች ማሽኑን እንደሚፈልጉት ይናገራል። ‹‹በቀጣይም ከኅብረተሰቡ የተሰጡት አስተያየቶች በመሰብሰብ የተሻለ ስራ ሰርተን እናሳያለን ››ብለዋል።

ሌላኛው የአውደርዕዩ ተሳታፊ የምስራቅ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ነው። የኮሌጁ አሰልጣኝ ዳኛቸው ወልደሚካኤል ኮሌጁ በርካታ የቴክኖሎጂና ፈጠራ ሥራዎች እየሰራ ቢሆንም ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑትን በአውደርዕዩ ይዞ መቅረቡን ይገልጻሉ። ማንኛውንም አይነት የባልትና ውጤት ማቀነባበሪያ ማሽን፣ የቃጫ ማውጫ ማሽን እና የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖች በአውደ ርዕዩ ቀርበዋል።

ከእነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አንዱ የሆነው በኮሌጁ አሰልጣኞች የተሰራ ማንኛውንም አይነት የባልትና ውጤት ማቀነባበሪያ ማሽን ነው። እሳቸው እንደሚሉት፤ ይህ ማሽን በተለየ መልኩ ማንኛውንም አይነት የባልትና ውጤት ለማቀነባበር ያስችላል። ማሽኑ ሦስት አይነት ሲሆን፤ አንደኛው ማሽን የባልትና ውጤቱ የሚቆላበት፣ የሚታመስበት፣ የሚደርቅበት፣ እና የሚቀዘቅዝበት ነው። ሁለተኛው ማሽን የባልትና ውጤቱ የሚፈጭበት ሲሆን ሦስተኛው ማሽን ደግሞ የሚታሸግበት ነው። እነዚህ ሦስቱ ማሽኖች የባልትና ውጤትን ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ የሚደረገውን ሂደቶች ይከናወንበታል።

‹‹ማሽኑ የምንጠቀማቸው የተለያዩ የባልትና ውጤቶች ሁሉንም ሂደቶች በምንፈልገው ልክ እንደራሳችን ፍላጎት እያደረግን ለመስራት የሚያስችል ነው። የተወሰኑት ጤፍ መሰል ነገሮችን አይቆላም እንጂ እንደስንዴ፣ ገብስ እና የመሳሳሉት ደግሞ የመብሰል በሚገባው መጠን የሚያበስልና የሚቆላም ነው። እንዲሁም እንደቆሎ ለመቁላት ያስችላል›› ብለዋል።

‹‹ማሽኑ በአንድ ጊዜ እስከ 25 ኪሎ ግራም እህል የመቁላት አቅም አለው›› ያሉት አሰልጣኙ፤ ይህ ማሽን ለየብቻ የተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሦስቱንም ማሽኖች በማገናኘት በአንድ ላይ ቢያያዙ ደግሞ ይበልጥ የሥራ ቅልጥፍና ይጨምራል፤ ሰዓት ይቆጥባል፤ ምርታማነትንም ይጨምራል። በማለት በቀጣይም እነዚህን ማሽኖች በአንድ ላይ በመገጣጠም እንደሚሰሩ አመላክተዋል።

ማሽኑን አብዛኛው በቀላሉ ከሚገኙ ማቴሪያሎች የተሰራ ሲሆን፤ የሚሰራው በኤሌክትሪክ ኃይል ነው። አሁን ላይ በኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሰራ የተደረገ ቢሆንም በሌሎች ሲስተሞች እንዲሰራ አድርጎ መስራት የሚቻል መሆኑን ጠቁመዋል።

አሰልጣኙ ‹‹እንደዚህ አይነት ማሽኖች በሌላው ዓለም ላይም ያሉ ናቸው። ካሉት ውስጥ ግን ተመራጭ እና ወጪ ቆጣቢ የሆነውን እያወዳደርን የሚጨመሩት ነገሮች እየጨመርን ነው የሰራነው›› ይላሉ። ከውጭ ከሚመጣው ጋር ሲነጻጸር እያንዳንዱ የማሽኑ ዋጋ የተሻለና በግማሽ ያህል ቅናሽ ያለው ነው፤ ማሽኑ በሀገር ውስጥ በስፋት የሚመረት ከሆነ ደግሞ ለበርካታ ሰዎች የሥራ እድል ይፈጥራል። ተጠቃሚውን ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እንዲያመርት ስለሚያስችለው ምርታማ ያደርገዋል ብለዋል።

እሳቸው እንደሚሉት፤ የሀገር ውስጥ ምርቶች ላይ የሚታየው የጥራት ችግር በሂደት የሚቀረፍ ነው። በተደጋጋሚ ሲሰራ ብዙ ነገሮች እየተስተካከሉ መሻሻሎች እየመጡ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። ማሽኑ በአውደ ርዕዩ ከቀረበ በኋላ የሚሰጡ አስተያየቶችን በመጨመር ኢንተርፕራይዞቹ በምን መልኩ አሻሽለው መጠቀም እንደሚችሉ ምክረ ሀሳብ ይሰጣል። ማሽኑ ተባዝቶ ተሻሽሎ ለገበያ ሊውል ይችላል። አሁን ላይ የሀገር ውስጥ ምርቶች መጠቀም ላይ መሻሻሎች እየታዩ ኅብረተሰቡ የውጭውን እየተወ የሀገር ውስጥ ምርቶች እየተጠቀመ መምጣቱ አበረታች ነው።

እስካሁን የሚሰሩት ቴክኖሎጂዎች ለኢንተርፕራይዞች የሚተላለፉበት ሁኔታ እንዳለ ያነሱት አሰልጣኙ፤ ነገር ግን በቀጣይ በኮሌጁ አምርቶ እንዲያበዛ የሚደረግበት አሠራር ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን ኅብረተሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን ለማቅረብ እንደሚሰሩ ይገልጻሉ። በቀጣይ ምስራቅ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ኅብረተሰቡ ሊጠቀምባቸው የሚችለውን ቴክኖሎጂዎች በመስራት ያቀርባል ሲሉ አስገንዝበዋል።

በኮሌጁ የተሰራው ሁለተኛው ቴክኖሎጂ የቃጫ ማውጫ ማሸን ሲሆን፤ በሰልጣኞችና በአሰልጣኞች እገዛ የሰሩት መሆኑን ገልጸው፤ ይህ ማሽን ሀገር በቀል ቴክኖሎጂ ላይ የተሰራ በመሆኑ በቀላሉ ቃጫ በመፋቅ የቃጫ ውጤት የሚያቀርብ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሦስተኛው የቴክኖሎጂ ውጤት የመኖ ማቀናበሪያ ማሽን ነው። ይህ ማሽን አነስተኛ መጠን ያለው ሲሆን በውስጥ ያለውን መፍጫ ብቻ በመቀያየር ማንኛውንም አይነት የእንስሳት መኖ ለማቀነባበር ይጠቅማል። በአሁኑ ወቅት በኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሰራ የተደረገ ሲሆን፤ በሌሎች የኃይል አማራጮች እንዲሰራ ማድረግ እንደሚቻልም ይገልጻሉ።

ኮልፌ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅም በአውደ ርዕዩ በርካታ ቴክኖሎጂ ውጤቶች ይዞ ከቀረቡት መካከል ይገኝበታል። አቶ ወርቅነው ሰማኝ የኮልፌ ኢንዱስትሪያል ኮሌጁ የማኑፋክቸሪንግ አሰልጣኝ ናቸው። ኮሌጁ የሸክላ መፍጫ ማሽን፣ ሻምፖና ኮንዲሽነር ማምረቻ ማሽን እና ብረት በተለያዩ ቅርጻች ለማውጣት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሰርቷል።

የሸክላ መፍጫ ማሽኑ በአራት አሰልጣኞች የተሰራ ሲሆን፣ ይህ ማሽን ምጣድም ይሁን ማንኛውንም አይነት የተሰባበረ ሸክላ በመፍጨት ወደ አፈርነት ያቀይራል። ሸክላው ወደ አፈርነት ከተቀየረ በኋላ መልሶ ይቦካና የተፈለገውን አይነት የሸክላ ቁስ ይሰራበታል። በመሆኑም ማሽኑ በሰዓት እስከ አንድ ኩንታል ወይም መቶ ኪሎ ግራም አፈር ይፈጫል።

ማሽኑን በቀላሉ ከሚገኙ ማቴሪያሎች የተሰራ በመሆኑ ከውጭ ከሚመጣው ጋር የተመሳሳይነት ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ ቴክኖሎጂ ከውጭ ከሚመጣ የተቀዳ ቢሆንም ከውጭ ከሚመጣው ማሽን የተሻለ እንደሆነ አመላክተዋል።

በዋጋም ከውጭ አገር ከሚመጣው ጋር ሲነጻጻር በተመጣጣኝ የሚባል ዋጋ እንዳለው ያመላክታሉ። ከውጭ የሚገባው ማሽን ለመግዛት 480 ሺ ብር የሚጠይቅ ሲሆን፤ ይህ ማሽን ግን 115 ሺ ብር እንደፈጀ ተናግረዋል። ይህ ቴክኖሎጂ ሀገር በቀል ቴክኖሎጂ በኢንተርፕራይዞች ፍላጎት መሰረት የተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል። ‹‹በሀገራችን ብዙ የሸክላ ሠሪዎች መኖራቸውና አብዛኛውን ጊዜ እንጀራ ለመጋገር የምንጠቀመው የሸክላ ምጣድ ስለሆነ ይህንን የሸክላ ምጣድ ለመስራት ደግሞ ሸክላ ሰሪ ባለሙያዎች የሚጠቀሙት አፈር እስካሁን ድረስ በእጃቸው የእየፈጩ ነው። በመሆኑም ማሽኑ ይህ ችግር ለመቅረፍ ታስቦ የተሰራ ነው›› ይላሉ።

በመሆኑ ኅብረተሰቡ አውቆ እንዲጠቀምበት በአውደርዕይ መቅረቡን ጠቁመው፤ ማሽኑን አምርተው ለተጠቃሚ ለሚያቀርቡ ኢንተርፕራይዞች የተሸጋገረ ነው። ከዚህ በኋላ ኢንተርፕራይዞቹ ዲዛይኑን ወስደው ማምረት ይችላሉ ሲሉ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ሻምፖና ኮንዲሽነር ማምረቻ ማሽን ይዘው መቅረባቸውን የገለጹት አሰልጣኙ፤ ይህ ማሽን እንደሌሎቹ ማሽኖች ሁሉ በሀገር ውስጥ የተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በጥራት ሆነ በዋጋ ከውጭ ከሚመጣው በጣም የተሻለ እንደሆነ ይገልጻሉ። ‹‹በአገር ውስጥ የሚሰሩት ማሽኖች ጥራታቸው የጠበቁ ከመሆናቸው በላይ በአገር ውስጥ ሊጠገኑ የሚችሉ ናቸው›› ይላሉ። ብዙ ጊዜ ከውጭ የሚመጡ ማሽኖች ለጥገናም ቢሆን የማይቻልበት እና ግዴታ ባለሙያ የሚፈልጉ ስለሚሆኑ ይህ ማሽን ግን ሁሉ ነገር ገልጸው ስለሆነ ማንኛውም መካኒክ ሊጠግነው የሚችለውን መሆኑን ገልጸው፤ እንዲሁም ለረጅም ጊዜ እንዲያገለግል ተደርጎ የተሰራ መሆኑም ለየት እንደሚያደርገው አመላክተዋል።

ሌላው የሰውን ጉልበት በመቀነስ ድፍን ብረቶች ለተለያዩ ጌጣጌጦች በሚሆን መልኩ ለመስራት የሚያስችል ማሽን መስራታቸውን አንስተዋል። ማሽኑ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ካልሆነ አብዛኛው ሀገር ውስጥ የሌለ መሆኑን ገልጸው፤ በሀገር ውስጥ የተሰራ በመሆኑ የሀምሳ ሺ ብር ያህል ቅናሽ እንዳለው አመላክተዋል። በተለይ ጥገና ላይ የሰራው አካል በቦታው ተገኝቶ ጥገና ማድረግ የሚችልበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል።

አሁን ላይ ያሉት ሁሉም ማሽኖች የተሸጋገሩ ስለሆኑ በቀጣይ ኮሌጁ ከኢንተርፕራይዝ ፍላጎት በመነሳት ኅብረተሰቡን ሊጠቅሙ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን የሚሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You