የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪን በአራት ደቂቃ የሚሞላ ቻርጀር ተሠራ

የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪን በአራት ደቂቃ የሚሞላ ቻርጀር ተሠራ።

በዓለማችን ላይ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ፍላጎት እና ምርት እየጨመረ ይገኛል። ይሁንና እነዚህን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እንደ ልባቸው ሊስተናገዱበት የሚችሉት ቻርጀር ማግኘት አዳጋች ሆኗል።

ሌላኛው አስቸጋሪ ነገር ደግሞ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቻርጅ ለማድረግ የሚፈጀው ጊዜ ረጅም መሆን ሲሆን በየጊዜው እየተሻሻለ በመምጣት ላይ ይገኛል።

የእንግሊዙ ኒዮቦልት የቴክኖሎጂ ኩባንያ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን በቶሎ ቻርጅ ለማድረግ መላ አግኝቻለሁ ብሏል።

ኩባንያው እንግዶች በተገኙበት በአራት ደቂቃ ውስጥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባትሪን እንደሚሞላ አረጋግጧል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

በስፖርት ተሽከርካሪ ላይ የተሞከረው ይህ የባትሪ ቻርጀር በአራት ደቂቃ ውስጥ 80 በመቶ እና ከዛ በላይ መሙላት የቻለ ሲሆን በቅርቡ ተጨማሪ ሙከራዎችን እና ማሻሻያዎችን በማድረግ ለገበያ እንደሚውል አስታውቋል።

አሁን ላይ የኢለን መስኩ ቴስላ ኩባንያ ይፋ ያደረገው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባትሪ መሙያ ጊዜ ከ15-20 ደቂቃ ይፈጃል።

የዓለማችን የቴክኖሎጂ ኩባያዎች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባትሪ የሚሞላበትን ጊዜ ለማሳጠር በሙከራዎች ላይ ሲሆኑ የዓለም ገበያን እየተቆጣጠሩ የመጡት የቻይና ኩባንያዎች አዲስ ፈጠራ ይፋ እንደሚያደርጉ ይጠበቃሉ።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You