ተተኪና ወጣት አትሌቶችን ለማፍራት ተስበው ከተቋቋሙ የማሰልጠኛ ማዕከላት መካከል አንዱ የበቆጂ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ነው። የበቆጂ ከተማ እና አካባቢው የአትሌቶች መፍለቂያ እንደመሆኑ የስፍራውን እምቅ አቅም ለመጠቀምና ለአትሌቲክስ የዋለውን ውለታ ለማስተወስ የተመሰረተ ማዕከል ነው። ዘመናዊ የማሰልጠኛ ማዕከላት ማሟላት የሚገባቸውን ነገሮች አካቶ የተገነባ ቢሆንም፤ ለማዕከሉ ሰልጣኞች መሠረታዊና አስፈላጊ የሆነው የመሮጫ መም እና የውሃ አገልግሎትን ግን ማካተት አልቻለም። እነዚህ ክፍተቶችም ለሰልጣኞች ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር አድርገዋል።
ማዕከሉ የተመሰረተው በ2004 ዓ·ም ሲሆን፤ በስፖርቱ ታይቶ የነበረውን የመቀዛቀዝ ስሜት ለማነቃቃትና የተተኪ አትሌቶችን ክፍተት ለመድፈን የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ ቆይቷል። በኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፤ እንዲሁም፣ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስምምነት የተቋቋመው ማዕከሉ 23 ሴት እና 23 ወንድ፣ በድምሩ 46 ሰልጣኞችን በማቀፍ የስልጠና ሥራውን ጀምሯል። ከሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በተቀመጠው የመመልመያ መስፈርት መሠረት ሰልጣኞችን መልምሎ ለሁለት ዓመት ተገቢውን ስልጠና ከሰጠ በኋላ፣ ወደ ክለብ ያሸጋግራል። በዚህም በርካታ ተተኪና ውጤታማ አትሌቶችን ማፍራት የቻለ ሲሆን፤ ከተመሠረተ ጀምሮ 200 ሰልጣኖችን ተቀብሎ በማሰልጠን 83 ወንዶች እና 77 ሴቶችን በድምሩ 160 ታዳጊ አትሌቶችን ለክለብ አብቅቷል። ከነዚህም ውስጥ ሀገርን በተለያዩ መድረኮች በመወከል ውጤታማ የሆኑ 20 የሚደርሱ አትሌቶችን አፍርቷል፡፡
በዚህ ዓመትም 46 ታዳጊዎችን መልምሎ በማሰልጠን ላይ ይገኛል። ምንም እንኳን በሚሰጠው ስልጠና ውጤታማ እና ሀገርን መወከል የሚችሉ አትሌቶችን እያፈራ ቢሆንም የተሟላና ለስልጠና የሚያስፈልግ ጥራቱን የጠበቀ ሜዳና የመሮጫ መም ግን የለውም። ከሚሰጠው ስልጠና እና አገልግሎት ባለፈ የሜዳ እና የውሃ አቅርቦት ችግር የፈተናቸው መሆኑንም የማዕከሉ ሰልጣኞች ይናገራሉ። ማዕከሉ የራሱ ሜዳና መሮጫ መም ስለሌለው በከተማው በሚገኝ ሜዳ ስልጠናው የሚደረግ ቢሆንም ምቹ አይደለም፡፡
የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ጸጋዬ አንበሳ፤ በምልመላ መስፈርቱ መሠረት አትሌቶችን ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በመምረጥ ማዕከሉን ተቀላቅለው ስልጠናቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ ክለብ እንደሚገቡ ያብራራሉ። ማዕከሉ እምቅ አቅም እና ፕሮጀክቶች የሚገኙባቸውን ቦታዎች በመለየት እና ውድድሮችን በማድረግ ከተመለመሉ በኋላ አሰላ ላይ የመጨረሻ ዙር ውድድር በማድረግ የተመረጡ ታዳጊዎች ስልጠናውን ይጀምራሉ።
ለስልጠና የሚያግዙ የተሻሉ ሁኔታዎች የመኖራቸውን ያህል ግን ጉድለቶች ስለመኖራቸውም አልካዱም። ከሜዳ እና ከውሃ አቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ድጋፍ እያደረገ በመሆኑ መሻሻል እንዳለም ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ለማዕከሉ ትጥቅን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋል። ማዕከሉ ጂምናዚየምን ጨምሮ የማደሪያ፣ የምግብ እና የትምህርት አገልግሎትን ለሰልጣኞቹ ይሰጣል። የራሱ የሆነ ሜዳ ባለመኖሩ የከተማውን ሜዳ የሚጠቀም ቢሆንም፤ ግን የማያረካና ለአገልግሎት የማይመች በመሆኑ ስልጠናው ላይ የራሱን ተጽእኖ እንደሚያሳድርም ያምናሉ። ሌላኛው ማዕከሉን የፈተነው የውሃ ችግር ሲሆን፤ እንደ ከተማ የተከሰተ ነው። ለማዕከሉ ሰልጣኞች በመኪና ተቀድቶ እየቀረበ ቢሆንም የራሱን ጫና ማሳደሩ አልቀረም። በከተማ አስተዳደሩ የተጀመረ ትልቅ የውሃ ፕሮጀክት ሥራ ከተጠናቀቀ ችግሩ እንደሚፈታ እምነታቸው እንደሆነም ይጠቅሳሉ፡፡
ደረጃውን የጠበቀ ሜዳ በማዕከሉ ለመሥራትና ችግሩን ለመቅረፍ ከክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር ተነጋግሮ በበጀት እቅድ ውስጥ መግባቱንም ያስረዳሉ። ክልሉም በጀት ውስጥ አስገብቶ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ክትትል በማድረግ ላይም ነው፡፡
ማዕከሉ በክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የተቀጠሩ አራት ባለሙያዎች እና አንድ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተቀጠረ ባለሙያ በድምሩ አምስት ባለሙያዎች ያሉት ሲሆን፤ ቁጥራቸው በቂ ባይሆንም ጥሩ አቅም ያላቸው መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ። በእውቀት የተደገፉ እቅዶችን አውጥቶ ሳይንሳዊ ስልጠናዎችን በአግባቡ በመስጠት ውጤታማ አትሌቶችን በማፍራት ላይም ይገኛሉ።
ማዕከሉ የተመሠረተው ወደ አካዳሚ ደረጃ ለማሳደግ እቅድ ተይዞ በመሆኑ እና 11 ሄክታር ላይ ያረፈ ሰፊ ቦታን በመያዙ የማስፋፊያ ግንባታን በማካሄድ ወደ አካዳሚ ለማሳደግ ከሚመለከተው አካል ጋር እየተሠራ እንደሆነም ጨምረው ጠቁመዋል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም