የስዊድኗ ከተማ ነዋሪዎችን ለመሳብ መሬት በ10 ሳንቲም አቀረበች

በነዋሪዎች ድርቅ የተመታችው የስዊድኗ ጎተን ከተማ ቤት መሥሪያ መሬት በርካሽ አቀረበች፡፡

የስዊድኗ ጎተን ከተማ በአውሮፓ ካሉ ከተሞች መካከል በየዓመቱ አነስተኛ ሕጻናት ከሚወለዱባቸው ከተሞች መካከል አንዷናት፡፡

እንዲሁም ይህች ከተማ በእድሜ የገፉ ሰዎች ከሚኖሩባት ከተሞች መካከልም አንዷ ስትሆን የከተማዋ አስተዳደር ተጨማሪ ነዋሪዎች እንዲመጡ ማበረታቻዎችን ዘርግቷል፡፡

ለሁለት ዓመት ይቆያል የተባለው ይህ ማበረታቻ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ሁሉ በጎተን ከተማ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ በርካሽ አቅርቧል።

የከተማዋ ከንቲባ ጆሃን ማንሰን ለዩሮ ኒውስ እንዳሉት ወደ ጎተን ከተማ መጥተው ለሚኖሩ እና ቤት መሥሪያ ለሚፈልጉ ሰዎች አንድ ስኩዌር ሜትር ቦታ በአንድ የስዊድን ክሮና ወይም በ0 ነጥብ 08 ዶላር ዋጋ እንሸጣለን ብለዋል፡፡

ይህ ማበረታቻ ከተያዘው 2024 ጀምሮ እስከ ቀጣዩ ዓመት ድረስ ይቆያል ያሉት ከንቲባው ለሽያጭ የቀረበው ቦታ ለመኖሪያ ምቹ በሆኑ በከተማዋ እምብርት ላይ የሚገኝ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

“ለማንኛውም ሰው መሬቱን ለመሸጥ ዝግጁ ነው ዋናው እዚህ እኛ ከተማ መጥቶ ለመኖር ፍላጎት ብቻ ይኑረው” ሲሉም ከንቲባው አክለዋል፡፡

ይሁንና መሬቱን የገዙ ነዋሪዎች በሁለት ዓመት ውስጥ መኖሪያ ቤቱን መገንባት አልያም ግንባታውን መጀመር እንደሚኖርባቸው ይህ ካልሆነ ግን መሬቱን ሊነጠቁ እንደሚችሉ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡

ጎተን ከተማ በአውሮፓ ካሉ ውብ ስፍራዎች መካከል አንዷ ስትሆን በመልክዓ ምድር አቀማመጥ፣ የዱር እንስሳት እና ሌሎች የሚጎበኙ ስፍራዎችን የያዘች ከተማ ናት፡፡

ከተማዋ ማስታወቂያውን ካወጣች በኋላ በአንድ ወር ውስጥ ሦስት የመኖሪያ ቤት መሬት የተሸጠ ሲሆን በቀጣዮቹ ጊዜያት ተጨማሪ ገዢዎች እንደሚመጡ ይጠበቃል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2016

Recommended For You