ውበትና ጽዳትን ከአዲስ የሥራ ባህል ጋር ያስተሳሰረው የኮሪደር ልማት

በመዲናዋ በቅርቡ የግንባታ ሥራው ተጀምሮ በፍጥነት እየተጠናቀቀ ለአገልግሎት ክፍት እየሆነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ለመዲናዋ ልዩ ውበትን እያላበሳት ነው። በተለይ በምሽት የከተማዋ ውበት እውነትም አዲስ የሚያሰኝ አዲስ ገፅታን አላብሷታል። አዲስ የሥራ ባህልን በሳምንት 24 ሰዓት መሥራትን ጭምር በስፋት እያስተዋወቀ ይገኛል።

በኮሪደር ልማቱ ቀደም ሲል የነበሩ የሸረሪት ድር መሰል ለእይታ የማይመቹ በርካታ የተደራረቡ የኤሌክትሪክ እና የስልክ ገመዶች አሁን ላይ በኮሪደር ልማቱ አይታዩም። ይልቁንም ስማርት በሆነ መንገድ ለቀጣይ ታሳቢ ተደርገው በመሬት ውስጥ የተገጠሙ የቴሌ እና የኤሌክትሪክ ገመዶችም የኮሪደር ልማቱ አካል ሆነዋል። ዜጎችም በነፃነት በእግረኛ መንገዶች እንዲንቀሳቀሱና የትራንስፖርት አገልግሎቱ ከጭንቅንቅ የወጣ እንዲሆን የፈጠረው መደላድልም ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። የመንገድ ዳር መብራቶች እና የስክሪን መልዕክት ማስተላለፊያ ልዩ ፖሎች ውበቱን በጠበቀ መልኩ በዘመናዊ መንገድ ተገጥመው ላስተዋላቸው አግራሞትን ይፈጥራሉ።

የብስክሌት መንገዶች እና የእግረኛ መንገዶችም ሰፋፊ መንገዶች ቀደም ሲል በስፋት በመዲናዋ የሚከሰቱ የትራፊክ መጨናነቆችን እና አደጋዎችን እንደሚቀንሱ ታሳቢ ሆነው እየተሰሩ ናቸው። እግረኞች የተሽከርካሪ መንገዶችን ይሻሙ የነበረበትን ሁኔታ ለማስቀረት በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት፣ ሲያስፈልጋቸው እረፍት የሚያደርጉባቸው መቀመጫዎች፣ መንፈስን የሚያድሱ የመንገድ ላይ አረንጓዴ እፅዋት እና ዛፎች እንዲሁም በልዩ መልኩ የተገነቡ የመፀዳጃ ቤቶች የኮሪደር ልማቱ አካል ሆነው ተሰርተዋል፤ እየተሰሩም ይገኛሉ። የአረንጓዴ ስፍራዎቹም የሰው ልጅ አእምሮን በማደስ ለሥራ መነሳሳትን ስለሚፈጥሩ ሰዎች ይህንን ተመልክተው ወደ ሥራ ሲገቡ ትልቅ የሥራ መነቃቃትን የሚፈጥርና ከሥራ ገበታ ሲወጡም መንፈስን የሚያድሱ በመሆናቸው በርካቶች ልማቱን ሲጎበኙ ይስተዋላሉ።

የከተማዋን የኮሪደር ልማት ሲጎበኙ ያገኘናቸው እና ከሀዋሳ መምጣታቸውን የተናገሩት አቶ ፍቅሬ ሀንዶሮ በበኩላቸው፤ አዲስ አበባ የዲፕሎማት መቀመጫ ከተማ መሆኗን አንስተው፤ ከሌሎች ከተሞች አኳያ ደረጃዋን በማይመጥን ሁኔታ ላይ የቆየች መሆኗን አስታውሰው፤ አሁን ግን ደረጃዋን በሚመጥን መልኩ እየተገነባች መሆኑን አይቻለሁ፤ በከተማዋ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ አበረታችና ለመጪው ትውልድ የሚሆን ሥራ መሆኑን ይገልጻሉ። የኮሪደር ልማቱ በፍጥነት እየተከናወን መሆኑን ለግለሰቦች ጭምር የጀመሩትን በፍጥነት እናጠናቅቅ የሚለው እምነት እንዲኖራቸው የሚያደርግ መሆኑን ያመላክታሉ።

እሳቸው እንደሚሉት፤ አደጉ የተባሉ ሀገራት አብዛኛው 18 ሰዓት በላይ የሰሩ ናቸው። ቀን እና ሌሊት፤ ሠራተኛውም ከአንድ ሁለት ቦታዎች ላይ ይሰራሉ፤ በዚያም ለውጥ ያገኛሉ። እራሳቸውን እና አካባቢያቸውንም ይለውጣሉ፤ ይህ የሥራ ባህል እንዲሁ መቀጠል አለበት። በተለይ በክልሎች እንደዚህ አይነት ሥራ ቢለመድ እና ሥራዎችን በፍጥነት ጀምሮ ለአገልግሎት ማብቃት ቢቻል ሀገርን መለወጥ ይቻላል፤ ኅብረተሰቡም ለውጥ ሲያይ ተባባሪ ይሆናል።

ሥራዎችን በዚህ መልኩ በተግባር ማሳየት ተገቢ ነው። ይህንን መገናኛ ብዙኃን በመጠቀም እየታዩ ያሉትን ለውጦች፣ የተጀመሩ ሥራዎች በፍጥነት እየተጠናቀቁ መሆኑን ግንዛቤ መፍጠር ይገባል ሲሉም ሃሳባቸውን ሰጥተውናል። ፒያሳ አካባቢ ሊፈረስ ነው ሲባል አካባቢውን ማየታቸውን አስታውሰው፤ ተሰርቶ በዚህ ደረጃ ሲታይ ሕዝቡም እርካታ እያገኘ እንደሚሄድ ገልጸዋል። ሌላው አካል ደግሞ የተሠራውን ሥራ እየተመለከተ በርቱ ማለት እንደሚጠበቅበት ጠቅሰው፤ የሁሉንም ቅንጅት እና የሁሉንም ትብብር የሚጠይቅ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

አቶ ፍቅሬ ሀንዶሮ ፒያሳ አካባቢም የሚያስደንቅ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ሲያስረዱ፤ የዓድዋ መታሰቢያ አካባቢ ተዘዋውረው ማየታቸውን ጠቁመው፤ በአፍሪካ ደረጃ ለኢትዮጵያ ትልቅ ቅርስ፣ ትልቅ እሴት ዓድዋ ብለን ለሌሎችም በኩራት ለመናገር የሚያስችል ሙዚየም ተሠርቷል። ዓድዋ አካባቢ ሕፃን ትልቅ፣ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ብዙ ጎብኚዎች እየታዩ ናቸው። ይሄ በራሱ ውጤት የሚያሳይ ነው። የተደበቁ የታሪኮቻችን ዳግም ወደ ገቢ ምንጭነት የተለወጡ መሆኑ አስደሳች ነው። በተለይም ቀደም ሲል ምንም ጥቅም ላይ ሳይውሉ የቆዩ ወደተሻለ አገልግሎት የገቡበት ሁኔታ መኖሩን በመጥቀስ አድንቀዋል። “ሰባ ደረጃ አካባቢ ያለውን ሚዲያ ላይ ሳይ በዓይን ለማየት ናፍቄ ነበር። አሁንም ገና እየተሰራ ያለው ሥራ የሚገርም ነው” በማለት ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

አያይዘውም ቦሌ አካባቢ እየተሰራ ያለውን የኮሪደር ልማት ሥራ መጎብኘት እንደቻሉ ገልጸው፤ አካባቢው እየሰፋ እየለማ እና እያማረ፣ ውበቱን እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። ቦሌ የውጭ ዜጎች ባለሀብቶች፣ በውጭ ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ መግቢያ ስለሆነም ቅድሚያ ከተሰጣቸው በጣም እያማረ ግራ ቀኝ ሰው እያየ ከተማዋን እያደነቁ የሚገቡበት ከተማዋ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ማዕከልም እየሆነች መምጣቷ የግድ ነው ብለዋል።

አዲስ አበባ አሁን ላይ በትክክል የአፍሪካ፣ የዓለም፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከተማ ነች ያሉት አቶ ፍቅሬ፤ በእድሜያቸው የዚህ ዓይነት ሥራ ሲሠራ ማየት በመቻላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ይናገራሉ። የተጠናቀቁ ሥራዎች በቴሌቪዥን ሲታይ የሲንጋፖር ነው እንጂ ይሄ አዲስ አበባ አይደለም የሚል ክርክሮችን ሀዋሳ ሆነው መስማታቸውንም ያስታውሳሉ። ለውጥ ምቾት ባይኖረውም እንኳን የግድ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ውብ እና የተሻለ አገልግሎት የምትሰጥ ከተማን ለማስረከብ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ከክልል ከተሞችም ከየትኛውም ጫፍ ወደ መዲናዋ በመምጣት ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ለማስፋፋት ሙከራዎች እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ ወደፊት ሕዝቡ በከተሞች ለመንቀሳቀስ እንዳይቸገር እና የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘትም ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥርለት በመሆኑ የኮሪደር ሥራው ቀጣይነት ያለው መሆን እንዳለበት አመላክተዋል። አሁን ላይ በተለይ በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማቱ በተጠናቀቀባቸው አካባቢዎች በእግርም ሆነ በመኪና ወደ ተፈለገው ቦታ በፍጥነት ደርሶ ለመመለስ የሚያስችል ብርሃን እየበራ ነው ይላሉ። ያለአገልግሎት ጫካ ሆነው ዓመታትን ያስቆጠሩ ቦታዎች አሁን ላይ በሌላ ከተማ እንደሚታየው አይነት ወደ ጥቅም እየተለወጡ ይገኛሉ። በተለይ መጪው ትውልድ ሳይሸማቀቅ ሀገሬ ከተማዬ የሚልበት ከተማ እየመጣ ስለመሆኑም አመላክተዋል።

በሜክሲኮ አካባቢ ወደ ሳር ቤት እና ወሎ ሰፈር መንገድ ላይ ያለውን የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴ ስንቃኝ ያገኘናቸው አቶ አስጨናቂ ወሰኑ፤ የኮሪደር ልማቱ በመዲናዋ የፈጠረውን 24 ሰዓት የመሥራት አዲስ የሥራ ባህል መፈጠሩን ያደንቃሉ። በዋናነትም በኮሪደር ልማት ሥራው ቀደም ሲል ከተለመደው አካሄድ በተለየ ከፍተኛ ቅንጅት የሚታይበት መሆኑን መታዘባቸውንም ገልጸዋል። ቅንጅቱም ቴሌ፣ መንገድ፣ መብራት፣ ውሃ አንድ ላይ የሚቀመጡበት ቦታ አልነበራቸውም፤ አሁን ግን የየራሳቸው ዲዛይን ያላቸው በመሆኑ በዚያ መሠረት ደረጃቸውን ጠብቀው የተቀመጡ መሆኑን ገልጸዋል። የኮሪደር ልማቱ ሥራ ፕሮጀክቶች የሚጠናቀቁበት ትልቅ የሥራ ባህል የታየበት እና ትልልቅ ፕሮጀክቶች 24 ሰዓት ተሰርተው በፍጥነት የሚጠናቀቁበት እንደሆነም ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል። ሌሊት መሥራት የትራፊክ መጨናነቅም የማይኖር በመሆኑ በተሻለ ፍጥነት የተቀላጠፈ የሥራ እንቅስቃሴ ለማድረስ የሚያስችል መሆኑ ልምድ የተወሰደበት እንደሆነም ተናግረዋል።

አቶ አስጨናቂ ወሰኑ በኮሪደር ልማቱ ከሜክሲኮ ከሳርቤት እስከ ወሎ ሰፈር ባለው የቴሌኮም መስመር ሥራው ላይ አስተባባሪ መሆናቸውን ገልጸዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ቀደም ሲል የነበረው እና አሁን ያለው ሲነፃፀር ትልቅ ለውጥ የታየበት ነው። የሸረሪት ድር የመሰሉ የኤሌክትሪክ እና የቴሌኮም ገመዶች አሁን ፀድተዋል። ክልል ከተሞችም ከዚህ ተሞክሮ ወስደው የሚሰሩበትን ሁኔታ ተመልክተዋል። አሁን በተከናወነው የቴሌኮም ፋሲሊቲ ለሚቀጥሉት 20 እና 30 ዓመታት የሚያገለግሉ የመሬት ውስጥ ኬብሎች ገብተዋል። ቀደም ሲል በጣም የተዘበራረቁ የቴሌኮም ዋይሮች የነበሩ መሆኑን አስታውሰው፤ ከአሁን በኋላ የመሠረተ ልማት ሥራዎች በተለመደው መንገድ እንዳይሠራ ስምምነት አለ ብለዋል።

እንዲሁም የሲሲ ቲቪ ካሜራ ሲስተሞች፣ ለመንገድ መብራት የሚሆኑ የተዘረጉ ስማርት ፖሎች አሉ። ስማርት ፖሉ ላይ ስክሪኖችን ዲስፕሌይ ለማድረግ፣ ካሜራ ማድረግ የሚያስችሉ ናቸው። ለወደ ፊትም የገመድ አልባ አገልግሎቶችን በአካባቢው በእግር ለሚንቀሳቀሱ ሰዎችም እግረ መንገዳቸውን አገልግሎቶች የሚያገኙባቸው የዋይኤፍአይ አገልግሎቶችን የሚጠቀሙባቸውን፣ ቻርጀሮችን ጭምር የሚያካትቱ ናቸው። በኮሪደር ልማቱ የሚታዩ ስማርት ፖሎች እና የተለያዩ አዳዲስ አገልግሎቶች በኢኮኖሚያቸው በተሻሉ ሀገራት የሚታዩ ዓይነት ናቸው ሲሉም አቶ አስጨናቂ ተናግረዋል።

እንደአቶ አስጨናቂ ማብራሪያ፤ በኮሪደር ልማቱ ተግባራዊ እየሆነ ያለው ብልህ የትራንስፖርት ሥርዓት በርካታ ነገሮች ያካተተ ነው። መረጃ ይሰበስባል ያገናዝባል መፍትሔም ለመስጠት የሚጠቅም ነው። በተለይ ከዳታ ከተሰበሰበ በኋላም በየመንገዶቹ ላይ ያሉት በካሜራ ይታገዛል፣ በዳታም ያለ ነው። በመሆኑም በዚህ መልኩ ለመቆጣጠር ጭምር የሚያስችል ነው። ከጂፒኤስ ጋር የተገናኘ በመሆኑም በየትኛውም አቅጣጫ መሄድ እንደሚፈልጉም ያካተተ ነው። እንዲሁም ለትራፊክ ማኔጅመንት የትራፊክ ትንተና ይሰራል። በመሆኑም በአንድ መንገድ ላይ በሰዓት ምን ያህል ተሽከርካሪዎች ፍሰት እንደሚያደርጉ የሚሰላበት ነው። የት ቦታ ላይ ትራንስፖርት የተጨናነቀ መሆኑን በመመልከትም በየአካባቢው ወዲያው ማስተካከያ ማድረግ የሚያስችል ነው።

አቶ አስጨናቂ እንደተናገሩት፤ የኮሪደር ልማቱ ከሚሰጠው አበርክቶ መካከል የእግረኛ መንገዱን ማስፋት ነው። ቀደም ሲል በቂ የእግረኛ መንቀሳቀሻ ቦታ ያልነበረ በመሆኑ ብዙ ጊዜ ከተሽከርካሪ ጋር እየተጋፉ የመሄድ ሁኔታ ነበር። ከዚህ አኳያ ኮሪደር ልማቱ ላይ የተሰራው የእግረኛ መንገድ ትልቅ ጠቀሜታ አለው። እንዲሁም ቀደም ሲል ብስክሌት ከመኪና ጋር ተጋፍቶ ይሄድ ነበር። በመሆኑም ብስክሌት መጠቀም የሚችል ሰው አሁን ላይ መኪና መያዝ የማያስፈልግበት ሁኔታ እየተፈጠረለት ነው። በፍጥነት መድረስም እንዲሁም ጭንቅንቅ ሳይኖር ከመኪና ጋር መጋፋት ሳያስፈልግ ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ነው። ቀደም ሲል በተመሳሳይ በእግር ለመንቀሳቀስ ቢፈለግ ደግሞ እረፍት ለማድረግ ከተፈለገ የሚታረፍባቸው ቦታዎች በበቂ አልነበሩም። አሁን ግን በነፃነት ለመንቀሳቀስ እና ሲያስፈልግ እረፍት ለማድረግ አደጋ ሳይበዛ መጨናነቅ ሳይኖር ለመንቀሳቀስ የሚስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ከመንገዱ አኳያም በጣም ጠባብ የነበሩ እና ተሽከርካሪዎች ተጨናንቀው የሚንቀሳቀሱባቸው መንገዶች የሰፉ እና የተሽከርካሪ ማቆሚያ ተርሚናሎችም በአግባቡ የተከናወነበት በመሆኑ የተሻለ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል። አንድ ከተማ ሊያሟላ የሚገባውን ደረጃ በማሟላት የተሻለ ሥራ የተሠራበት እንደሆነም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሜክሲኮ ሳር ቤት የኮሪደር ልማት መጠናቀቁን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት እንደተናገሩት፤ መሠረተ ልማት ማጎልበት፣ የሥራ ባህል እና ታታሪነት፣ የእግረኛ መንገዶች፣ በቂ የተሽከርካሪ መንገዶች ለከተማ እድገት ወሳኝ ናቸው። ያረጁ እና የተጎዱ የከተሞቻችንን ክፍሎች ማስወገድ ለትውልድ የተሻለ ከባቢን እና መፃዒ እድልን ለመተለም አስፈላጊ እርምጃ ነው። ከተጎዱ እና የጤና ጠንቅ በሆነ ከባቢ መኖርን ልንለማመደው አይገባም። የከተማችን የእድገት መንገድ ገና መጀመሩ እንደመሆኑ የለውጡን እድገት ቀጣይ ማድረግ ቁልፍ ነው። በጋራ ጥረታችን የተሻለ ነገን እናሳካለን ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከሜክሲኮ እስከ ሳርቤት ያለው የኮሪደር ልማት በገመገሙበት ወቅት እንደገለጹት፤ ትልቅ የመፈጸም ብቃት የታየበት፣ ለየት ያለ የሥራ ባህል የተተገበረበት፣ ትብብር እና የመሠረተ ልማት ቅንጅት የተሻሻለበት፣ በርካታ በከተማችን ውስጥ ያልነበሩ አዳዲስ የመሠረተ ልማት አገልግሎትና ስታንዳርዶችን በዓይነት፣ በጥራት እና በውበት ለከተማችን ያስተዋወቅንበት ለከተማችንና ለሀገራችን ትልቅ ብስራት ነው ብለዋል። የከተማዋን ስታንዳርድ ለማስጠበቅ እና ለእግረኛ መተላለፊያነት እንዲውል ሕንፃ በማፍረስ እና በተሰጠው ስታንዳርድ መሠረት እድሳት ላደረጉ ተቋማት፣ የቤትና ሕንፃ ባለቤቶች እንዲሁም በትብብር ለተሳተፉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል። ይህንን እና ሌሎቹንም ኮሪደሮች በቀሪ ጊዜያት ውስጥ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት እንደሚውሉም አመላክተዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You