ትራምፕ በዘንድሮው ምርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ ለዩክሬን የሚደረገውን ወታደራዊ ድጋፍ ሊያቋርጡ ይችላሉ ተባለ

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዘንድሮ ምርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ እንደሚያቋርጡ የደህንነት አማካሪዎቻቸው ተናግረዋል።

የትራምፕ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሊውተነንት ጄነራል ኬት ኪሎግ የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት መቋጫ ስትራቴጂን አዘጋጅተው ለትራምፕ ማቅረባቸውን ለሮይተርስ ተናግረዋል።

በዚህ ስትራቴጂ ጦርነቱን ሊያስቆሙ የሚችሉ የመፍትሔ ሃሳቦች የተቀመጡ ሲሆን፤ ከነዚህ መካከል ሁለቱን ተዋጊዎች በየትኛውም መንገድ ወደ ድርድር መድረክ ማምጣት የሚለው የመፍትሔ ሃሳብ ትኩረት ተሰጥቶታል ነው ያሉት።

ዩክሬን ለመደራደር ፈቃደኛ ካልሆነች አሜሪካ ወታደራዊ ድጋፏን የምታቆም ሲሆን፤ በአንጻሩ ሩሲያ እምቢተኝነትን ካሳየች ለዩክሬን ገደብ የሌለው የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንደሚያደርግ በስትራቴጂው ላይ ተጠቅሷል።

ትራምፕ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በነበራቸው ቆይታ እና በምርጫ ቅስቀሳ መድረኮች ላይ እርሳቸው በስልጣን ላይ ቢሆኑ ሩሲያ ዩክሬንን እንደማትወር በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት የአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆባይደን የሩስያ እና የዩክሬንን ጦርነት የያዙበት መንገድ ወደ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት የሚወሰድ ነው ሲሉም ይተቻሉ።

ዩክሬን ሩሲያን የማሸነፍ አቅም የላትም ብለው የሚያምኑት ትራምፕ ጦርነቱን ለማቆም ሁለቱን ወገኖች አስቀምጦ ማደራደር መፍትሔ እንደሚሆን ተናግረዋል።

“የጆ ባይደን አስተዳደር ለዩክሬን በአሜሪካ ታክስ ከፋዮች ገንዘብ ያስታጠቀው የጦር መሳሪያ የጦርነቱን ውጤት ሊቀይረው አልቻለም፤ ስለዚህ መጨረሻው ላልታወቀ ጦርነት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማድረግ ከኪሳራ የዘለለ ውጤት የለውም” ያሉት የትራምፕ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጄነራል ኪሎግ ናቸው::

አማካሪው አክለውም ጦርነቱን ለማስቆም መፍትሔው ሁለቱ ሀገራት ልዩነቶቻቸውን አጥብበው እንዲቀራረቡ ማድረግ ብቻ ነው ብለዋል።

ከ2017-2021 በነበረው የትራምፕ የስልጣን ዘመን በብሔራዊ ደህንነት አማካሪነት ያገለገሉት ሊውተነንት ጄነራል ኪሎግ በተኩስ አቁም የሚጀምረው በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል የሚደረገው የሰላም ድርድር ቀጥሎም ወደ ዘላቂ ጦርነት ማቆም እንዲገቡ፣ የኔቶ የአባልነት ጥያቄን ጨምሮ በድንበር ጉዳዮች ላይ እንዲደራደሩ ያስችላል ነው ያሉት።

ይህ በትራምፕ የደህንነት አማካሪዎች የተዘጋጀው የጦርነት ማቆም ስትራቴጂ አሜሪካ በቀጣናው የምታሳልፈው ትልቁ ውሳኔ መሆኑን ተከትሎ ወደ ተግባራዊነት የሚቀየር ከሆነ ተቃውሞዎችን ሊያስተናግድ እንደሚችል ይጠበቃል።

ትራምፕ በዚህ ስትራቴጂ የዋሽንግተን የቅርብ አጋር ከሆኑ አውሮፓውያን እና ከራሳቸው ሪፐብሊካን ፓርቲ ሊገጥማቸው የሚችለው ተቃውሞ ተጠቃሽ ነው። ትራምፕ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪዎቻቸው ባቀረቡት ስትራቴጂ ዙሪያ ይፋዊ ማብራሪያ አልሰጡም።

ነገር ግን በምርጫው የሚያሸንፉ ከሆነ ይህን ስትራቴጂ ባይቀበሉ እንኳን አሜሪካ በራሷ ጉዳዮች ላይ ማተኮር አለባት በሚለው አካሄዳቸው ለዩክሬን የሚደረገውን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ሊቀንሱ እንደሚችሉ ይጠበቃል።

አሜሪካ እስካሁን ለዩክሬን 70 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ወታደራዊ ድጋፎችን አድርጋለች።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Recommended For You