በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ክርክር ትራምፕ በባይደን ላይ የበላይነትን ተቀዳጁ

ለ2024ቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሚፎካከሩት ጆ ባይደን እና ዶናልድ ትራምፕ ሰሞኑን የመጀመሪያውን የፊት ለፊት ክርክራቸውን አድርገዋል።

በሴኤንኤን አዘጋጅነት በተደረገው የአሜሪካ የፕሬዚዳንታዊ ተፎካካሪዎች ክርክር ለ90 ደቂቃ የቆየ ሲሆን፤ ክርክሩን የሪፕሊካኑ ተወካይ ዶናልድ ትራምፕ የበላይነት የያዙበት ነው ተብሏል።

ፕሬዚዳንት ባይደን አቅማቸውንና አለመድከ ማቸውን ሊያሳዩ፤ ገና ሌላ የሥልጣን ዘመንን የመምራት አካላዊና አዕምሯዊ ብቃት እንዳላቸው ሊያስመሰክሩ ነበር ያለሙት።

ያም ሆኖ ጆ ባይደን እ.አ.አ. በ2024 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዘመቻ የመጀመሪያው የቴሌቪዥን ክርክር የ90-ደቂቃ ፍልሚያ ላይ ደካማ አፈጻጸም አሳይቷል ነው የተባለው።

ጆ ባይደን ድምፃቸው ደክሞ፣ በራስ መተማመናቸው ጠፍቶ፣ አቀርቅረው፣ ሃሳባቸው ተበትኖና አንደበታቸው ተሳስሮ ነበር ክርክሩን የጨረሱት።

በክርክሩ ወቅት ትራምፕ ባይደንን በኢኮኖሚው እና በውጭ ፖሊሲ ላይ ደጋግመው ያጠቁ ሲሆን፤ ባይደን በአንጻሩ በተፎካካሪያቸው የወንጀል ክስ እና እ.አ.አ የ2020 ምርጫን ለመቀልበስ ሙከራዎች በማንሳት አጥቅተዋል።

ባይደን ትራምፕን “ተሸናፊ እና “የዱር ድመት ሞራል” ያለው ሰው ነው ሲሉ ዘልፈዋቸዋል።

ትራምፕ በምላሹም፤ በባይደን ስህተቶች ላይ ተንተርሰው፤ ባይደንን ሃሳባቸው ግልጽ ያልሆነ፣ ከሕዝብ እሳቤና ችግር የተፋቱ አድርገው አቅርበዋቸዋል።

በክርክሩ ማብቂያ ላይ በተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት ትራምፕ 67 በመቶ ባይደን ደግሞ 33 በመቶ ድምፅ በማግኘታቸው ትራምፕ ክርክሩን በሰፊ ልዩነት ማሸነፋቸውን አሳይተዋል።

ዴሞክራቶች በፕሬዚዳንቱ አፈጻጸም ላይ ስጋታቸውን ገልጸዋል የተባለ ሲሆን፤ የፓርቲው የውስጥ አዋቂዎች ቀደም ሲል የሰጡት መልሶች ፍርሃትን እንዳጫረባቸው ተናግረዋል።

ሆኖም ግን ምክትል ፐሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ “በዝግታ የተጀመረ፣ ነገር ግን ጠንካራ አጨራረስ የነበረው” ሲሉ ለባይደን ወግነው ተከራክረዋል።

የ81 ዓመቱ የዴሞክራት እጩ ጆ ባይደን እና የ78 ዓመቱ ሪፐብሊካን ዶናልድ ትራምፕ እ.አ.አ. በ2020 ሁለት ጊዜ የፊት ለፊት ክርክር አድርገዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You