ታዳሽ ኃይልን የመጠቀም ጉዞ

የምድራችን ሙቀት መጠን ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። ለዚህም ዋናው ምክንያት የሰው ልጅ ሲሆን፤ በሰው ልጆች ድርጊት የአየር ንብረት ለውጥ መላውን ዓለም ሕይወት እየቀየረው መሆኑ ይታመናል። ታዲያ በአሁን ወቅት በፍጥነት እየተለዋወጠ ያለው የአየር ንብረት በሰው ልጆች ምክንያት እንደሆነ ሁሉ መፍትሔዎቹም በሰው ልጆች መዳፍ ውስጥ ስለመሆናቸው ዕሙን ነው።

የሰው ልጅ በተለያዩ ምክንያት ለአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየሆነ ነው። ለአብነትም የሰው ልጅ ነዳጅ ይጠቀማል፤ ጋዝና ከሰል ያቀጣጥላል፤ በድንጋይ ከሰልና በጋዝ ለቤቱ ብርሃን ያጎናፅፋል፤ ፋብሪካ ያንቀሳቅሳል፤ መጓጓዣ ያበጃል። እነዚህ ኃይል አመንጪ ንጥሮች በሙሉ የሚለቁት ጭስ ደግሞ ግሪንሃውስ ጋዝ ይባላል። አብዛኛው ክፍሉ ካርቦንዳይ ኦክሳይድ [CO2] ነው። ይህ ጋዝ ከፀሐይ የሚመጣውን ሙቀት አምቆ የፕላኔታችንን የሙቀት መጠን እንዲጨምር ያደርጋል።

መረጃዎች እንዳሚያመላክቱት፤ ዓለም በ19ኛው ክፍለ ዘመን ከነበረችበት የሙቀት መጠን በአሁን ወቅት አንድ ነጥብ ሁለት ዲግሪ ሴልሺዬስ ጨምሯል። በዚሁ ምክንያት ወደ አየር ንብረት የሚለቀቀው የካርበን ዳይኦክሳይድ መጠን 50 በመቶ ጨምሯል።

የዘርፉ ምሑራን እንደሚሉት፤ የአየር ንብረት ለውጥ ይዞት የሚመጣውን መዘዝ ለማስቀረት የሙቀት መጠንን መቀነስ የግድ ነው። ለዚህም ዛፍ መትከል አንዱና ዋነኛው መፍትሔ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው። ይህን የተረዳችው ኢትዮጵያም በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጣውን ስጋት ለመቀነስ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች። በመሆኑም ለአየር ንብረት ተፅዕኖ የማትበገር የተዋበች፣ ፅዱና አረንጓዴ ኢትዮጵያን ለመገንባት እያደረገች ባለው ሰፊ ርብርብ አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገብ ችላለች። በተለይም በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እንደ ሀገር ትርጉም ያለው ሥራ መሥራት መቻሏ የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ዛፍ መትከል አንዱና ዋነኛው መፍትሔ እንደመሆኑ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የድርሻዋን እየተወጣች ትገኛለች። ዛፍ ከመትከል ባለፈም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በናፍጣ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለመቀየር እያደረገች ያለች ጥረት ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።

በአሁን ወቅት በሀገራዊ ዕድገት ላይ ትልቅ አቅም እንዳላቸው በስፋት የሚነገርላቸው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በተለይ ለአፍሪካ ሀገራት ሰፊ የገበያ ዕድል ይዘው መምጣት እንደቻሉ በስፋት ይነገራል። አፍሪካ በዓለም ላይ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ገበያዎች አንዷ መሆኗ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንዱስትሪው መስፋፋት ከፍተኛ ዕድሎችን የሚፈጥር ይሆናል ተብሏል። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በተለይም ብክለትን የሚቀንሱ እና ኃይል ቆጣቢ መጓጓዣ በመሆናቸው በተለይም ወደፊት እጅግ ተፈላጊና ተመራጭ እንደሚሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ።

ለዚህም ነው ብዙ የአፍሪካ መንግሥታት ማበረታቻዎችን በማቅረብና የቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንዱስትሪዎችንና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ተጠቃሚዎችን እየደገፉ የሚገኙት። አሁን ላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ብዙ ፈተናዎች እየገጠሟቸው ቢሆንም፤ ኢንዱስትሪው በመጪዎቹ ዓመታት ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል። በ2030 በአፍሪካ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ገበያ 100 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል አንዳንድ ግምቶች የተቀመጡ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ ከ2019 ጀምሮ የኤሌክትሪክ መኪኖች በዓለም አቀፍ ደረጃም እንዲሁ ቁጥራቸው በከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ መጥቷል።

መረጃዎች እንዳመለከቱት ከሆነ በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም ከ25 ሚሊዮን በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ይገኛሉ። ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ የሚገኙት በቻይና ነው። ከዓለም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች 60 በመቶ ያህሉም የተመረቱት በቻይና ነው። ኢትዮጵያም ይህንኑ ጉዞ በመቀላቀል አያሌ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች በአውራ ጎዳናዎቿ እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ላይ ትገኛለች። ሀገሪቱ በከፍተኛ መጠን እያለማች የምትገኘውን እምቅ ታዳሽ ኃይል ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹ በማዋል ለነዳጅ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማዳን የምትችል መሆኑም ታምኖበታል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱም በዚሁ ምክንያት ነው። መንግሥት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ዛፍ መትከል ያለውን ትልቅ ድርሻ በመረዳት በአረንጓዴ ዐሻራ እያበረከተ ካለው አስተዋፅዖ በተጨማሪ አሁን ደግሞ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት የአየር፣ የድምፅና የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል እየሠራ ይገኛል።

ይሁንና በአሁን ወቅት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹ በስፋት ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ ባሉበት በዚህ ወቅት ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹ አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን ከማሟላት አንጻር የተጀማመሩ ሥራዎች እንዳሉ ሆነው ቀሪ ሥራዎች ስለመኖራቸው ግን አይካድም። በቅርቡ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት ለዘርፉ መሠረተ ልማት ከማሟላት አንጻር መዘግየት እንዳለ ተመላክቷል። ባለሥልጣኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በዋናነት የሚያስፈልጋቸው የኤሌክትሪክ ኃይል መሆኑን በመጥቀስ የኃይል መሙያ መሠረተ ልማት ለማሟላትና ታሪፍ ለማውጣት የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ሊገባ እንደሆነ አመላክቷል።

በውይይቱ ተሳታፊ ከነበሩት ባለድርሻ አካላት መካከል የግሪን ፔትሮሊየም ዲስትሪቢዩሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አንዱ ነው። የኩባንያው ምክትል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ዳንኤል ባልቻ እንዳሉት፤ ኩባንያው ነዳጅ በማከፋፈል ሥራ ላይ የተሠማራ እንደመሆኑ ለነዳጅ ማደያዎች ነዳጅ ያቀርባል። በአሁን ወቅትም መንግሥት በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኤሌክትሪክ ለመቀየር በሚያደርገው ጥረት ኩባንያው ትልቅ ድርሻ አለው። ለዚህም አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓል።

በአሁን ወቅት ከ180 ሺ በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል። እነዚህ ተሽከርካሪዎችም የቻርጅ አገልግሎት እያገኙ ያሉት በቤታቸው ነው። ይህ ተገቢነት የሌለው አሠራር በመሆኑ በየ50 እና 100 ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኙ ነዳጅ ማደያዎች፣ የተለያዩ ሆቴሎችና ሕንጻዎች ላይ የቻርጅ አገልግሎቱ ሊኖር ይገባል። ይህ መሆን ከቻለ ዘርፉ ለባለሃብቱም ሆነ ለሀገር ትልቅ ጠቀሜታን ያበረክታል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማውጣት ነዳጅ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የምታስገባ እንደመሆኗ ብዙ ጊዜ የነዳጅ እጥረት ያጋጥማል ያሉት አቶ ዳንኤል፤ እንደ ሀገር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም መቻል በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ነው ያስረዱት። እሳቸው እንዳሉት ፤ የነዳጅ ወጪን ከመቀነስ ባለፈ የካርቦን ልቀትን ከመከላከል አንጻርም ትልቅ ጠቀሜታ አለው። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ይዘው የመጡትን ዕድል ለመጠቀም መንግሥትን ጨምሮ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

ዘርፉ አዲስ እንደመሆኑ ተሽከርካሪዎቹ የቻርጅ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ፈጣን የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ለማቋቋም ከፍተኛ ወጪን ይጠይቃል ያሉት አቶ ዳንኤል፤ ኩባንያው በአሁን ወቅት ናዝሬትና ሀዋሳ ላይ አገልግሎት መስጠት የሚያስችላቸው ማደያ መኖሩን ጠቅሰዋል። አዲስ አበባ ላይም እንዲሁ ፈጣን ኃይል የመሙላት አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ጣቢያዎችን ለመገንባትና ቻርጀሩን ለማስመጣት ዝግጁ እንደሆኑና አዲስ አበባን ጨምሮ በዋና ዋና ከተሞች ላይ ተደራሽ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

ያም ቢሆን ታዲያ የኃይል መሙያ ጣቢያው ትራንስፎርመርን ጨምሮ የተለያዩ ግብዓቶችን የሚፈልግ በመሆኑ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ በቶሎ ወደ ገበያው መግባት እንዳለበት አመላክተዋል። ይህም በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችል እንደሆነ አብራርተዋል።

በአገር ደረጃ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ እየገቡ እንደሆነ ያነሱት አቶ አሕመድ ሰይድ በነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የኢነርጂ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው። እሳቸው እንዳሉት፤ በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ገደብ የተጣለባቸው በመሆኑ በአሁን ወቅት በአብዛኛው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ ናቸው። እነዚህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚንቀሳቀሱበት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ይህን ተደራሽ ለማድረግ ባለሥልጣኑ መመሪያ አዘጋጅቷል።

የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ያወጣው መመሪያ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴርን ጨምሮ በርካታ የሚመለከታቸው አካላት የተሳተፉበት ነው። መመሪያውን ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር የዘገየ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አሕመድ፤ በአሁን ወቅት በመመሪያው የመጨረሻ ረቂቅ ላይ ውይይት መደረጉንና በቅርቡም መመሪያው ፀድቆ ሥራ ላይ የሚውል እንደሆነ ነው የገለጹት።

በግልም ይሁን በተቋም ደረጃ ቀደም ብለው የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን የገነቡና አገልግሎት መስጠት የጀመሩ አካላት በዚሁ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲካተቱ የስድስት ወር ጊዜ የተሰጣቸው መሆኑን ያነሱት አቶ አሕመድ፤ መመሪያው ከፀደቀ በኋላ ቁጥጥር የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል። አዳዲስ የሚገነቡትንና ወደ ዘርፉ የሚመጡትንም እንዲሁ በተመሳሳይ በዚሁ ሕግ ውስጥ እንዲያልፉ የማድረግ ሥራ ይሠራል ብለዋል።

‹‹ባለሥልጣኑ እንደተቆጣጣሪ ተቋም ሕጎችንና መመሪዎችን ያወጣል›› ያሉት አቶ አሕመድ የወጡ ሕጎችንና ደረጃዎችንም በሥራ ላይ እንዲውሉ ጭምር ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል። በመሆኑም በዘርፉ የተሠማሩ ባለሃብቶች ወደ ተግባር ሲገቡ ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ የተለያዩ ችግሮችን ከወዲሁ በማንሳት ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፤ ከባለሥልጣኑ ተግባርና ኃላፊነት ውጭ የሆኑ ችግሮችም ቢሆኑ ወደሚመለከተው አካል በማቅረብ ችግሩ የሚፈታበትን አግባብ የማመቻቸት ሥራ ይሠራል ሲሉ ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ለአብነትም አዳዲስ የኃይል መሙያ ጣቢያ የሚገነቡ አካላት የመሬት ጥያቄ አላቸው። ይህንን ጥያቄ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመወያየት ችግሩ መፍትሔ እንዲያገኝ የማድረግ ሥራ ባለሥልጣኑ ይሠራል። የማበረታቻ ፓኬጆችን በተመለከተም እንዲሁ የኃይል መሙያ ቻርጀሮችና ሌሎች ግብዓቶች ከታክስ ነፃ እንዲገቡና ሌሎች ማበረታቻዎችም በባለሃብቱ ተጠይቋል። በመሆኑ ባለሥልጣኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት በማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያገኙ ያደርጋል።

በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች በአጭር ጊዜ ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል ይለወጣሉ የሚል ዕምነት አለመኖሩንና ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ መሆኑን ያነሱት አቶ አሕመድ፤ አሁን በሥራ ላይ ላሉት ነዳጅ ማደያዎች ቅድሚያ በመስጠት የኃይል መሙያ ጣቢያ ሆነው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል። ለዚህ ዋናው ምክንያት ማደያዎቹ በቂ ቦታ ያላቸው በመሆኑ የቻርጅ ጣቢያዎችን መገንባት የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥራል። በቀላሉም ማላመድ ይቻላል። በቀጣይም ታዳሽ ኃይልን በስፋት መጠቀም የሚቻልበትን ዕድል አጠናክሮ መቀጠል ይገባልም ብለዋል።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ በሀገሪቱ ተግባራዊ መሆን እንዲችል የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እየተወጡ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ አሕመድ፤ አንዱና ዋናው ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ሲሆን፤ ለተሽከርካሪዎቹ ፈቃድ እየሰጠ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የሚፈቅደው ነው። ሁለተኛው ኃይል የሚያቀርቡት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ነው። ሦስተኛው የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ተቆጣጣሪ እንደመሆኑ እነዚህ ሦስቱ ተቋማት በቀጥታ ተሳታፊ ናቸው። ከማበረታታት አንጻር የገንዘብና ኢኮኖሚ፣ ጉምሩክ፣ ገቢዎችና ሌሎችም በጋራ በመሆን የሚሳተፉ ይሆናል።

‹‹እንደ አገር ለነዳጅ ብቻ በዓመት ከአራት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ይወጣል›› ያሉት አቶ አሕመድ፤ ለነዳጅ እየወጣ ያለው ወጪ ከፍተኛ ሃብት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይኸው ነዳጅ ደግሞ ሀገር ውስጥ ገብቶ በምን ሁኔታ እየተሸጠ እንደሆነ አንስተዋል። በአሁን ወቅት ነዳጅ ላይ በቂ የሆነ የሪፎርም ሥራ በመሥራት ውጤት መምጣቱን ጠቅሰው፤ አንደኛው ከድጎማ የመውጣትና በዓለም አቀፍ ዋጋ መመራት ሲሆን፤ በሂደት ደግሞ የሚደጎም ካለ እየተደጎመ ይሄዳል በማለት አጠቃላይ የሪፎርም ሥራው ግን ውጤት አምጥቷል ነው ያሉት።

እሳቸው እንዳሉት፤ ይህንን ሪፎርም ወደ ኢነርጂ ማምጣት ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ኢነርጂ እንደሚታወቀው ታዳሽ ኃይል ነው። ስለዚህ በዚህ ታዳሽ ኃይል ሪፎርም ማድረግ ከተቻለ ከአገር አልፎ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር ኢነርጂ መሸጥ ይቻላል፤ ተችሏልም። ከዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት የሚችል ይሆናል። በሂደት ደግሞ ያለውን ኢነርጂ በአግባቡ በመጠቀም ትልቅ ለውጥ ማምጣት የሚቻል ሲሆን፤ እንደሀገር የምንከተለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ በመሆኑ በአረንጓዴ ዐሻራ አበረታች ውጤት እየታየ ነው።

ስለዚህ ረጅም ጊዜ ሊወስድብን ቢችልም አሁን ላይ ከነዳጅ እየወጣን ታዳሽ ኃይልን መጀመር አለብን በሚል ወደ ተግባር ተገብቷል ያሉት አቶ አሕመድ፤ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት የምትችልና ምንም ጥርጥር የሌለው እንደሆነም አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You