በሱዳን ከጥይት በበለጠ ረሃብ በርካቶችን ለሞት እየዳረገ ነው – ሃምዶክ

በሱዳን ጦርነት ምክንያት በረሃብ የሚያልቀው ሕዝብ ቁጥር አሳሳቢ መሆኑን የቀድሞው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ተናገሩ።

ሃምዶክ ከዘናሽናል ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሱዳናውያን በጦርነቱ ምክንያት “ከሚታሰበው በላይ ስቃይ” ውስጥ እንደሚገኙ ነው የገለጹት።

ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉባት እና ከ25 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በረሃብና ቸነፈር ውስጥ የሚገኙባትን ሱዳን ቀውስ ለመፍታት ፈጣን እርምጃ ያሻል ብለዋል።

በሰሜን ዳርፉር ዋና ከተማ ኤል ፋሸር ለሳምንታት የዘለቀ ጦርነት እየተካሄደ መሆኑን ያነሱት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር፥ የሱዳን ጦርና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በመላ ሀገሪቱ እያካሄዱት ያለው ጦርነት በፖለቲካዊ ንግግር እንዲቆም ጥረት እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል።

የሱዳን የሲቪል ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጥምረት ሊቀመንበሩ ሃምዶክ ከሰሞኑ በኖርዌይ መዲና ኦስሎ በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ባተኮረው ምክክር ተሳትፈዋል።

ነፃነቷን ከማወጇ አስቀድሞ ከፈረንጆቹ 1955 ጀምሮ ጦርነት የተፈራረቀባት ሱዳን፥ ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿን በእርስ በርስ ጦርነት አጥታለች፤ በዳርፉር የዘር ፍጅትም ከ300 ሺህ በላይ ሱዳናውያን ሕይወታቸው መቀጠፉን የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ ያሳያል።

ካርቱም በየጊዜው በሚቀያየር ሕገመንግሥት እና ወታደራዊ መንግሥት መመራቷ ከጦርነት አባዜ እንዳትወጣ እንዳደረጋትም ነው አብደላ ሃምዶክ ለዘናሽናል የተናገሩት።

ሱዳንን ለ30 ዓመታት የመሩት ኦማር አል በሽር ከሥልጣን እንደተወገዱ ከ2019 እስከ 2021 ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት ሃምዶክ፥ በተፋላሚዎቹ ጄኔራሎች ላይ ጫና ለማሳደርና የሲቪል አስተዳደር እንዲቋቋም እየሠሩ ነው።

በጥቅምት ወር 2023 ባቋቋሙት የሲቪል ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጥምረት (ታቃዱም) ስርም የተለያዩ ሲቪል ተቋማት እና የፖለቲካ ኃይሎችን ለማቀራረብ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።

የመጀመሪያ ስብሰባቸውንም በአዲስ አበባ አድርገው ባለፈው ወርም ከ600 በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት ምክክር ማድረጋቸው ይታወሳል።

የሱዳን ዲያስፖራዎችን እና የሲቪል ተቋማትን እያስተሳሰረ ያለው “ታቃዱም” ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና ጄኔራል ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሚቲ) ልዩነታቸውን በፖለቲካዊ ንግግር እንዲፈቱና ሱዳን ከጦርነት አዙሪት እንድትወጣ የጀመረውን ጥረት ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ እንዲደግፍ ሃምዶክ ጠይቀዋል።

ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር የጀመረው የሱዳን ጄኔራሎች ፍልሚያ በንግግር እንዲቆም ሳዑዲ ዓረቢያ እና አሜሪካ በጂዳ ካደረጉትና በአጭሩ ከተቀጨው ሙከራ ውጭ እስካሁን ተስፋ ሰጪ ንግግር አልተካሄደም።

የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) እና የሱዳን ጎረቤቶች ተፋላሚ ጄኔራሎቹን ፊት ለፊት ለማገናኘት ያደረጉት ሙከራም ሳይሳካ መቅረቱ ይታወቃል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2016 ዓ.ም

Recommended For You