ከቆዳ ስር ያለ የቀለም ቀመር ከአለባበስ ጋር ያለው ተዛምዶ

በማንኛውም አጋጣሚ በሥራ ቦታ፣ በተለያዩ ሁነቶች፣ እና በአንዳንድ ፕሮግራሞች ላይ ሰዎች አምሮባችኋል ሊሉ ይችላሉ። በአለባበሳችሁ ምክንያት አይን ውስጥ የሚገባ ውበት ለመፍጠር ሰዎች ብዙ አይነት የአለባበስ መንገድን ይከተላሉ። ከሰውነት ቅርጻቸው ጋር የሚሄድ፤ የሚወዱትን የቀለም ምርጫ ያማከለ፤ አልያም ደግሞ ከሚሄዱበት ቦታ አንጻር የሚለብሱትን ልብስ ይመርጣሉ። ብዙዎች የልብስ ምርጫቸውን ከሚውሉበት ቦታዎች ጋር የተሳሰረ ከማድረግ ባለፈ ምርጫቸው ከስሜታቸው ጋር ጭምር ቁርኝት ይኖረዋል።

አሁን ላይ ተዘርዝረው የማያልቁ ብዙ አይነት ፋሽኖች ይስተዋላሉ። ሰዎች የራሳቸውን የአለባበስ ስታይል የሚመርጡባቸው መንገዶችም የተለያዩ መሆናቸውም በዚሁ ምክንያት ነው። በእነዚህ መሰረት ሰዎች የሚያምርብኝ ይህ ነው በማለት የራሳቸውን ስታይል ሲከተሉ እናስተውላለን። አንድ ሰው በእለት ተዕለት በሚኖረው እንቅስቃሴ ውስጥ የሚለብሰውን ልብስ ሲመርጥ ካለው የሰውነት ቅርጽ ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን፣ ለሚውልበት ቦታ የሚመጥን እና ምቹ መሆኑን ማስተዋል የተለመደ ነው። በዛሬው የፋሽን ገጻችን ሰዎች የሚለብሱትን ልብስ ሲመርጡ ካላቸው ትክክለኛ የቆዳ ቀለም ጋር እንዴት አብረው ማስኬድ ይችላሉ የሚል ነው።

የቆዳ ስር ያለውን ትክክለኛ ቀለም ማግኘት ሰዎች የሚለብሱበትን እና ልብሶቻቸውን የሚመርጡበትን ሁኔታ እንከን የለሽ ያደርገዋል። የቆዳ ቀለም እና ከቆዳ ስር ያለ ቀለም ሁለት ልዩነት ያላቸው ነገሮች ሲሆኑ ቀይ ፣ ጥቁር ፣ ጠይም በማለት የምንለያቸው የቆዳ ቀለም ሲሆኑ፤ የቆዳ ቀለም ስር ያለ ቀለም ደግሞ ሞቃት ፣ ረጋ ያለ እና ድብልቅ የቆዳ ስር ቀለም ተብሎ ይለያል። የቆዳ ቀለም ስር ያለ የቆዳ አይነት በፋሽን ኢንዱስትሪ ላይ ጥናት በሚያደርጉ ሰዎች ሲገለጽ የተለያዩ እንደሆኑ ነው።

ሰዎች የሚስማማቸውን ልብስ ለመምረጥ ከቆዳ ቀለማቸው ስር ያለውን የቆዳ ቀለም ወይም ውስጣዊ ባህሪያቸውን መረዳት የግድ እንደሆነ ጥናቶች ያመላክታሉ። በፋሽን ኢንዱስትሪው ላይ ጥናት ያደረጉ የተለያዩ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ በዋናነት ሶስት አይነት ከቆዳ ቀለም ስር ያሉ የቀለም አይነቶች አሉ። (warm under tone) ሞቅ ያለ የቆዳ ቀለም፣ (cool under tone) በረድ ያለ የቆዳ ቀለም፣ ሁለቱንም አቀላቅሎ የያዘ (neutral under­tone) ይባላሉ። ለደንበኞቻቸው ልብስን የሚመርጡ ባለሙያዎች ልብስን ሲመርጡ እነዚህን የቆዳ ስር ቀለም በማጥናትና በተጨማሪም የጸጉር ቀለም የአይን ቀለምን ታሳቢ ያደርጋሉ።

ሞቃት የቆዳ ስር ቀለም ያላቸው ሰዎች ሲታዩ ጠየም ያለ የቆዳ ቀለም ያላቸው ሲሆኑ፤ እንዲህ አይነት የቆዳ ቀለም ያላቸው ሰዎች ደማቅ ቀለም ያላቸውን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ሰማያዊ ልብሶች አልያም ነጭ ልብስ ቢለብሱ ይበልጥ ጎልተው እና አምረው ይታያሉ። በተጨማሪም ደብዘዝ ያሉ የሚባሉ የቀለም አይነቶችም ሞቃት የቆዳ ስር ቀለም ካላቸው ጋር አብረው ይሄዳሉ። እንደ እነዚህ አይነት የቆዳ ቀለም ያላቸው ሰዎች በተለይም የጸጉር ቀለም ቢፈልጉ በተለምዶው ወርቃማ የምንለው የጸጉር ቀለም ከእነሱ ጋር አብሮ ይሄዳል።

በረድ ያለ የቆዳ ቀለም ስር ቀለም (cool under tone ) ያላቸው ሰዎች በተለምዶው ቀይ አልያም ጠይም ብለን ባንለያቸውም የቀይ ዳማ የሚባሉ እና በጣም ቀይ የማይባል የቆዳ ቀለም ያላቸው ሰዎች ሲሆኑ፤በሌሎች እይታ ረጋ ያለ የቆዳ ቀለም ያላቸው ናቸው። ረጋ ያለ የቆዳ ስር ቀለም ያላቸው ሰዎች የሚመርጡት የልብስ ቀለም ደመቅ ያላሉ አልያም ዝም ያሉ የቆዳ ቀለሞችን ምርጫቸው ቢያደርጉ ይመከራል። ቡናማ ቀለም፣ ወይነጠጅ አልያም ደብዘዝ ያለ ቀይ ቀለም ይበልጥ ውበት ይሰጣቸዋል። በረድ ያለ የቆዳ ቀለም ያላቸው ሰዎች ከወርቅ ይልቅ የብር ጌጣጌጥን ምርጫቸው እንዲያደርጉ ይመከራል።

ሞቃት እና በረድ ያለውን የቆዳ ቀለም ቀላቅለው የያዙ የቆዳ ቀለም ስር የሚገኙ የቆዳ ቀለም የያዙ ሰዎች (neutral undertone) ይባላሉ። የዚህ አይነት የቆዳ ቀለም ያላቸው ሰዎች ማንኛውንም አይነት ቀለም ያላቸውን ልብሶች ቢለብሱ ከእነርሱ ጋር አብሮ ይሄዳል። ምክንያቱም ያላቸው ቀለም ሞቃት እና ረጋ ያለ የሚባለውን የቆዳ ስር ቀለም አጣምሮ የያዘ በመሆኑ ነው። ድብልቅ የቆዳ ስር ቀለም ያላቸው ለእነርሱ ተብለው የተለዩት የቀለም አይነቶች ደማቅ ከሚባሉትም ሆነ ደብዘዝ ያሉ ናቸው ከሚባሉት ቀለሞች መካከል ላይ ያሉ የልብስ ቀለሞች ናቸው። በርገንዲ፣ ቤጅ ወይንም ሰማያዊ ቀለም ያላቸውን ልብሶችም ድብልቅ የቆዳ ስር ቀለም ያላቸው ሰዎች ቢለብሷቸው የተመረጡ የሚባሉ ናቸው።

ሰዎች ምን አይነት የቆዳ ስር ቀለም እንዳላቸው ለማወቅ የተለያዩ መንገዶች ስለመኖራቸው በዘርፉ የተደረገ ጥናት ያመላክታል። በብዛት የሚጠቀሰው በእጃችን ያለውን የደም ስሮች በመመልከት ሲሆን፤ የደም ስራቸው አረንጓዴ ተብሎ የሚለይ ከሆነ ከቆዳቸው ቀለም ስር ያለው ሞቃት ሲሆን፤ ረጋ ያለ የቆዳ ስር ቀለም አላቸው የሚባሉት ደግሞ ሰማያዊ የደም ስር ያላቸው ሲባሉ የእጃቸውን ደም ስር ቀለም ለመለየት የተቸገሩ ሰዎች ድብልቅ አልያም (neu­tral undertone) ያላቸው ናቸው። ሌላኛው የቆዳ ስር ቀለም የማወቂያ መንገድ በቅርብ ያሉ ሰዎች በእለት ተዕለት የልብስ ምርጫቸው ላይ የሚሰጡትን አስተያየት በመረዳት ሲሆን፤ ሌላኛው መንገድ ለማጌጫነት የምንጠቀማቸውን የተለያዩ ጌጣጌጦች በመምረጥ ይሆናል። የብር ማጌጫዎች የእጅ ሰዓት ውበትን የሚያላብሳችሁ ከሆነ የቆዳችሁ ቀለም ስር ያለው ቀለም ረጋ ያለ የሚባለው አይት ሲሆን፤ ወርቅ የሚያምርባቸው ሰዎች ደግሞ ሞቃት የቆዳ ስር ቀለም ያላቸው ናቸው፤ ሁለቱንም መልበስ የሚያምርባቸው ሰዎች እንዲሁ ድብልቅ የቆዳ ስር ቀለምን የያዙ ናቸው።

ዘመኑ የደረሰበት ይህ የቆዳ ቀለም ስር ያለውን ቀለም ማወቅ ሰዎች የሚለብሷቸውን ልብሶች፣ የጸጉራቸውን ቀለም መምረጥ የሚያስችላቸው ሲሆን፤ በተለይም እንስቶች የሚቀቡትን የሜካፕ አይነት ለመምረጥ ምቹና ቀላል እንደሆነ ጥናቶች አመላክተዋል።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You