ሰላምና ልማት የማይነጣጠሉ ጉዳዮች ብቻም ሳይሆኑ፤ ለአንድ ማኅበረሰብ ወይም ሕዝብ መሠረታዊ ነገሮች ናቸው፡፡ በተለይም በመንግሥት እና ሕዝብ የግንኙነትና መተማመን አውድ ውስጥ ልማት እና ሰላም ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ለመበልጸግ እየተጉ ላሉ ሀገራት ደግሞ የልማት እና ሰላም ተሰናስሎ መገኘት የብልጽግና ግስጋሴያቸው እውን መሆን አስኳል ነው፡፡
በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ይስተዋል የነበረው ፍትሐዊ ያልሆነ የልማት ተጠቃሚነት ችግር፤ ኢትዮጵያውያን ከፍ ላለ ጥያቄ እንዲነሱ፤ ለውጥንም እንዲናፍቁ አደረጋቸው፡፡ የመልማት ጥያቄዎቻቸው አለመመለስ ደግሞ ሕዝቡ የለውጥ ፍላጎቱን ወደ አመጽ እንዲያሸጋግረው አስገደደው፡፡ እናም በሕዝብ አመጽና እንቢታ የታጀበው ጉዞ፤ በለውጥ ተደመደመ፡፡
የሕዝቦች ፍትሐዊ የመልማት ፍላጎት ገፍቶት፤ የሰላም አጀንዳም ተሰጥቶት ወደ ስልጣን የመጣው የለውጥ ኃይልም ይሄንኑ የሕዝብ ጥያቄ የመመለስ ኃላፊነቱን ለመወጣት እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም ከለውጥ ማግስት ባሉ ዓመታት በኢትዮጵያ የሕዝቦችን ሁሉን አቀፍ ጥያቄዎች፤ በተለይም የልማት፣ የመልካም አስተዳደር እና የሰላም ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል፡፡
ከሰሞኑም እየታየ ያለው እውነት የዚህ ተግባር አንድ አብነት ነው፡፡ በተለይ በክልሎች ሰው ተኮር የሆኑ እና ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው የመሠረተ ልማት አውታሮች በስፋት ተገንብተው ለአገልግሎት እየበቁ መሆናቸውን እየተመለከትን ነው፡፡ ለአብነትም፣ በኦሮሚያ ክልል ከ20 ሺህ በላይ የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ወደሥራ የማስገባት እንቅስቃሴ ታይቷል፡፡ በሐረሪ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎችም ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች እየተመረቁ ለአገልግሎት ክፍት እየሆኑ ነው፡፡
እነዚህ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ቀደም ሲል ሕዝቡ የፍትሐዊነት ጥያቄ ሲያነሳባቸው የነበሩ፤ የመማር፣ የመታከም፣ ሰርቶ የመለወጥ፣… የመሳሰሉ ፍላጎትና ጥያቄዎቹን የሚመልሱለት ናቸው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ፕሮጀክቶች ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ መንገዶች፣ የውሃ እና መብራት መሠረተ ልማቶች፣ የወጣቶች ስብዕና መገንቢያዎች፣ የማምረቻ እና የመገበያያ ስፍራዎችን ያካተቱ ለወጣቱ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ማህበራዊም ኢኮኖሚያዊም ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው፡፡
እነዚህ ፕሮጀክቶች ዜጎች ሠርተው እንዲለወጡ፣ ተምረው ክህሎት እንዲጨብጡና የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡ፤ እናቶችና ሴቶች ብሎም ወጣቶች ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ተላቀው ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሀገራቸውን የሚጠቅሙበትን ዕድል የሚያገኙባቸው፤ ሥራ ፈትተው ለሌላ ዓላማ የሚውሉ ጭንቅላቶችና እጆች ለልማት እና ሀገራዊ ብልጽግና ተደማሪ አቅም እንዲሆኑ የሚያደርጉ ናቸው፡፡
የሕዝቡ ጥያቄም ይሄው ነበር፡፡ ምክንያቱም የሕዝቡ መሻት ትምህርት ቤቶች በሙላት ተገንብተው ልጆቹ ተምረው ነገ የተሻለ የሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዲሆኑለት ነው፡፡ የጤና ተቋማት ተደራሽ ሆነውለት ጤናው ተጠብቆ ብቁ የልማት ተሳታፊ መሆን ነው፡፡ መንገዶች ተገንብተው ያመረተውን በቀላሉ ለገበያ ማድረስ እንዲችል ነው፡፡ የውሃ እና መብራት ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን በየአካባቢው አነስተኛም፣ መካከለኛም ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ አቅም እንዲፈጥሩለት ማስቻል ነው፡፡
በጥቅሉ፣ ያመረተው ገበያ እንዲያገኝ፣ ልጆቹ እንዲማሩለት፣ ጤናው እንዲጠበቅለት፣ ኢንዱስትሪዎች እና ሌሎችም ለአካባቢው ልማት፣ ለወጣቱም የሥራ ዕድል አበርክቶ ያላቸው የልማት አውታሮች በፍትሐዊነት እንዲደርሱት ነበር ሕዝቡ ከየአቅጣጫው ሲጠይቅ እና ለውጥ ፈልጎም ሲታገል የነበረው፡፡ አሁን ላይ ደግሞ እነዚህ ጥያቄዎቹ እየተመለሱለት መሆኑን በተግባር መመልከት ተችሏል፡፡
ይሁን እንጂ ዛሬም ይሄን መሰል የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዳያገኙ እንቅፋት የሆኑ ተግባራት እዚህም እዚያም መታየታቸው አልቀረም፡፡ ለአብነት፣ ከ20 በላይ የልማት ፕሮጀክቶች ተገንብተው እየተመረቁ ባሉበት የኦሮሚያ ክልል፤ የጥፋት ኃይሎች የዜጎችን ሰላም የሚነሱ ወጣቶች የመግባት፣ ሰርቶ የመለወጥ ሂደታቸውን የሚፈትኑ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡
እነዚህ ሁነቶች ደግሞ ዜጎች የትናንት ጥያቄዎቻቸው እንዳይመለሱ ብቻ ሳይሆን፤ ከዛሬ የተሻገረ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ነገር ግን በመንግሥት በኩል በችግር ውስጥም ተሆኖ የሕዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ፍሬ እያፈራ ከጥፋት ኃይሎች ሴራ በተቃራኒው እየተጓዘ ስለመሆኑ በወለጋ ዞኖች ያሉ ተግባራት እማኞች ናቸው፡፡
ይሄን መሰል ጉዞ ደግሞ ዜጎች ለልማታቸውም፣ ለሰላማቸውም ዋጋ ሰጥተው ከመንግሥት ጎን ሆነው እንዲተጉ የሚያደርግ፤ የልማት ጥያቄዎቻቸውን በመመለስ ውስጥ ዘላቂ ሰላማቸውን ለማስጠበቅ አቅም የሚሆን ሕዝባዊ አሰላለፍን የሚያጠናክር ነው፡፡ በመሆኑም አሁን ላይ እየታየ ያለው የሕዝብን የልማት ጥያቄ የመመለስ ጥረት እና እየታየ ያለውም ፍሬ፤ ዘላቂ ሰላምን እውን ለማድረግ ለሚደረገው ሥራ ተደማሪ አቅም የሚሆን ነው!
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2016