በሆሳዕና ከተማ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ ነው

– የ5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራም ተጀምሯል

አዲስ አበባ፡- ከሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆኑን የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ዳዊት ጡምደዶ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በከተማዋ በተያዘው ዓመት ከሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡

25 ኪሎ ሜትር አስፓልት መንገድ፣ በ286 ሚሊዮን ብር ሁለት የንፁሕ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች፣ የሁለት ትምህርት ቤቶችና ሁለት ጤና ጣቢያዎች ግንባታ፣ የሕዝብ መዝናኛ ሥፍራዎች፣ ድልድዮችና የመንገድ አካፋይ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡

ከተጠቀሱት ፕሮጀክቶች ውስጥ በ60 ሚሊዮን ብር የሚሠራው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቋል ያሉት ከንቲባው፤ ሁለተኛው የውሃ ፕሮጀክት ግንባታም ከ85 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ የከተማውን የንጹሕ መጠጥ ውሃ ፍላጎት 85 በመቶ ያሟላሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የውሃ መፋሰሻ ቦይ ሥራዎች፣ የአረንጓዴ ልማትና የውስጥ ለውስጥ መንገድ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተው፤ የከተማዋን የፅዳት ለማስጠበቅም ከልማታዊ ሴፍትኔት ጋር በማስተሳሰር እየተሠራበት ይገኛል፡፡ ማኅበረሰቡን በማስተባበርም አካባቢያውን እንዲያለማና የየአካባቢውን ፅዳት እንዲጠብቅ እየተደረገ ነው፡፡

ከከተማዋ የሚሰበሰበው ቆሻሻ ሀብት መሆኑን በመገንዘብ መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

እነዚህ የልማት ሥራዎች ሲከናወኑ ማኅበረሰቡ የሚያደርገው ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይነትም የከተማዋን የገቢ መሰብሰብ አቅም በማሳደግና የኅብረተሰቡን ተሳትፎ በማጠናከር ከተማዋን ለማልማት ይሠራል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ከአዲስ አበባ ከተማ ተሞክሮ በመውሰድ የአምስት ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ለመሥራት ታቅዷል ያሉት አቶ ዳዊት፤ አሁን ላይ አንድ ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ ተጀምሯል። በቀጣይነትም ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

የሆሳዕና ከተማን የኮሪደር ልማት ከሌሎች ከተሞች የሚለየው ኅብረተሰቡ በተቀመጠው ፕላን መሠረት በፈቃደኝነት ያለምንም የካሣ ክፍያ ቤትና ንብረቱን አፍርሶ ማንሳቱ ነው ያሉት ከንቲባው፤ የኮሪደር ልማቱ የእግረኛ መንገዶችን፣ አረንጓዴ ልማትና ሌሎችንም አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች ያሟላ ነው፡፡

በአጠቃላይ ከተማዋን ለኑሮ ምቹና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ መዳረሻ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በከተማዋ ለባለሀብቶች የሚሆን የመሬት አቅርቦትና ሌሎችም አስፈላጊ ድጋፎች ይደረጋሉ፡፡ ባለሀብቶች ወደ ከተማዋ መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱም ጥሪ አቀርበዋል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You