የኬንያ ፖሊሶች በዚህ ሳምንት ሀይቲ እንደሚደርሱ አሜሪካ ገለጸች

የሀይቲ ወሮበሎችን ለመዋጋት የተመደቡት የመጀመሪያዎቹ የኬንያ ፖሊሶች በዛሬው እለት ከኬንያ መነሳታቸውን እና በዚህ ሳምንት ውስጥ እንደሚደርሱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

“በተለይ የሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲከወን ከማድረግ አንጻር የሚጨበጥ ለውጥ እናያለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማቴው ሚለር ተናግረዋል።

ወሮበሎቹ የካሪቢያኗን ሀገር ዋና ከተማ ፖርታው ፕሪንስን አብዛኛውን ክፍል በመቆጣጠር ግድያ፣ እገታ እና ጾታዊ ጥቃት እየፈጸሙ ናቸው።

ኬንያ ይህን ለማስቆም የተቋቋመውን ዓለምአቀፍ የበጎ ፈቃደኞች ቡድን ለመምራት ባለፈው አመት በፈረንጆቹ ሐምሌ 2023 ተስማምታለች።

የመላኩ ሂደት የዘገየው በፍርድ ቤት በቀረበው ጥያቄ እና በሀይቲ ያለው ሁኔታ ተባብሶ ባለፈው ሚያዝያ ወር የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አሪል ሄንሪይ ከስልጣን እንዲለቁ በማስገደዱ ምክንያት ነው ተብሏል።

ሮይተርስ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አራት ወታደሮችን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ የጦር መሳሪያዎቻቸው እና የግል መገልገያቸው ተሰብስቦ እሁድ ምሽት አውሮፕላን ላይ መጫኑን ተናግረዋል።

የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ከትናንት በስተያ በመጀመሪያ ዙር ለሚላኩት 400 ወታደሮች ሽኝት እንዳደረጉላቸው ሮይተርስ ዘግቧል።

“ተልእኮው በጣም አስቸኳይ፣ ጠቃሚ እና በዓለምአቀፍ አጋርነት ታሪክ ታሪካዊ ነው” ብለዋል ሩቶ።

አራቱ ወታሮች እንዳሉት ከሆነ ሌሎች 600 ወታደሮች በመጀመሪያው ዙር ይላካሉ። ወታደሮቹ ሀይቲ ከመድረሳቸው በፊት ሌላ ሶስተኛ ሀገር ያርፋሉ ተብሏል።

ከኬንያ በተጨማሪ ጃማይካ፣ ባሀማስ፣ ባርባዶስ፣ ቻድ እና ባንግላንዲሽ በዋናነት በአሜሪካ በጀት በሚንቀሳቀሰው ተልእኮ 2500 ወታደሮችን ለማዋጣት ተስማምተዋል።

የሄንሪን ከስልጣን መልቀቅ ተከትሎ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን በዚህ ወር ቃለ መሀላ የፈጸሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ጋሪ ኮኒል የኬንያን ድጋፍ በበጎ ተቀብለዋል።

“ይህ ብዙ ሀገራት የተሳተፉበት ተልእኮ ሀገሪቱ እንድትረጋጋ እና ወደ ዲሞክራሲ እንድትመለስ እንደሚያስችል የሀይቲ ሕዝብና መንግሥት ተስፋ አድርጓል” ሲሉ ኮኒሌ በኤክስ ገለጻቸው ጽፈዋል።

በሀይቲ ከዚህ በፊት የነበሩት ተልእኮዎች ንጹሀን እንዲገደሉ እና የኮሌራ ወረርሽኝ እንዲከሰት እና ጾታዊ ጥቃት እንዲደርስ ሚና ነበራቸው የሚል ትችት ይቀርብባቸዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You