ዓለማችን በተለያየ የዕድገት ሂደት ውስጥ ስትጓዝ ቆይታለች። ግብርና የመጀመሪያውን የሰው ልጅ ስልጣኔ ያመጣ ሲሆን፤ በተራው ደግሞ የተሻለ ካፒታልና የሰለጠነ የሰው ኃይል ለሚሻው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ቦታውን አስረክቧል። የኢንዱስትሪው ዘርፍ በርካታ ሀገራትን ለዕድገትና ለብልጽግና አብቅቷል፤ የተሻለ የአኗኗር ሥርዓትን ፈጥሯል። አሁን ደግሞ ዘመኑ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘመን ነው። ዘመነ ዲጂታላይዜሽን ዓለም በየዕለቱ አዳዲስ ክስተቶችን እንድታስተናግድና በፍጥነት እንድትጓዝ እያደረጋት ይገኛል።
ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎቶችን በማቀላጠፍ፤ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራትና ገንዘብ፤ጊዜንና ጉልበትን በመቆጠብ ለአንድ ሀገር ዕድገትና ብልጽግና የማይተካ ሚና ይጫወታል። በተለይም በአሁኑ ጊዜ የአገልግሎት አሰጣጥም ሆነ የኢኮኖሚ ዝውውሩ በቀጥታ የታያዘው ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂው ጋር በመሆኑ የሀገራት ዕድገትም ሆነ ውድቀት ለዘርፉ በሰጡት ትኩረት ልክ የሚለካ ነው።
ይህንኑ እውነታ በመገንዘብም ኢትዮጵያ ከአምስቱ የዕድገት ዘርፎች ውስጥ አንዱ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እንዲሆን ፈቅዳ ወደ ሥራ ገብታለች። ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን በመቅረጽም ሀገሪቱ በሁሉም መስክ ተወዳዳሪ የሆነ ኢኮኖሚን ለመገንባት ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች። ይህ ስትራቴጂም በዋናነት የዲጂታል መሰረተ ልማት በመገንባት እና በማስፋት የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እድገት ማፋጠንን ዓላማ ያደረገ ነው።
ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ እየተገበረች ያለችው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስትራቴጂ የመንግሥትን አገልግሎት በዲጂታል የታገዘ እንዲሆን በማድረግ ዜጎች ባሉበት ሆነው የመንግሥትን አገልግሎቶች በቀላሉ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። የዜጎች የዕለት ተዕለት ሕይወት እንዲቀላጠፍም መሠረት ይጥላል። ሌብነትና የጨለማ ኢኮኖሚን ለማስወገድም ትልቅ አቅም ይሆናል።
ይህንኑ መነሻ በማድረግም ኢትዮጵያ እየገነባች ባለው ዲጂታል ኢኮኖሚም ከ526 በላይ የሆኑ የመንግሥት አገልግሎቶች በኤሌክትሮኒክ መንገድ እንዲፈጸሙ፤ የክፍያ ሥርዓቶችም በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ሥርዓት እንዲሆኑ እና የተለያዩ መተግበሪያዎች እንዲለሙ ተደርገዋል።
ከታችኛው ቀበሌ ጀምሮ እስከ ላይኛው አካል ድረስ ያሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን እርስ በርሳቸው በማገናኘትና መረጃ በማለዋወጥ ለኅብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፤ ይህም በአገልግሎት አሰጣጡ ለተማረረው ሕዝብ ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ ነው።
ሆኖም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የጥቅሙን ያህል ለብሔራዊ አደጋም የተጋለጠ ዘርፍ ነው። የዲጂታል ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሥርዓት በጥንቃቄና በአግባቡ ሊመራ ካልቻለ የሀገርን ጥቅም ሊጎዳ የሚችል ነው። በሌላ በኩል የዜጎችን የማኅበራዊ ትስስር እሴት በመሸርሸር ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ቀውስም ያስከትላል።
የአሠራር ሥርዓትና አገልግሎት ወደ ዲጂታላይዜሽን እየተሸጋገሩ በመሆኑ የሳይበር ጥቃትም እያደገ መጥቷል። የሳይበር ወንጀለኞች ጥቃት ለመሰንዘር፣ መረጃ ለመስረቅ፣ አገልግሎትን ለማወክ ኅብረተሰቡ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶች በርካታ ናቸው።
ስለዚህም የዲጂታል ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሥርዓት በጥንቃቄና በአግባቡ ሊመራ ይገባል። ዘርፉ የራሱ የሆነ እውቀትና ክህሎትን የሚጠይቅ በመሆኑም በክህሎት የዳበረ የሰው ኃይልንም ማፍራት የግድ የሚል ነው።
ዘመኑ የሚጠይቀውን አቅም በመፍጠር ሀገራዊ ግንባታን ለማፋጠን እና ከዘርፉ ሀገርና ሕዝብ የሚፈለገውን ጥቅም እንዲያገኙ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አተገባበር ሥርዓትና አመራር ዙሪያ ሁሉም አካላት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል። በሀገር አቀፍ ደረጃ የሳይበር ደህንነት አቅምን የሚያጠናክሩና የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን ደህንነት የሚያረጋግጡ የሕግ ማዕቀፎችን መቅረጽ ይገባል።
እያደገ የመጣውን የጥቃት መጠን ለመከላከል በማህበረሰቡ ላይ ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ፈጠራ ሥራን መሥራት ወሳኝ ነው። የሳይበር ደህንነት ጉዳይ በመንግሥት ተቋማት፣ በግሉ ሴክተርና በዓለም አቀፍ አጋሮች መካከል ትብብርና ቅንጅት የሚጠይቅ በመሆኑም ሁሉም አካላት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፋይዳንና ተያይዘው የሚመጡ ስጋቶችንም ሊረዱ ይገባል።
ከዚሁ ጎን ለጎንም የጉዳዩን አሳሳቢነት በውል በመረዳት ጊዜውን የዋጁ የወደፊቱን ታሳቢ ያደረጉ አዋጆች፣ ደንቦችንና ሌሎች የሕግ ማዕቀፎችን ተግባራዊ ማድረግም ያስፈልጋል!
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2016 ዓ.ም