ደስተኛ የመሆን ምስጢር

የምንፈልጋቸው ነገሮች ቢሳኩም ባይሳኩም፤ ነገሮች በምንፈልገው መንገድ ቢሄዱም ባይሄዱም እንዴት ነው ደስተኛ መሆን የምንችለው? ሁልጊዜ ደስተኛ መሆን፣ ተመሳሳይ የስሜት ሁኔታ ውስጥ መሆን እንዴት ነው መሆን የምንችለው? ደስተኛ ለመሆን እነዚህን አምስት ምስጢሮች ማወቅ ይኖርባችኋል። እነዚህን አምስት ምስጢሮች ካወቃችሁ በርግጠኝነት ህይወታችሁ ላይ የሆነ ነገር ትጨምራላችሁ። ምስጢሮቹን ልታውቋቸው ትችላላችሁ። ነገር ግን አዲስ ነገር ባይሆኑ እንኳን የምታውቋቸው ነገሮች በራሳቸው ህይወታችሁ ላይ አንድ ነገር ይጨምሩላችኋል። የሚያውቁትን ነገር ማስታወስም ጥሩ ነው።

‹‹The code of extraordinary mind›› የተሰኘው መጽሐፍ አንድ የሚገርም ሃሳብ አለው። ‹‹Bending the reality›› ብሎ የሚጠቅሰው አንድ ፅንሰ ሃሳብም አለ። አንዳንዴ የምንፈልጋቸው ነገሮች እየተሳኩ ባሉበት ወቅት ወይም ደስተኛ ስንሆን ነገሮች ይደራረባሉ። ‹‹ደስታ በደስታ፤ እንዴት ነው ሰሞኑን! የሰላምና የጤና ያርግልኝ›› እንላለን። ደግሞ አንዳንዴ መጥፎ ነገሮች ሲገጥሙን ይደራረባሉ። ‹‹ኧረ አምላኬ ምን አድረኩህ፤ ፈተናዎች በዙብኝ፤ ምን ተፈጥሮ ነው›› እንላለን። ደስታ ሲሆን ይከታተላል፤ ሀዘን ሲሆን ይከታተላል።

ለምን ይመስላችኋል? በጣም ደስተኛ ስትሆኑ ደስተኛ መሆናችሁ በራሱ ፈጣሪያችሁን እንድታመሰግኑና መልካም ነገርን እንድታስቡ ስለሚያደርጋችሁ፤ ምን አይነት እድለኛ ነኝ እያላችሁ ደስተኛ ስትሆኑ ሌላ ደስታ ይጨመራል። ስለዚህ እውነታውን ወደ እናንተ ትቀለብሱታላችሁ ይላል መጽሐፉ። ስለዚህ በየቀኑ ደስተኛ ለመሆን የሚረዱ አምስት ምስጢሮች እንሆ….

1ኛ. ዘላለም እንደሚኖር ሥራ፤ ዛሬ እንደሚሞት ተደሰት

ሰውየው ወጥሮ ይሰራል። ቤተሰቦቹን ሊያሳልፍላቸው፤ ጥሩ ነገር እንዲኖራቸው በየቀኑ ወጥቶ ይገባል። ይለፋል፤ ይጥራል። ግን ከእነርሱ ጋር ራት የሚበላበት ጊዜም የለውም። ማታ ሲገባ ደክሞት ነው የሚተኛው። ቤት በጊዜ ከመጣ እንኳን ስራ ቦታ ያልጨረሰውን ስራ እቤቱ ቢሰራ ነው እንጂ ለቤተሰቦቹ ጊዜ ለመስጠት አይደለም። ይነግራቸዋል፤ ‹‹ትንሽ ጊዜ ታገሱ፤ ጥሩ ገቢ ሲኖረን ጥሩ ጊዜ እናሳልፋለን። ራት ብቻ መብላት አይደለም ጥሩ ጊዜ ይኖረናል›› ይላል። ጊዜያት ያልፋሉ።

ግን ሰውዬው ወጥሮ ስለሚሰራ ጥሩ ገቢ ማግኘት ጀመረ። ከዛ ነገራቸው ‹‹አሁን ከእናንተ ጋር ለማሳለፍ ጥሩ ጊዜ ነው፤ ግን አንድ ነገር ብቻ ይሳካ። እሱም ቤት ልግዛ፤ ቤት ከገዛን ጥሩ ኑሮ ስለሆነ ከእናንተ ጋር ጥሩ ጊዜ አሳልፋለሁ›› ይላቸዋል። ከዛ ሰውዬው በጣም ወጥሮ ይሰራል። ጊዜ ለቤተሰቡ አይሰጥም እንጂ ስራ ላይ ጎበዝ ነው። ከዛ ተሳካለት። አመታት ሄዱ። ቤቱ ተገዛ። ቤተሰቡ አለፈለት። ጥሩ ኑሮ መኖር ጀመሩ።

ከዛ ሰውዬው ‹‹አሁን ከእናንተ ጋር የማሳልፍበት ጥሩ ጊዜ ላይ ነው ያለሁት፤ ግን አንድ ነገር ብቻ ይቀራል። እርሱም የምናስተዳድረው ቢዝነስ ያስፈልገናል። ቁጭ ብለን መብላት አለብን። ገንዘባችን ለእኛ መስራት አለበት። ሌላ ገንዘብ ይዞ መምጣት አለበት። እኛ ግን ፈታ እንላለን። ትንሽ ጊዜ ስጡኝ›› ይላል። አመታት ተቆጠሩ። ሰውዬው በስራው ጎበዝ ነውና ቢዝነሱን ቀጥ አድርጎ አቆመው። አመታት ግን እየሄዱ ነው። ቢዝነሱ ጥሩ ሆነለት። ከዛ እርሱን የሚተካ ማኔጀር ቀጠረ። ‹‹ከዚህ በኋላ እኔ የዚህ ቢዝነስ ካምፓኒ የቦርድ አባል ነኝ። አልፎ አልፎ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ለማወቅ ብቻ ነው የምመጣው። ከቤተሰቦቼ ጋር አሳልፋለሁ›› አለ።

ሁሉን ነገር ለአዲሱ ማናጀር አስረከበ። ቤቱ ሄደ። ማታ ላይ ነገራቸው። ‹‹ዛሬ የቢዝነስ ካምፓኒዬን ለሌላ ሰው አስተላልፊያለሁ። የእኔ ስራ አልፎ አልፎ ብቻ እየሄዱ ማረጋገጥ ነው። ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋር ነው የማሳልፈው። ጥሩ ጊዜ ይኖረናል። በደንብ እንከባከባችኋለሁ›› አለ። ቤተሰቡ ተደሰተ። ከዛ ሁሉም ወደ አልጋቸው ገቡ። ጠዋት ግን አልተነሳም ይሄ ሰው። በዛው አሸልቧል። አስቡት ምን ያህል እንደሚያንገበግብ። ለፍቶ፣ ጥሮ፣ ግሮ ሳይበላው ሞተ። ከቤተሰቡ ጋር ሳይደሰት። ለቤተሰቦቹ ጊዜ ሳይሰጣቸው ሞተ።

ለዛ ነው ይህን ምስጢር ማወቅ ያለባችሁ። ዘላለም እንደምትኖር ወጥረህ ስራ፤ ግን ዛሬ እንደሚሞት ሰው ተደሰት። እንዴ! የሚጠበቅብህን እኮ ከሰራህ ለምን አትደሰትም? ተደሰት! የሆነ ነገር አድርግ። ከቤተሰቦችህና በዙሪያ ካሉ ሰዎች ጋር ጊዜህን አሳልፍ። ለምን እስከ ጥግ ድረስ እንደማሽን ትሰራለህ። መስራት የሚጠበቅብህን ከሰራህ መዝናናትማ ግድ ነው። ያኔ ደስተኛ ትሆናለህ። ሁልጊዜ ‹‹እኔ እኮ እንደዚህ ነው የምለፋው›› አትልም። ደስተኛ ትሆናለህ። ለምን? የሚጠበቅብህን ትሰራለህ፤ በጊዜህ ደግሞ ትዝናናለህ። ይህ በየቀኑ ለመደሰት የመጀመሪያው ምስጢር ነው።

2ኛ. ደስታን አሳደህ አታገኘውም

ደስታ ከባድ ምስጠር ነው። ደስታ ራሱ ያሳድድሃል እንጂ አንተ ማሳደድ የለብህም። ያለበለዚያ ንፋስ ነው የምትከተለው። ምን መሰለህ ለመደሰት የሆነ ቅድመ ሁኔታ የምታስቀምጥ ከሆነ አትደሰትም። ‹‹ይሄን ሳገኝ እደሰታለሁ›› ትላለህ። ታገኘዋለህ እኮ! ከዛ ትደሰታለህ። ደስታው ግን ጊዜያዊ ይሆናል። በየቀኑ ለመደሰት ጥሩ ምክንያት አይኖርህም። ወይ በየቀኑ የምትፈልገውን ሁሉ ማግኘት አለብህ። እንዲህ ለመሆን ደግሞ የምትኖርባት ዓለም አትፈቅድልህም።

ስለዚህ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ የለብህም። ወይም ለመደሰት ይህን ሳገኝ ነው ማለት የለብህም። ሰውዬው ‹‹ደስተኛ የምሆነው የሆነ ነገር ሳገኝ ነው፤ ምን ይሆን እርሱ?›› እያለ ሁሌ ይፈልጋል። እናም በዙሪያው ያሉ ሰዎችን ሁሉ ረሳቸው። እርሱ ለመደሰት የሆነ ምክንያት እየፈለገ ነው። በቃ! የሆነ የሚያስደስተውን ነገር ለማወቅ እየፈለገ ነው። እድሜው አለፈ፤ ገፋ። ሰዎች ሸሹት። ምክንያቱም ሰዎችን አይቀርብም። እርሱ የሚያስደስተኝ ሌላ ነገር ነው ብሎ እያሳደደ ነው። ስለዚህ ሰዎች ከእርሱ ጋር መሆን አያስደስታቸውም። ሸሹት። ብቻውን ቀረ።

ሰማንያ አመቱ ላይ ግን ተቀየረ ሰውዬው። ሰዎች ሁሉ ምን አይነት ደስተኛ ሰው ሆነ እያሉ ማውራት ጀመሩ። ከዛ እራሳችን ሄደን ለምን አንጠይቀውም፤ ምን ለወጠው ብለው ሄዱ። “ምንድን ነው ደስተኛ ያደረገህ?” ብለው ጠየቁት። ሰውዬው መለሰ ‹‹እድሜ ልኬን ደስታን ሳሳድደው ነበር። አሁን ማሳደዱን እርግፍ አድርጌ ተውኩኝ። በቃ፣ ቁጭ ብዬ ዛሬን ማጣጣም፤ ዛሬን መደሰት ጀመርኩ። በቃ! ዛሬ ህይወቴን መኖርና ማጣጣም ስጀምር ደስታ ራሱ መጣ። ደስተኛ ሆንኩኝ›› አለ። አንተም ደስታን አሳደህ አትይዘውም፤ ካሳደድከው ንፋስን እያሯሯጥክ ነው። ስለዚህ አንተ ማድረግ ያለብህ አሁንን መኖር፣ አሁንን ማጣጣም ነው፤ ልክ እንደ ሽማግሌው፡፡

3ኛ. እቅድ ይኑርህ

አንዳንድ ጊዜ ቀኑ ዝም ብሎ ስለሚያልፍ ሊሆን ይችላል ደስተኛ ያልሆንከው። ለምንድን ነው በየቀኑ ደስተኛ ያልሆንኩት ስንል ማታ ላይ ምንም የማይረባ ነገር እያደረኩ እኮ ነው የሚሆነው ልንል እንችላለን። ስለዚህ እቅድ እናስቀምጥ። ወይ የምንኖርለት አላማ ይኑረን። በነገራችን ላይ ዶክተር መሆን እቅድ አይደለም። ዶክተር መሆን ግብ ነው። ግን የህይወት አላማ ነው የሚያስፈልገን። ለምሳሌ ሰዎችን ማገልገል። ይህ ማለት ለምሳሌ ዶክተር ብትሆንም ባትሆንም ሰዎችን አገልግለህ አትረካም። ገደብ የለውም። ስዚህ ሁልጊዜ የምትኖርለት አላማ ይኖራል።

አለበለዚያ ግን አንድ ነገር ካሳካህ በኋላ ነገሮች አሰልቺ ይሆናሉ። በቃ ዝም ብሎ ቀኑ የሚያልፍ ይመስልሃል። ስለዚህ እቅድ ታስቀምጣለህ። እቅድህ ላይ ግን ሁለት ነገሮችን ማካተት አለብህ። እነዚህን አምስት ኳሶች መርሳት የለብህም። ከነዚህ አምስት ኳሶች ውስጥ ሶስቱ ከፕላስቲክ የተሰሩ ናቸው። ቢወድቁ ነጥረው ይነሳሉ። ሁለቱ ጎኖች ከመስታወት ነው የተሰሩት። ከወደቁ ይሰበራሉ። ስለዚህ እቅድህ እነዚህ ሁለቱን ማጣጣም አለበት።

ሶስቱ ፕላስቲክ ኳሶች ማለት ስራህ፣ ትምህርትህ፣ ጓደኞችህ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህን ካበላሸሃቸው የሆነ ሰአት ማስተካከልህ አይቀርም። በስራህ ወይም በገንዘብህ ብትከስር መልሰህ ታገኘዋለህ። አንተ ብቻ እድሜና ጊዜ ይኑርህ እንጂ! ትምህርትህ ቢበላሽብህ ይስተካከላሉ። ከጓደኞችህ ጋር ብትጣላ ይቅር ትባባላለህ። በህይወትህ ውስጥ ደስተኛ እንዲያደርጉህ ግን ሁለቱ መስታወቶች ላይ ተጠንቀቅ። እነርሱን ስታቅድ በተለይ ቅድሚያ ስጣቸው። ሁለቱ ወድቀው የሚከሰከሱት ኳሶች አንደኛው ቤተሰቦችህ ናቸው፡፡

ቤተሰቦችህን ካጣሃቸው አታገኛቸውም። ስለዚህ ስታቅድ ከእነርሱ ጋርም አቅድ። ሁለተኛው የሚሰበረው ኳስ ጤናህ ነው። ጤናህን ካጣኸው መልሰህ ላታገኘው ትችላለህ። ታክመህ የማትድነው በሽታ ሊይዝህ ይችላል። ስለዚህ ለጤናህም ቅድሚያ ስጥ። ለደስታችንም ለስራችንም እኩልና ሚዛናዊ የሚያደርግ እቅድ ያስፈልገናል። ለምሳሌ ስራችን ከበዛ ባዶነት ይሰማናል። ‹‹በቃ፣ እኔ ዝምብዬ እንደማሽን ነው የምለፋው፤ ምንድን ነው የማሳካው ታዲያ፣ ምንድን ነው የደስታዬ ሚስጥር እንላለን። መደሰት ካበዛን ደግሞ መጨረሻ ላይ ህይወታችን ትርጉም አልባ ይሆናል። ከዚህ አንፃር እቅዳችን መመጣጠን አለበት።

4ኛ. ለመደሰት ምክንያቶች ፈልግ

አንዳንዴ ከመሬት ተነስተህ ላትደሰት ትችላለህ። አንዳንዴ ደግሞ ያለህበት ሁኔታ ትንሽ ሊደብህር ይችላል። አሁንን ማጣጣም ሲባል ታዲያ ማጣጣም የምትችልበት እድል ላይኖርህ ይችላል። ስለዚህ ምክንያቶችን ፈልግ።

ሰዎቹ እስር ቤት ናቸው። አንደኛው በጣም ደስ ብሎታል። ሌላኛው ደግሞ ከፍቶታል። የከፋው እስረኛ የተደሰተውን ‹‹ለምድን ነው ደስተኛ የሆንከው›› ይለዋል። ደስተኛው መለሰ ‹‹እንዴ፣ ያንተ አለመደስት ሲገርመኝ እኔን ትጠይቀኛለህ እንዴ? እኔ በጣም ደስተኛ ነኝ። አንተ ለምድንነው ያልተደሰትከው?›› አለው። ‹‹እስር ቤት መሆን ምኑ ያስደስታል? እኔ እኮ ባለፈው ሳምን ሪዞርት ውስጥ እየተዝናናሁ ነበር። አሁን እዚህ እስር ቤት ውስጥ እንዴት ልደሰት?›› አለው። ‹‹አሃ! ለዛ ነው ለካ አንተማ ልክ ነህ። እንደዛ ብትል እኔ ደግሞ ባለፈው የነበርኩበት እስር ቤት ስቃዩ ከባድ ነበር። አሁን ለእኔ ይሄኛው እስር ቤት እንደሪዞርት ነው እየተዝናናሁ ነው›› አለው፡፡

አያችሁ! አንዳንድ ጊዜ ምክንያቶች ስናገኝ እንደሰታለን። ያ ሰውዬ ምን ብሎ ነው መደሰት ያለበት ማለት ነው? ባለፈው ሳምንት ሪዞርት ነበርኩ፤ አሁን እስር ቤት ነኝ። ብሎ አይደሰትም። ማለት ያለበት ቢያንስ በህይወት ተርፌያለሁ፣ እፈታለሁ፤ ብሎ ምክንያት ቢያገኝ ወይም ከእርሱ የባሰ ሁኔታን ቢያስብ ይደሰታል።

አንዳንድ ጊዜ ያለንበት ሁኔታ ታላላቆቻችንንና ከእኛ የተሻሉትን ስናይ ደስታችን ይቀንሳል፤ ያንስብናል። ግን ትናንትናችንን ብናይስ? ምንም እኮ አልበረኝም ትናንት፣ ዛሬ እዚህ ደርሻለሁ፣ ዛሬ እኮ እንዲህ አሳክቻለሁ፣ ፈጣሪ ይመስገን ጤና አለኝ፣ የሆነች ነገር ብለፋ አሳካለሁ ብለን ምክንያት ፈልገን መደሰት ነው። በነገራችን ላይ ትኩረታችን ድክመታችን ላይ ከሆነ ይባስ እንጎዳለን። እየሰፋብን ይመጣል። ስለዚህ እሱ ላይ ማተኮር የለብህም።

5ኛ. ሂደቱን ውደደው

አንዳንድ ጊዜ የሆነ ነገር ለማሳካት ስትፈልግ ያንን ነገር ካላሳካሁ አልደሰትም ካልክ ያ ነገር ቢሳካም ደስታህ ሙሉ አይሆንም። ለምሳሌ ከአዲስ አበባ አዳማ እየሄድክ መንገዱን ካላጣጣምከው አዳማ ስትገባ ብዙም ስሜት አይሰጥህም። በሌላ በኩል በወር 30 ብር መቆጠብ የፈለገ ሰው እኔ ደስተኛ የምሆነው 30 ብሩን ስቆጥብ ነው ካለ በቃ! ሰላሳ ብሩን እስኪያገኝ ጭንቀት ነው። እያንዳንዱ ቀን እንዴት ነው ሰላሳ ብር ሞልቶልኝ ወሩ መጨረሻ ላይ እንዴት ነው ሰላሳ ብር የሚሞላው ነው የሚለው።

ነገር ግን፣ ይህ ሰው በቀን አንድ ብር መቆጠቡ ላይ ትኩረት ቢያደርግና አንድ ብር ቆጥቤያለሁ ብሎ ቢደሰት ወሩ መጨረሻ ላይ ሰላሳ ብሩን ማግኘቱ አይቀርም። አየህ፣ ሳታስበው ደስ እያለህ መጨረሻ ላይ ደግሞ የምትፈልገውን ታሳካለህ። በጣም ስትደሰት ነገሮች ወደ አንተ አቅጣጫ ማድላት ይጀምራሉ። እውነታው ይገለበጣል። ጠረጴዛው ወዳንተ ይሆናል። ስለዚህ ሂደቱን ውደደው።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You