12ኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከነገ ጀምሮ በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ አስተናጋጅነት ለተከታታይ አምስት ቀናቶች ይካሄዳል፡፡ በውድድሩ የሚስተዋለውን የእድሜ ማጭበርበር ለመከላከል የህክምና ምርመራ በማድረግ የቅጣት እርምጃ እንደሚወስድም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየዓመቱ የሚያዘጋጀው ከ20 እና ከ18 ዓመት በታች የወጣቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከነገ ሰኔ 25 – ቅዳሜ ሰኔ 29/2016 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ አስተናጋጅነት ይካሄዳል። የሩጫ እና ሜዳ ተግባራትን በማካተት የሚካሄደው ውድድሩ ከክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች እና ክለቦች የተወጣጡ ታዳጊ አትሌቶች ውድድራቸውን ያካሂዳሉ። የውድድሩ ዓላማም በክለቦች ለሚገኙ ታዳጊና ወጣት አትሌቶች የውድድር እድልን በመፍጠር ሀገርን የሚወክሉ ውጤታማና ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት ነው። በተጨማሪም በነሐሴ ወር አጋማሽ በፔሩ ዋና ከተማ ሊማ በሚካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ወጣቶች ቻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች እንደሚመረጡበትም ፌዴሬሽኑ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
በቻምፒዮናው 10 ክልሎች፣ 2 ከተማ አስተዳደሮች፣ 32 ክለቦች እና የማሰልጠኛ ተቋማት ይሳተፋሉ፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አትሌቶች የሚካፈሉበት ሲሆን፤ 422 ሴት እና 549 ወንድ በድምሩ 971 አትሌቶች የሚፎካከሩም ይሆናል። ለውድድሩ የሚያስፈልገው ዝግጅትም ተጠናቋል፤ በዚህም ዓለም አቀፍ ስልጠና የወሰዱ እና ብቁ የሆኑ 80 ዳኞች ውድድሩን ለመምራት ተመድበዋል። በተጨማሪም የበጎ ፍቃደኛን ጨምሮ ከ150 ሰው በላይ ውድድሩን ለመምራትና ለማስተባበር ተዘጋጅተዋል። ለዚህም በቂ የሆነ በጀት የተመደበ ሲሆን፤ የአስተናጋጁ ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ እንዲሁም የጸጥታ ክፍሉ ቅድመ ዝግጅት አድርጓል፡፡ ለውድድሩ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችም ተሟልተዋል፡፡
በፌዴሬሽኑ የተሳትፎና ውድድር ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ፤ ታዳጊ አትሌቶች በሀገር ውስጥ በለመዱት የአየር ንብረት የውድድር እድል መፍጠር የውድድሩ ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በስልጠና እና ውድድሮች ላይ የቆዩ ታዳጊ አትሌቶችን በሽልማት ማበረታታትና በቀጣይም በዓለም አቀፍ ውድድር ሀገራቸውን እንዲወክሉ ማድረግ ሌላው ተጠቃሽ ነጥብ ነው፡፡ ማንኛውም አትሌት ያለ ትክክለኛ እድሜው የማይወዳደር ከሆነ እርምጃ እንደሚወሰድበትም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
የህክምና ክፍሉ ከፍተኛ ባለሙያ ዶክተር አያሌው ጥላሁን በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ተገቢና ተተኪ አትሌቶች የሚያስፈልጉት ቢሆንም ከእድሜ ጋር ተያይዞ ችግር እንደገጠመው ጠቁመዋል፡፡ ክለቦች፣ ክልሎች እና አሰልጣኞች፣ አትሌቶችን ያለ እድሜያቸው የሚያወዳድሩ በመሆኑ ከዓለም አቀፉ ተቋምም ጭምር የቅጣት ስጋት ሊፈጥር ችሏል፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንዲሁም እርምጃዎች ተወስደውም መፍትሔ ማምጣት አልተቻለም፡፡ ተተኪን ለማፍራት እና ስፖርቱን ለማሳደግ ሳይሆን ለዋንጫና ለዝና እንደሚሰሩም በርካቶች ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ፌዴሬሽኑ በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ አዲስ የምዝገባና የመረጃ ስርዓትን ለመጀመር ተዘጋጅቷል፡፡ የመጨረሻው የመቆጣጠሪያ ሙከራ በዚህ ውድድር የሚደረግ ሲሆን፤ ሁሉም ክልል እና ከተማ አስተዳደር የእድሜ ምርመራ በማድረግ በህክምና ባለሙያዎች አስፈርሞ እንዲመጣ መደረጉንም ዶክተር አያሌው ገልጸዋል። በውድድሩ በሚገኘው ውጤት መሰረት ሀገራዊ ውሳኔን በማሳለፍ ከዜሮ ለመጀመርም ታቅዷል። በተጨማሪም በፔሩ ሊማ ለሚደረገው የወጣቶች ቻምፒዮና የሚያልፉትን አትሌቶች በህክምና ምርመራ ለመለየት ጥረት ይደረጋል። አሰላ በተካሄደው ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮና 800 የሚደርሱ አትሌቶች እድሜን በማጭበርበራቸው ከውድድር መሰረዛቸውንም ባለሙያው አስታውሰዋል፡፡
አሸናፊ አትሌቶቹን ለማበረታታት ከሜዳሊያ ሽልማት በተጨማሪ እንደየደረጃቸው የገንዘብ ሽልማት የተዘጋጀ ሲሆን፤ ከ1ኛ እስከ 3ኛ የሚወጡ አትሌቶች 1ሺ ብር፣ 800 ብር እና 500 ብር ይሸለማሉ፡፡ በሪሌ ውድድር ከ1-3 የሚወጡት ደግሞ 3 ሺ ብር፣ 2 ሺ ብር እና 1ሺ500 ብር በቅደም ተከተሉ መሰረት ያገኛሉ። በቡድን ውጤት ቀዳሚ ለሚሆኑት ሶስቱ ቡድኖችም ከ10 ሺ ብር -3 ሺ ብር የገንዘብ ሽልማት ይበረከትላቸዋል፡፡ በድምር የቡድን ውጤት አንደኛ የሚወጣ 15 ሺ ብር፣ ሁለተኛ 10 ሺ ብር እና ሶስተኛ ደረጃን የ8 ሺ ብር ሽልማት የተዘጋጀ ሲሆን ወደ 444 ሺ ብር ለሽልማት ወጪ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም