ዘመኑ ግድ ከሚላቸው የጥናት መስኮች፣ የስልጠናና ትምህርት አይነቶች አንዱ ቴክኒክና ሙያ ሲሆን፤ ይህንኑ በመገንዘብም ሀገራት ለዘርፉ ልዩ ትኩረትን በመስጠት ማሰልጠኛ ተቋማትን ሲያቋቁሙ፣ የነበሩትንም ሲያጠናክሩ፤ ምሩቃንን ሲያሰለጥኑና ሙያተኞችን ሲያፈሩ እየተስተዋለ ነው። በተለይ እንደነ ቻይና ያሉ ሀገራት በቴክኒክና ሙያ አማካኝነት የት መድረስ እንደሚቻል በማሳያነት እየቀረቡ መሆናቸው ለዘርፉ አስፈላጊነት ከበቂ በላይ ማሳያ እየሆነ ይገኛል።
ትምህርት ሚኒስቴር ባዘጋጀው፣ በአምስተኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት መርሀ-ግብር (2008-2012 ዓ.ም) ላይ እንደተገለጸው፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዋና ዓላማ፣ በዝቅተኛና መካከለኛ ደረጃ ብቁ የሆነ፣ ሙሉ ፍላጐት ያለው፣ ራሱን ከሁኔታዎች አንፃር የሚያስተካክልና የፈጠራ ችሎታ ያለው የሰው ኃይል ማፍራት ነው፡፡ አላማው በፍላጐት ላይ በመመስረትና ጥራት ባለው የቴክኒክና ሙያ ትምህርት በመሰልጠን ተፈላጊ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት፤ ድህነትን ለመቀነስና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ለማበርከት የሚችል የሰው ኃይል መፍጠር ነው፡፡ (ገጽ 37)
በ“የግል ቴ/ሙያ ት/ስልጠና ተቋማት/ኮሌጆች ቼክሊስት” ላይ እንደሰፈረው የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ዓላማ በመካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ሰልጣኞቹ ብቁ ሥራ ፈጣሪና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ ሲሆን፤ የወደፊቱም የኢንዱስትሪውንና የአገልግሎቱን ሴክተር በማጎልበት፣ በሀገሪቱ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት በማምጣት የሕዝቡን ኑሮ መለወጥ ነው፡፡
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በሀገራዊ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ የጎላ ቢሆንም ከጥራት ችግር አለመላቀቃቸውን የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኤጀንሲ ማስታወቁ እንዳለ ሆኖ ኮሌጆቹ ወጣቶች ሙያዊ ክሂሎትን በመላበስ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የማድረግ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ የሚገባ መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም። ይህንን ተቋማዊና ሙያዊ ኃላፊነት ለመወጣት ደግሞ ብቁ ሆኖ መገኘትን የግድ ስለሚል ብቁ ናቸው በሚል እሳቤ ውይይታችንን እንቀጥላለን። (እዚህ ላይ፣ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና በኢትዮጵያ በመንግሥት እውቅና ተሰጥቶት በ1987 ፖሊሲ የተቀረጸለት መሆኑን፤ የኢፌዴሪ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት በ2005 መቋቋሙን ማስታወስ ተገቢ ይሆናል።)
መረጃዎች እንደሚናገሩት፤ በሀገሪቱ በሚገኙ የልማት ተቋማት ውስጥ ሰፊ የሰለጠነ የሰው ኃይል ሆነው የሚገኙት፤ በሀገራዊ የልማት ሂደት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ያሉት በቴክኒክና ሙያ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ናቸው። ይሁን እንጂ፣ ከላይ የጠቀስነው ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ክብረት ከኢቢሲ ጋር አድርገውት በነበረው ቆይታ እንደተናገሩት፣ ዘርፉ ጥራት ያለው ሰልጣኝ በማፍራት በሚፈለገው ደረጃ ለኢንዱስትሪው ማቅረብ አልታቸለውም።
እንደ አቶ ሀብታሙ ማብራሪያ የምዘና ደረጃው፣ የትምህርት ካሪኩለምና የማሰልጠኛ መሳሪያ አለመናበብ አሁንም የዘርፉ ተግዳሮቶች ናቸው። ክልሎች ከተፈጥሮ ሀብቶቻቸው ጋር የተቆራኘ የትምህርት ስልጠና እየተከተሉ አይደለም፤ ለአብነት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰፊ የቀርከሀ ሀብት ቢኖረውም ወደ ውጤት ከመቀየር አንፃር አልተሰራበትም።
እነዚህን ችግሮች በጥናት ላይ ተመስርቶ እየተዘጋጀ ያለው ፍኖተ ካርታ ይፈታዋል የሚል እምነት በብዙዎች ዘንድ አለ።
ፍኖተ ካርታው ተጠናቆ ወደ ሥራ እስኪተረጎም ድረስ ግን ችግሩ ዝም ተብሎ እየታየ እንዳልሆነ ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ካገኘናቸው መረጃዎች እንደተረዳነው ከሆነ ችግሮች አሉ። በተለይም ከጥራት ጋር ችግሮች አሉ። ችግሮቹን ለመፍታት ግን እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አሉ።
የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ፕሮግራሞችን የጥራት ደረጃ ለማሻሻል በተወሰደው እርምጃ የአሰልጣኞች ብቃት ተጠንቶ አስፈላጊ የሆኑ የሥራ ላይ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡ የስልጠናዎቹ ርዕሶች በታየው የቴክኒካል ጉድለት ላይ ብቻ ያተኮሩ ሳይሆኑ፣ የሥራ ፈጠራ ስልጠና፣ ሥራ ተኮር ሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ፣ ስልጠና የመስጠት ዘዴዎች፣ እንደዚሁም ተቋማዊ ግምገማ፣ ጥራትና ምርት ማሻሻያዎችን ያካተቱ ናቸው።
ሰልጣኞች መሠረታዊ ክሂሎቶችን ለማሻሻል እንዲችሉ 30 በመቶ ጊዜያቸውን በተቋሙ፤ ቀሪውን 70 በመቶ ደግሞ የተግባር ክሂሎታቸውን ያዳብሩ ዘንድ በኢንዱስትሪ እንዲያሳልፉ የተቀናጀ የስልጠና ዘዴ እንዲካሄድ ይደረጋል። ማለትም “የተቀናጀ ስልጠና” ይሰጣል።
ጉዳዩን በተመለከተ የተዘጋጀው “ብሄራዊ የልማት ሰነድ” እንደሚለው፣ የተቀናጀ ስልጠና ማለት በቴክኒክና ሙያ ተቋማትና በኢንዱስትሪ የሥራ ቦታዎች በጋራ ስልጠና በመስጠት ላይ የሚያተኩር የትብብር ሞዴል ነው፡፡ ይህ አሰለጣጠን ሰልጣኞች ሙሉ በሙሉ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ከሚሰጠው ስልጠና ይለያል፡፡ የተቀናጀ ስልጠና የሥራ ቦታ ሁኔታን በቅርበት እንዲያውቁ ከማድረግ በተጨማሪ ስልጠናው አግባብነቱ የተረጋገጠ፣ የተሟላና ዘላቂነት ያለው እንዲሆን ያደርጋል፡፡ አሁን ባለው መስፈርት ሰልጣኞች 70 በመቶ ስልጠናቸውን በኢንዱስትሪ ማግኘት ቢኖርባቸውም ይህ በስፋት ተግባር ላይ አልዋለም (ወይም ስለመዋሉ ትክክለኛ መረጃም አልተገኘም)፡፡ ለዚህ አንዱ ምክንያት፣ ተቋማቱ በኢንዱስትሪው በቂ የስልጠና ቦታ ማግኘት አለመቻላቸው ነው፡፡ በቂ የስልጠና ቦታ ለማግኘት ይችሉ ዘንድ ተቋማቱ ፊታቸውን ወደ መካከለኛ ሴክተር ኢንተርፕራይዞች ማዞር ይኖርባቸዋል፡፡ እነዚህ ኢንተርፕራይዞች ብዙ ሰልጣኞች ሊፈጥሩ የሚችሉ ከመሆናቸው በተጨማሪ ወደፊት ብዛት ያላቸው የቴክኒክና ሙያ ምሩቆች የሚሰሩባቸው ቦታዎች ይሆናሉ፡፡
የመካከለኛ ሴክተር ኢንተርፕራይዞች በኢኮኖሚ ልማት፣ በሥራ ፈጠራና ድህነትን በመቀነስ ሊኖራቸው የሚችለው ሚና በብሄራዊ የልማት ሰነዱ ተዘርዝሯል፡፡ ኢንተርፕራይዞቹ እንዲፈጠሩና እንዲያድጉ ስትራቴጂዎች ተነድፈዋል፡፡ ከእነዚህ ስትራቴጂዎች አንዱ ነሐሴ 2003 ዓ.ም የተጀመረው በቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚገኙ አሰልጣኞች ለኢንዱስትሪዎች የሚሰጡት የኤክስቴንሽን አገልግሎት ነው፡፡ ይህ አገልግሎት መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን በጥራትና በምርታማነት ለመርዳት የተዘጋጁ አራት ፓኬጆች ያሉት ሲሆን፤ እነርሱም የቴክኖሎጂ አቅም መገንባት፣ የቴክኒክ ክህሎት ማሳደግ፣ ኢንተርፕረነርሺፕ አቅም ግንባታ እና የካይዘን አቅምን ማሳደግ ናቸው፡፡
ከተጠቀሰው ኤጀንሲ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ በሀገሪቱ ከ462 በላይ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ማእከላት ያሉ ሲሆን፤ 62 ወደ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተሸጋግረዋል፤ አድገዋል። ዘርዘር አድርገን ስንመለከተው ደግሞ የሚቀጥሉትን አሃዞች (አሁን ጨምረዋል ተብሎ ይታሰ ባል) እንመልከት።
ከላይ በጠቀስነው የትምህርት ሚኒስቴር ሰነድ ላይ እንደተገለጸው፣ በ2006 ዓ.ም 1ሺህ 348 የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛዎች (የታቀደው 1074 ነበር) የነበሩ ቢሆንም፣ በሙሉ አቅም (እስከ ከፍተኛው ደረጃ 5) የሚያሰለጥኑት 334 የመንግሥትና 282 የግል ብቻ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ 732 (325 የመንግሥት፣ 407 የግል) ተቋማት አጫጭር ስልጠናዎችን (ለምሣሌ በ2006 ዓ.ም የአጭር ጊዜ ስልጠና የወሰዱ ተማሪዎች ቁጥር 1ሚሊዮን 955ሺህ 826 ነበር) ብቻ የሚሰጡ ናቸው (አንዳንዶቹ እስከ ደረጃ 2 ስልጠናንም ይሰጣሉ)፡፡
ስልጠናዎቹም ወደ አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች የተደረገው የቴክኖሎጂ ሸግግር ቁጥርም ከፍ እንዲል የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ለዚህ ጽሑፍ ግብአት ይሆኑን ዘንድ የተጠቀምንባቸው መረጃዎች ያመለከታሉ።
አዲስ አበባን በማሳያነት ወስደን እንመልከት።
በዚሁ በያዝነው አመት (ኅዳር 7 ቀን 2016 ዓ.ም) በሚመለከታቸው አካላት እንደ ተገለጸው፤ በአዲስ አበባ ከተማ 15 የመንግሥትና 114 የግል፤ በድምሩ 129 የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ኮሌጆች ይገኛሉ። በእነዚህ ኮሌጆች ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማሠልጠን በቂ ዝግጅት ተደርጓል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ቢሮ እንዳስታወቀው፤ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው አዲሱ የትምህርት ሥልጠና ፖሊሲ መሰረት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትን የመግቢያ ነጥብ ያስመዘገቡ 33ሺህ 766 ተማሪዎችን ተቀብለው በማሰልጠን ላይ ይገኛሉ።
ከሥራ ደረጃዎች አኳያም ቴክኒክና ሙያ የራሱ የሆኑ ባህርያት ያሉት ሲሆን፤ የሚከተለው በተለይ ይገልጸዋል ተብሎ በባለሙያዎች ይነገራል (ከእነዚህ ደረጃዎች አብዛኛዎቹ ከሌሎች ሀገሮች በቀጥታ የተወሰዱ ቢሆንም፤ በተቻለ መጠን የሀገራችን የኢንዱስትሪው ዘርፍ ኤክስፐርቶች ደረጃዎቹን በመፈተሽና በማጽደቅ ሂደቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ፤ እንዲሁም፣ ከብሄራዊው የቴክኒክና ሙያ የደረጃ መስፈርቶች ጋር እንዲተሳሰሩ ማድረግ ተገቢ መሆኑ ይመከራል)፤
የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ንዑስ ዘርፍ OSን (የሥራ ደረጃ) በመነሻነትና በማጣቀሻነት የሚጠቀም ውጤት ተኮር አሠራርን ይተገብራል፡፡ የሥራ ደረጃዎች (OS) በሥራ ቦታ ያለውን እውነታና ፍላጐት የሚያመላክቱና በየኢንዱስትሪው ባሉ በኤክስፐርቶች የሚጠኑ እንደመሆናቸው የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎች በፍላጐት ላይ በመመስረት ውጤት ተኮር ሆነው የመደራጀታቸው ጉዳይ እንደ ማዕዘን ድንጋይ ተደርጐ ይወሰዳል፡፡ የዚህ ዓይነት አደረጃጀት የመማር- ማስተማር ሂደቱ እንደ አስፈላጊነቱ እንዲስተካከል ስለሚፈቅድና በጊዜና በቦታ ስለማይወሰን፣ የብቃት እውቅና ችግር የለበትም፡፡ ስለሆነም መደበኛና መደበኛ ያልሆነ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠናን በማዋሃድ ሀገሪቱ ያላትን ሰፊ የስልጠና አቅም በጥቅም ላይ ማዋል ያስችላታል፡፡ በሥራ ላይ የተሰማራው የሰው ኃይልም የክህሎት ብቃቱን በማጥናትና ክፍተቶቹን በመለየት፣ በልዩ ትኩረት ፕሮግራሞችን አዘጋጅቶ በማሰልጠን የኢንዱስትሪ ውጤታማነት እና ጥራት እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ (ትምህርት ሚኒስቴር፣ ገጽ 40)
ከጥናትና ምርምር አኳያ፣ የምርምር አጀንዳዎችን መለየትና የፕሮጀክት ዲዛይኖች ምርጫ ወደፊት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች መሆናቸው፤ የሚካሄደው ምርምር በትምህርትና ሙያ ስልጠና ተቋማዊ አሠራርና በገበያ ፍላጐት መካከል ባለው ግንኙነት ላይ በማተኮር የሙያ ትምህርቱና ስልጠናው ወደፊት የሚሻሻልበትን መንገድ ተንትኖ ማሳየት የሚችል መሆን እንዳለበትና የመሳሰሉት በባለሙያዎች ከሚሰጡ ምክሮች መካከል ናቸው።
በላሃ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ (ባለፈው ዓመት በጎፋ ዞን ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መምሪያ 1ኛ ደረጃ የላቀ አፈፃፀም ተሸላሚ ኮሌጅ ነው) መምህር የሆኑት በረከት ሰጉ በኮሌጂ ድረ- ገጽ ላይ በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የመማር 10 ጥቅሞችን እንደሚከተለው በመዘርዘር ያብራሯቸዋል።
- የተግባር ክህሎት፡- የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ተማሪዎች በመረጡት የሥራ መስክ ላይ በቀጥታ የሚተገበሩ የተግባር ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ የሚረዳ የተግባር ስልጠና ይሰጣሉ። ለምሳሌ የብየዳ ትምህርትን የሚያጠና ተማሪ የተለያዩ ቴክኒኮችን እና መሳሪያዎችን በመጠቀም የተለያዩ ዲዛይኖች እንዴት እንደሚገጣጠሙ ይማራል።
- ኢንዱስትሪ-ተኮር ዕውቀት፡- የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በባህላዊ የትምህርት መርሀ ግብሮች ያልተማሩትን በኢንዱስትሪ ተኮር ዕውቀት ለተማሪዎች የሚሰጡ ልዩ ኮርሶችን ይሰጣሉ። ለምሳሌ፣ የአውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂን የሚያጠና ተማሪ ስለ መኪና ሞተሮች የቅርብ ጊዜ ግስጋሴዎች እና እንዴት መጠገን እንዳለበት ይማራል።
- የሥራ ምደባ እገዛ፡- ብዙ የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች ለተመራቂዎቻቸው የሥራ ምደባ እገዛ ይሰጣሉ። ይህ ተማሪዎች በመረጡት የሥራ መስክ በፍጥነት እና በቀላሉ ሥራ እንዲያገኙ ያግዛቸዋል።
- ተለዋዋጭነት፡- የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች ተማሪዎች ትምህርታቸውን ከሥራ እና ከሌሎች ኃላፊነቶች ጋር ማመጣጠን እንዲችሉ ተለዋዋጭ የጊዜ ሰሌዳዎችን ያቀርባሉ።
- ወጪ ቆጣቢ፡- የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ብዙ ጊዜ ከባህላዊ የአራት ዓመት ዩኒቨርሲቲዎች የበለጠ ወጪ ቆጣቢ ናቸው። ይህም ለከፍተኛ ትምህርት ወጪ ለሚጨነቁ ተማሪዎች የበለጠ ተደራሽ ያደርጋቸዋል።
- አጫጭር ፕሮግራሞች፡- የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ፕሮግራሞች ከባህላዊ የአራት ዓመት የዩኒቨርሲቲ ፕሮግራሞች ያነሱ ናቸው። ይህም ማለት ተማሪዎች በፍጥነት ወደ ሥራ ኃይል መግባት ይችላሉ። ለምሳሌ፣ ዳታ ቤዝ ዴቨሎፕ የሚያደርግ (የሚያበለፅግ) ተማሪዎች ፕሮግራማቸውን በሁለት ዓመት ውስጥ ማጠናቀቅ ይችላሉ።
- የተግባር ልምድ፡- የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ለተማሪዎች በተለያዩ መስኮች ለስኬታማነት አስፈላጊ የሆነ የተግባር ልምድ እንዲያገኙ ይደረጋል። ለምሳሌ፣ የምግብ አሠራር ጥበብን የሚማር ተማሪ በትልቅ ሆቴል ውስጥ ለመሥራት እና ለደንበኞች ምግብ የማዘጋጀት ልምድ ያገኛል።
- በሙያ ላይ ያተኮረ ትምህርት፡- የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ተማሪዎችን የተለየ ሥራ ማዘጋጀት ላይ ያተኮረ ትምህርት ይሰጣሉ። ይህ በተለይ ከተመረቁ በኋላ ምን ማድረግ እንደሚፈልጉ ግልጽ ግንዛቤ ላላቸው ተማሪዎች ጠቃሚ ነው።
- ተግባራዊ ሥርዓተ ትምህርት፡- የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ሥርዓተ ትምህርት የተነደፉት ተግባራዊ እና በገሃዱ ዓለም ሁኔታዎች ላይ ተፈፃሚ እንዲሆኑ ነው። ይህ ተማሪዎች በመረጡት መስክ ስኬታማ ለመሆን የሚያስፈልጋቸውን ክህሎቶች እና እውቀቶች እንዲያዳብሩ ይረዳል።
- ለግል የተበጀ ትኩረት፡- የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች ብዙ ጊዜ አነስተኛ የክፍል መጠኖችን ይሰጣሉ፣ ይህ ማለት ተማሪዎች የበለጠ ግላዊ ትኩረት ከአስተማሪዎቻቸው ያገኛሉ። ይህ በተለይ ተጨማሪ ድጋፍ ወይም መመሪያ ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች ጠቃሚ ነው።
ባጠቃላይ፣ ሀገራችን እየታተረች የምትገኘው ከድህነት መውጣት ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን መሥራት ላይ ነው። ከድህነት መውጣት ደግሞ እንዲህ እንደምናወራው ቀላል አይደለምና በርካታ የሙያ፣ የእውቀት፣ የክሂል፣ የግንዛቤ፣ የአሰራር፣ የአመራር ወዘተ ዘርፎችና ተግባራትን በእጅጉ ይሻል። ከእነዚህ መካከል አንዱ ቴክኒክና ሙያ ስለ መሆኑ መከራከርም ሆነ መጠራጠር አይቻልምና ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ፣ ማላቅ ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የመጀመሪያው የቲንክ ታንክ (Think Tank Group) ቡድን መቋቋሙ፤ ቡድኑም ቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሃሳብ አመንጪዎች ከመላው ዓለም በተሰባሰቡ ከፍተኛ ልምድና ዕውቀት ያለቸው ሰዎች ማካተቱ፤ ቡድኑ በዘርፉ የፖሊሲ አተገባበር ሂደት ሃሳብ በመስጠት፣ ልምዶችን በማካፈል፣ የውይይት ባህል በማዳበርና በዘርፉ ቅንጅታዊ አሠራር ለመተግበር ያስችላል የሚል እምነት የተጣለበት መሆኑ፤ ይህም የሀገሪቱን የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ጥራት ለማስጠበቅ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ መታመኑ እና የመሳሰሉት ያለ ምክንያት አይደለምና ዘርፉ የሁላችንንም ድጋፍና ትብብር ይፈልጋል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም