እሥራኤልና ሊባኖስ ወደከፋ ጦርነት እንዳያመሩ አስግቷል

እሥራኤልና ሊባኖስ የገቡበት ፍጥጫ ወደከፋ ጦርነት እንዳያመራ አስግቷል።

በአሜሪካ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የእሥራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንት እሥራኤል ከሊባኖስ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት እንደማትፈልግ ተናግረዋል።

“ጦርነቱን አንፈልገውም፤ ይሁን እንጂ በማንኛውም መንገድ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነን፤ ሄዝቦላህም ጦርነቱ ቢጀመር በሊባኖስ ላይ የሚደርሰውን ከባድ ኪሳራ ጠንቅቆ ያውቀዋል” ነው ያሉት።

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንት በበኩላቸው ከሄዝቦላህ ጋር የሚደረግ ጦርነት በመካከለኛው ምሥራቅ ከባድ ቀውስ እንደሚያስከትል ነው ለጋላንት የነገሯቸው።

በጋዛው ጦርነት የእስራኤል ሁነኛ አጋር መሆኗን ያሳየችው አሜሪካ የሊባኖስ እና እሥራኤል ውጥረት በዲፕሎማሲያዊ ንግግር እንዲፈታ ጥሪ ማቅረቧንም ፍራንስ 24 አስነብቧል።

ጀርመን እና ካናዳ በሊባኖስ የሚኖሩ ዜጎቻቸውን ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የመከሩ ሲሆን፥ ውጥረቱን የሚያረግብ ንግግር እንዲጀመር ጠይቀዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፍትስ ከጄኔቫ በሰጡት መግለጫ ሊባኖስ ላይ የሚጀመር ጦርነት ወደ ሶሪያና ሌሎች ሀገራት ሊስፋፋ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

የሊባኖስ ብሔራዊ የዜና ወኪል እስራኤል በአንድ ቀን ብቻ 10 የአየር ጥቃቶችን መፈጸሟን ዘግቧል።

ሄዝቦላህ በአንጻሩ በእሥራኤል የድንበር ከተሞች በሚገኙ ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ በ24 ሰዓት ውስጥ ስድስት ጥቃቶችን መፈጸሙን ነው ያስታወቀው።

የቡድኑ መሪ ሐሰን ናስራላህ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ እሥራኤል በሊባኖስ ላይ ጦርነት ብታውጅ የሚደርስባትን ታውቀዋለች ሲሉ መዛታቸው ይታወሳል።

ናስራላህ “ጠላቶቻችን (እሥራኤል) ለከባድ ጊዜ በሚመጥን ደረጃ ያደረግነውን ዝግጅት ያውቁታል፤ የድሮን እና ሮኬት ጥቃቶችን ሊቋቋሙት አይችሉም” ነበር ያሉት።

የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንይሁ በጋዛ “መጠነ ሰፊው ዘመቻ” እየቀነሰ መሄዱን ካሳወቁ በኋላ 10ኛ ወሩን ሊይዝ የተቃረበው ጦርነት መቀዛቀዙ እየተነገረ ነው።

እሥራኤል ከጋዛ የምታስወጣቸውን ወታደሮቿን ወደ ሊባኖስ ድንበር እንደምታሰማራ ኔታንያሁ መናገራቸውም ይታወሳል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2016

Recommended For You