ሰሜን ኮሪያ ያስወነጨፈችው ሚሳይል  አየር ላይ መፈንዳቱ ተገለጸ

ሰሜን ኮሪያ ከምስራቅ ጠረፍ ያስወነጨፈችው ሀይፐርሶኒክ ሚሳይል እንደሆነ የተገመተው መሣሪያ አየር ላይ መፈንዳቱን የደቡብ ኮሪያ ጦር አስታውቋል።

የደቡብ ኮሪያ ጦር አዛዥ እንደተናገሩት፤ ሚሳይሉ የተተኮሰው ከዋና ከተማዋ ፒዮንግያንግ በቅርብ ርቀት ከሚገኝ ቦታ ነው።

የጃፓን መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ሚሳይሉ በ100 ኪሎሜትር ከፍታ ላይ ሲበር እንደነበር እና 200 ኪሎ ሜትር ርቀት እንደሚሸፍን ገልጿል።

የደቡብ ኮሪያ፣ አሜሪካ እና ጃፓን ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚሳይል ማስወንጨፍ ሙከራው በርካታ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ሕጐችን ይጥሳል በሚል አውግዘውታል።

የደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ አየር ኃይሎች በኤፍ-22 እና ኤፍ-35 የጦር አውሮፕላኖች የታገዘ ዓመታዊ የጋራ ልምምድ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።

የደቡብ ኮሪያ ባሕር ኃይል ደቡብ ኮሪያን ከሰሜን ኮሪያ ጋር በሚያዋስነው የማሪታይም ድንበር በተናጠል ልምምድ አድርገዋል። ይህ ልምምድ የተካሄደው ሴዑል የኢንተር ኮሪያ ወታደራዊ ስምምነትን ከሰረዘች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

የአሜሪካ፣ የኢንዶ ፓሲፊክ እዝ የሰሜን ኮሪያን ድርጊት አውግዞ፣ ፒዮንግያንግ ከእንዲህ አይነት ሕጋዊ ያልሆነ እና ሠላም የሚያደፈርስ ተግባሯ እንድትቆጠብ ጥሪ አቅርቧል።

“ይህ ክስተት በአሜሪካ ወታደሮች፣ ግዛት እና አጋሮቿ ላይ ጥቃት ባያደርስም፣ ሁኔታውን መከታተላችንን እንቀጥላለን” ብሏል እዙ ባወጣው መግለጫ።

ሰሜን ኮሪያ ለመጨረሻ ጊዜ ሚሳይል የሞከረችው በፈረንጆች ባለፈው ግንቦት 30 ነበር።

አሜሪካ ከደቡብ ኮሪያ ጋር ለምታደርገው ልምምድ የጦር ጄት ተሸካሚ መርከብ መላኳን ባለፈው ሳምንት የተቃወመችው ሰሜን ኮሪያ በርካታ የማስጠንቀቂያ ሙከራዎችን እንደምታደርግ አስጠንቅቃ ነበር።

የሚሳይል ማስወንጨፍ ሙከራው የተደረገው የኮሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት የተጀመረበት 74ኛ ዓመት ከተከበረ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

ባለፈው ሳምንት የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን እና የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ወታደራዊ ጥቃት በሚሰነዘርባቸው ወቅት አንደኛቸው ለሌላኛቸው ሁሉንም አይነት ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።

ሴዑል፣ ዋሽንግተን እና ቶኪዮ የሁለቱን ሀገራት ወታደራዊ ግንኙት መጠናከር ያወገዙ ሲሆን የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ዩን ሱክ ዩኦል ደግሞ ስምምነት “ኋላቀር” ሲሉ አጣጥተውታል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

 አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2016 ዓ.ም

Recommended For You