ታዋቂው ተጫዋች የመቻል ስፖርት ክለብን ለመጎብኘት ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል

አንጋፋው የስፖርት ክለብ መቻል 80ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓሉን በተለያዩ ክንውኖች በማክበር ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። ስፖርታዊ ውድድሮች፣ የፓናል ውይይት፣ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ከክንውኖቹ መካከል የሚጠቀሱ ሲሆን፤ ዓለም አቀፍ ታዋቂ ስፖርተኛን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ልምዱን እንዲያካፍል ማድረግም ይገኝበታል። በዚሁ መሰረት ፖርቹጋላዊው የእግር ኳስ ኮከብ ሉዊስ ካርሎስ አልሜይዳ (ናኒ) ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ተረጋግጧል።

መቻል ስፖርት ክለብ ከሰኔ 1—2016 ዓ·ም ጀምሮ የ80ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓሉን የቀደመ ታሪኩን በሚዳስሱና ወደ ፊት ከአፍሪካ ምርጥ ክለቦች ተርታ ሊያሰልፉት የሚችሉትን እቅዶች ነድፎ በተለያዩ ክንውኖች እያከበረ ይገኛል። ለዚህም እንዲረዳው ካዘጋጃቸው ስፖርታዊ ኩነቶች በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ ስፖርተኞችን ጋብዞ ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ማድረግ ይገኝበታል። በዚህም የክለቡ የክብር እንግዳ በመሆን ልምዱን እንዲያካፍል የተመረጠው አንጋፋው እና የቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድ ተጫዋች ናኒ እንደሆነ በተሰጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ተጠቅሷል።

ሉዊስ ናኒ በትልቅ ደረጃ በእንግሊዙ ማንችስተር ዩናይትድ፣ ስፖርቲን ሊዝበን፣ ፌነርባቼ፣ ቫሌንስያ እና ላዚዮ የተጫወተ ሲሆን፤ አሁን ለተርኪዬው ክለብ አዳና ዴሚር ስፖርት ክለብ በመጫወት ላይ ይገኛል። በትልልቅ አውሮፓ ሊጎችና የእግር ኳስ ክለቦች በብቃት የተጫወተውና ከፍተኛ ልምድ ያከበተው ኮከቡ መቻልን የሚጎበኝ ሲሆን፤ የክለቡን ስፖርተኞችም ያበረታታል። ሐምሌ 6/2016 ዓ·ም ከጠዋቱ 12 ሰዓት ከፖርቹጋል ሊዝበን ተነስቶ አዲስ አበባ እንደሚገባ እና በክብር እንግድነት እንደሚገኝም ይጠበቃል።

ተጫዋቹ የአንጋፋው ክለብ የክብር እንግዳ ሆኖ እንዲገኝ አስፈላጊው ሂደት መጠናቀቁንና የተጫዋቹ መምጣት ብቻ እየተጠበቀ እንደሆነ የቦርዱ አመራር ዶክተር ሰይፉ ጌታሁን ገልጸዋል። የተጫዋቹ የዘር ግንድ ከምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ኬፕ ቨርዴ የሚመዘዝ ቢሆንም፣ አፍሪካን የጎበኘው ግን አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ሁለተኛው የአፍሪካ መዳረሻውም ኢትዮጵያና መቻል የስፖርት ክለብ ይሆናል።

ክለቡ ተጫዋቹን በኢትዮጵያዊ ደንብ አቀባበል በማድረግ ልምዱን እና እውቀቱን ለማካፈልም ዝግጅቱን አጠናቋል። በተጨማሪም የመቻል ስፖርት ክለብን እና የመከላከያ ተቋማት ጉብኝት መርሃ ግብሮች ተይዘዋል። ተጫዋቹ እንዲመጣ የተፈለገው በሁለት ምክንያቶች መሆኑን ያስረዱት የቦርዱ አመራር፤ የልምድ ልውውጥ እንዲሁም ክለቡን ወደ ተሻለ እና ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንዲቻል የግሉ ከሆነው የእግር ኳስ ማሰልጠኛ አካዳሚ ጋር ስምምነት ለመፈራረም እንደሆነ አስረድተዋል።

መቻል ስፖርት ክለብ ታሪካዊ እና ለኢትዮጵያ ስፖርት ትልቅ አበርክቶ ያለው ክለብ እንደመሆኑ ተጫዋቹ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንቅስቃሴዎችንም እንደሚጎበኝ ተመላክቷል። የወንዶች እግር ኳስ ክለቡ ከዩጋንዳው ክለብ ኪታራ ጋር የሚያደርገውን የወዳጅነት ጨዋታንም ይታደማል። በተጨማሪም የክለቡን ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኑን፤ እንዲሁም የክለቡ ሙዚየም የጉብኝቱ አካል ይሆናሉ።

ተጫዋቹ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የሚያደርገውን ጉብኝት አስመልክቶም አጭር የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፏል። በዚህም መሰረት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የመቻል ስፖርት ክለብ 80ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ለመታደም እድል በማግኘቱ ደስተኛ መሆኑን እና ኩራት እንደሚሰማው ተናግሯል። ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ በመሆኗ በልቡ ውስጥ ልዩ ስፍራ እንዳላትና በቅርቡ የክለቡን ስኬትና ታሪክ እንደሚጎበኝ ጠቁሟል።

መቻል ታዳጊዎች ላይ ለመስራት ያለውን እቅድ ተከትሎ ሉዊስ ካርሎስ አልሜይዳ (ናኒ) እስከ አሁን እየተጫወተ በመሆኑ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑን እንዲያበረታታ ተመርጧል። ተጫዋቹ በፖርቹጋል የራሱ አካዳሚ ስላለውና ሌላ መክፈት ስለሚፈልግ በጋራ ወደ ትግበራ ለመግባትም ታስቧል።

ክለቡ ነገ ሰኔ 23/2016 ዓ·ም ከ30ሺህ በላይ ህዝብ የሚሳተፍበትን የሩጫ ውድድር ያካሂዳል። በተጨማሪም፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ አብዛኞቹ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች የሚሳተፉበት የእራት ግብዣ ሰኔ 30 በስካይላይት ሆቴል ይካሄዳል። በመድረኩ እስከ አንድ ሺህ ሰው ይታደማል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ብዙ ገንዘብ እንደሚያሰባስብም ተገልጿል።

አለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You