ሰላምና ልማት የተረጋገጠበት ሸካ ዞን

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ውስጥ ከሚገኙ ስድስት ዞኖች አንዱ ሸካ ዞን ነው። በዞኑ ሦስት ወረዳዎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች ይገኛሉ። የሸካ ዞን ዋና ከተማ ደግሞ ቴፒ ናት። በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ክላስተር ከተሞች ተብለው ከተለዩት መካከልም ተጠቃሽ ናት።

ሸካ ዞን በተፈጥሮ ፀጋ የታደለ፤ በሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት ላይ ከፍ ያለ ሚና ያለው እምቅ የሆነ ሀብት የሚገኝበት አካባቢ ነው። በግብርናው ዘርፍ የቡና ልማት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። በግብርናና በቱሪዝም ለመሠማራት የሚያስችሉ ምቹ የኢንቨስትመንት እድሎች ያሏት ዞን እንደሆነች መረጃዎች ይጠቁማሉ። ዞኑም ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ባለሀብቶችን በተለያየ መልኩ በማበረታታት ላይ ይገኛል፡፡

ሸካ ዞን በተለይም ቴፒ ከተማ ከሦስት ዓመታት በፊት አካባቢው ላይ ሁከትና ግርግር እንደነበር አይዘነጋም። ሆኖም ችግሩ ሥር ሳይሰድ ዞኑ የሀገር በቀል እውቀት በመጠቀም አካባቢያዊ ሰላም ማረጋገጥ ችሏል። ዛሬ ላይ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በዞኑ ልማትና እድገት ለማምጣት እንቅስቃሴው ተጠናክሯል፡፡

በዞኑ በአንድ ወቅት አጋጥሞ ስለነበረው የፀጥታ መደፍረስና ችግሩንም በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር ስለተደረገው ጥረት፣ ዘላቂ የሆነ ሰላም ለማረጋገጥም በቀጣይ ስለተቀመጡ አቅጣጫዎች እንዲሁም በልማት ዙሪያ ስለተሰሩ ስራዎች ከሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ ጋር ቆይታ አድርገናል። ውድ አንባቢዎችም መልካም የንባብ ጊዜ ይሁንላችሁ፡፡

አዲስዘመን፦ በቅድሚያ አካባቢው ላይ ተፈጥሮ ስለነበረው የጸጥታ መደፍረስና ችግሩን ለመፍታት ስለተወሰደው ርምጃ ቢያብራሩልን?

አቶ አበበ፦ አካባቢው ላይ ተፈጥሮ ስለነበረው የሰላም እጦት ስናነሳ ፤ሀገራዊ ለውጥን ተከትሎ በመላ ሀገሪቱ ማለት በሚቻል ደረጃ ለውጥ አደናቃፊ ቡድኖች የጀመሩት ሥራ እንደነበር ይታወቃል። እነዚ የለውጥ አደናቃፊ ቡድኖችም ግርግርና ሁከት እንዲፈጠር በሰፊው ተንቀሳቅሰዋል።

በነዚህ የለውጥ አደናቃፊዎች እንቅስቃሴ የሰላም እጦት ከታየባቸው አካባቢዎች አንዱ ሸካ ዞን ሲሆን፤ ከዞኑ ደግሞ የበለጠ ችግሩ ጎልቶ የተስተዋለው ቴፒ ከተማና የኪ ወረዳ አካባቢ ነው። በነዚህ አካባቢዎች የተፈጠረው ችግርም ብዙ ኪሳራ አስከትሏል። የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፤ በችግሩ ሰዎች ከቀዬያቸው ተፈናቅለዋል። የለውጥ አደናቃፊዎቹ ያስከተሉት ኪሳራ እንደዞንም ተገምግሟል። በአጠቃላይ ችግሩ ሀገራዊ ለውጥን ተከትሎ የመጣ ነው ብዬ ነው የምወስደው።

ችግሩ ብዙ ጉዳት ቢያደርስም፤ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል። አካባቢው በኮማንድ ፖስት እንዲተዳደር ተደርጓል። የፀጥታ ኃይሉም ሰላም ለማስፈን ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል። በዚህ አጋጣሚ የፀጥታ ኃይሉን ጥረት ልናደንቅና ልናመሰግን ይገባል። አካባቢው ላይ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ከተለመደው የመንግሥት የአስተዳደር መዋቅር ወጣ ባለ የሀገር በቀል እውቀትን መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ ስለታመነበት እቅድ ተይዞ በዚህ መልኩም ጥረት ተደርጓል።

በወቅቱ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ግለሰብ ከግለሰብ፣ መንደር ከመንደር፣ ቀበሌ ከቀበሌ፣ ወረዳ ከወረዳ መሻከሮች ተፈጥረው ስለነበር ይህን ደግሞ ማስተካከል የሚቻለው ሀገር በቀል እውቅትን በመጠቀም ነው። ይህን አካሄድ ለመከተልም ከአካባቢው ነዋሪ ጋር የተስማማነው የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የተካተቱበት የሰላም አፈላላጊ ኮሚቴ በማዋቀር መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ነው። በዚሁ መሠረትም ችግር ባለባቸው ቀበሌዎች የሰላም አፈላላጊ ኮሚቴ አዋቀርን። ከነዚሁ ኮሚቴዎች ውስጥ የተውጣጡ ወረዳዊና ዞናዊ የሰላም ኮሚቴ በማዋቀር ነው ወደ ሥራ የተገባው። ሁሉም እቅድ ነድፈው ነው ወደ ሥራ የገቡት፡፡

ኮሚቴውም ወደ ሥራ ሲገባ፤ የተፈጠረው ግጭት ማህበረሰቡ ፈልጎት የመጣ ሳይሆን፣በህብረ ብሄራዊነት፣ በአንድነት አብሮ በኖረ ማህበረሰብ መካከል ቁርሾ እንዲከሰት ማድረጉንና ነገሩም በዚህ መቀጠል እንደሌለበት አጀንዳ ይዞ የፈጠረው ቁርሾና መሻከር በመታረቅ ተፈትቶ ሕዝቡ ወደቀደመው አንድነቱና አብሮነቱ እንዲመለስ ተደርጓል።

በዚሁ መሠረትም የተጣሉ እንዲታረቁ አደረገ። ሰላም አፈላላጊው ኮሚቴ ከአቅሙ በላይ የሆኑ ጉዳዮች ሲያጋጥሙት ለወረዳ በማሳወቅ ጭምር ባደረገው ጥረት ግጭት በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ችሏል። በሰላም እጦት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት ተፈትቶ ማህበረሰቡ እፎይታ እንዲያገኝ አደረገ፡፡

ሌላው በፀጥታው ምክንያት አጋጥሞ የነበረው ተግዳሮት፤ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሽፍታ የሆኑ ሰዎች ጉዳይ ነበር። እነዚህ ሰዎች ታጥቀው ጫካ ውስጥ ገብተው የሰላማዊውን ሰው ህይወት የሚያውኩ ነው የነበሩት። ሰላም አፈላላጊ ኮሚቴው እነዚህ ሰዎች ከገቡበት ጫካ እንዲወጡ፣ ትጥቃቸውንም እንዲፈቱ፣ የማድረግ ተልእኮ ጭምር ይዘው ነበር ለሰላም ሲንቀሳቀሱ የነበረው። ሰላም አፈላላጊ ኮሚቴው በቅድሚያ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ነበር ውይይት ያደረገው። በውይይቱም ድርጊታቸው ለራሳቸውም ሆነ ለአካባቢው አልፎ ተርፎም ለሀገር የሚጠቅም እንዳልሆነ ነበር ኮሚቴው አንስቶ የተነጋገረው።

በዚህ መልኩ ውይይቶች ተደርገው ታጥቀው ጫካ ከገቡት አካላት ጋር ድርድር ማድረግ ሲጀመር፤ በሸፈቱት አካላት የነበረው ቅድመ ሁኔታ ከጫካ ወጥተው መሳሪያቸውን አስረክበው እጃቸውን ቢሰጡ ችግር እንደማይደርስባቸውና እንደማይታሰሩ ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው ነበር። የዞኑ ዋና ዓላማና ግብ እርቅ በመፈፀም ሕዝቡን እንድ አድርጎ የአካባቢውን ሰላም ማረጋገጥ እንደሆነ ማረጋገጫ ተሰጠ። በዚህ መልኩ መግባባት ከተፈጠረ በኃላ ታጥቀው ጫካ የገቡ ለሰላም ዝግጁነታቸውን በማሳየት ተመለሱ። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ነበር መመለስ የተቻለው።

በዚህ አጋጣሚም በኃላፊነት ተልእኮአቸውን የተወጡትን የሰላም አፈላላጊ የኮሚቴ አባላትን በዞኑ ስም ማመስገን እፈልጋለሉ። ጫካ ውስጥ ገብተው ነበር ውይይትና ድርድሩን ሲያደርጉ የነበረው። በጥፋት ውስጥ የነበሩትም ከፖለቲካ አመራሩ ይልቅ የሀገር ሽማግሌዎችንና የኃይማኖት አባቶችን ያከብሩ ስለነበርም ሊታዘዟቸው ችለዋል።

በወቅቱም የሄዱበት ርቀት ጥፋት እንደሆነ፣ የሰላም አፈላላጊ ኮሚቴ፣ የፖለቲካ አመራሩና የፀጥታ ኃይሉ ፊት ቀርበው ነበር ይቅርታ የጠየቁት። ጉዳት ያደረሱበት አካባቢ ድረስ በመሄድም ነዋሪዎችን በተመሳሳይ ይቅርታ ጠይቀዋል። እንዲህ ባለው ተግባር አጥፊዎችን ከጥፋታቸው መመለስ ከመቻሉ በተጨማሪ ለጥፋት ይውል የነበረን መሳሪያም መሰብሰብ ተችሏል፡፡

ሸፍተው ጫካ የገቡትን ከማስመለስ ጎን ለጎን፤ በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት በህግ ቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ ተደርጎባቸው፣ ከስ ቀርቦባቸው በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ በእስር ላይ የነበሩትም እንዲፈቱ ነው የተደረገው። ይህም የሆነው በሰላም አፈላላጊ የኮሚቴ አባላት ጥያቄ ቀርቦ ነው፡፡

ኮሚቴው በእስር ላይ የሚገኙትም ቢሆኑ በማወቅም ባለማወቅም የተሳተፉ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሃሳብ በማቅረብ ነው። የእስረኞቹ መፈታት በአካባቢው ላይ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት ሙሉዕ እንደሚያደርገው እምነት ስላደረባቸውም ጭምር በመሆኑ ነው ጥያቄውን ያቀረቡት፡፡

እንደመንግሥትም ሃሳቡ ሰፋ ተደርጎ እንዲታይ ተደርጓል። ለክልሉ መንግሥትም ቀርቦ በክልሉ ፍትህ መዋቅር በኩል እስረኞቹ ይፈቱ የሚሉ ወይንም የሚደግፉ አካላት መለየት እንዳለባቸው ሀሳብ ቀረበ። ይህን መነሻ በማድረግ በተከናወነው ተግባርም ወደ 10ሺ የሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች እስረኞቹ እንዲፈቱ በፊርማቸው አረጋገጡ። የዞኑ አስተዳደርም ይህንኑ ለክልሉ አስተዳደር አቀረበ። ክልሉም ለፌዴራል ፍትህ ሚኒስቴር አቀረበ።

ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ የበዳይና ተበዳይ ሁኔታ ላይ ትኩረት እንዲሰጠው ነበር ሃሳብ የሰጠው። እርቅ ሳይፈፀም እስረኛው እንዲወጣ ከተደረገ ሌላ ችግር እንዳይፈጠር ነበር ሚኒስቴሩ ስጋቱን ያስቀመጠው። በተበዳይና በዳይ መካከል ሰላም እንዲሰፍንም የሰላም አፈላላጊ ኮሚቴው ሥራ ሠርቷል።

በዚህ መልኩ ሥራ መሠራቱንም የፌዴራል ፍትህ ሚኒስቴር በስፍራው ላይ ባለሙያዎችን ልኮ ያለውን እውነታ አረጋግጧል። ጉዳዩንም በሚኒስቴሩ በሚገኘው የይቅርታ ቦርድ በማቅረብ ጭምር ነው እስከመጨረሻው የተከታተለው። ከዚህ ሁሉ ሂደት በኃላ ወደ 56 እስረኞች በይቅርታ ከእስር ተፈቱ። ከእስር ከተፈቱት ጋርም በተደረገው ንግግር በሰሩት ሥራ መፀፀታቸውን፣ከእስር እንዲፈቱ የተደረገውንም ጥረት አድንቀው፣ በሰላምም ሆነ በልማት ሥራ ከመንግሥት ጎን እንደሚቆሙ በመግባባት ነው ከህብረተሰቡ ጋር የተቀላቀሉት።

ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሀገር በቀል እውቀት መሄድ ይሻላል የምንለው ውጤቱን በማየት ነው። በአንድ በኩል የታጠቀውን ኃይል መመለስ በመቻሉ የእኔ ልጅ ጫካ  ውስጥ ሆኖ ሊሞት ይችላል የሚል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከማረሚያ ቤት ታራሚ እንዲፈታ በመደረጉ ልጄ እስር ቤት ውስጥ ነው ብሎ የሚያዝን ቤተሰብ እንዳይኖር ማድረግ ተችሏል። ሁሉም ዜጋ በሰላም የሚኖርበት፣ ሰርቶ የሚገባበት አካባቢ ለመሆን ችሏል። በቅርቡም የአካባቢ የፀጥታ ሁኔታን በተመለከተ ባደረግነው ግምገማ ከተማው ላይ ይስተዋል የነበረው ንጥቂያና ዝርፊያ ሁሉ ሳይቀር መሻሻል እንዲታይ አስችሏል። በአጠቃላይ አካባቢው ላይ ሰላም ተረጋግጧል፡፡

አዲስዘመን፦ በብዙ ጥረት የተረጋገጠው ሰላም፤ ለልማቱ ያበረከተው አስተዋጽኦ እንዴት ይገለጻል?

አቶ አበበ፦ ሰላም ለልማትም ሆነ ለዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ፣ ለሁለተናዊ ብልጽግና ወሳኝ እንደሆነ ይታወቃል። ሸካ ዞን ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ የተፈጥሮ ፀጋም ያለው፤ ለሀገር የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት የኤክስፖርት ምርት ኮሪዶር ነው። ዞኑ 238ሺ ሄክታር ቆዳ ስፋት ያለው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 85ሺ ሄክታር መሬት ላይ ቡና ይለማል፡፡ወደ 64ሺ ሄክታር የሚሆነው መሬት ደግሞ ምርት ይሰጣል።

የቡና ልማቱም በአርሶ አደርና በባለሀብት እየለማ ሲሆን፤ ወደ 17ሺ ሄክታር የሚሆነው መሬት በባለሀብቶች እየለማ ነው። በልማቱ ከተሰማሩት 46 ኩባንያዎች ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ከሜድሮክ እህት ኩባንያዎች አንዱ የሆነው በዞኑ አድራቻ ወረዳ ውስጥ የሚገኘው አግሪስፍት የተባለው ድርጅት ይጠቀሳል፡፡ማሻ ወረዳ ላይ ኃይሌና ዓለም፣ ቴፒ ላይ ግሪን ኮፊ ኩባንያዎች ትልቅ ኢንቨስትመንት ናቸው። ኩባንያዎቹ ለዓለም ገበያ የሚቀርብ ደረጃውን የጠበቀ ቡና ነው የሚያመርቱት።

በአጠቃላይ ከአካባቢው በዓመት እስከ 20ሺ ቶን ቡና ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ ይቀርባል። ከቅመማ ቅመም አንጻር ደግሞ ለልማቱ የሚውል ወደ 15ሺ ሄክታር መሬት ይገኛል። በዓመት እስከ 23ሺ ቶን ቅመማቅመም ለማእከላዊ ገበያ ይቀርባል። በማር ምርትም እስከ 28ሺ ቶን ለገበያ ይቀርባል። በዞኑ በሀገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ ትልቅ አበርክቶ ያለው የልማት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። የቱሪስት መዳረሻ የሆኑ ፏፏቴዎች፣ ሀይቆች፣ ዋሻ አለው። በኢትዮጵያ በደን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) ከተመዘገቡ አንዱ የሸካ ዞን ነው፡፡

የፀጥታ መደፍረሱ በነዚህ የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ የራሱ የሆነ ተጽእኖ ያሳደረ ቢሆንም፤ ሰላም ከተፈጠረ በኃላ የነበረውን በማነቃቃትና አዳዲስ ኢንቨስትመንትንም በመሳብ በርብርብ እየተሰራ ይገኛል። በአሁኑ ጊዜም በሆቴል ኢንደስትሪ የተሰማሩ አራት ባለሀብቶች በግንባታ ሥራ ላይ ናቸው። የሆቴል ግንባታው ክልሉ በአዲስ መልክ ከተደራጀ በኋላ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ ከገቡ መካከል ይጠቀሳል።

የማደያ ግንባታውም ሌላው የግንባታ ዘርፍ ነው። በከብት እርባታ ላይ ለመሰማራት ባለሀብቶች ፈቃድ ወስደዋል። ለግንባታ የሚሰጠው ቦታም ባለሀብቱን የሚያበረታታ መሆኑ ትኩረት ይደረጋል። ሥራዎች በዚህ መልኩ እየተከናወኑ ቢሆንም የበለጠ ፈጥኖ መሥራት ላይ እንደሚቀረን በግምገማ ለይተናል። የተሻለ አፈፃፀም እንዲኖረን በክትትልና ድጋፍ የበለጠ እንሠራለን፡፡

በገጠር ኢንቨስትመንትም እንዲሁ ቀድመው ወደ ሥራ የገቡት ያለምንም ስጋት ተጠናክረው በመሥራት ምርታቸውንም ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ(ኢሲኤክስ) በዞኑ ቅርንጫፍ በመክፈቱም ጥራት ያለው ምርት ለገበያ እንዲቀርብ አስተዋጽኦ አበርክቷል። የአርሶአደሩም ምርታማነት ከመቸውም ጊዜ በበለጠ መሻሻል አሳይቷል። የኪ ወረዳ ላይ ብቻ በበልግ ወደ ዘጠኝ ሺ ሄክታር የበቆሎ ምርት መሰብሰብ ተችሏል። ለምርትና ምርታማነት እድገት የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ የታየው ለውጥም አበረታች ሆኖ ነው የተገኘው። ይሄ ሁሉ የሰላም ውጤት ነው፡፡

አዲስዘመን፦ ዞኑ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት የሚውሉ ሀብቶችን በውስጡ መያዙን ገልጸውልናል። ይሄን የሚመጥን የመሠረተ ልማት አለው ማለት ይቻላል?

አቶ አበበ ፦ሸካ ዞን በመንገድ መሠረተ ልማት የተጎዳ አካባቢ ነው። በተለይም ባለፈው ሥርዓት በመሠረተ ልማት ያልታየ አካባቢ ነው። የአስፓልት መንገድ የሚባል አልነበረም። ከጅማ፣ቦንጋ፣ ሚዛን ላይ ያለው አስፓልት 50 ኪሎ ሜትር ላይ ነው የቆመው። በኦሮሚያ ከኢሊባቦር ዞን የመጣው አስፓልት ጎሬ ላይ አሁንም ማሻ ላይ 50 ኪሎ ሜትር ላይ ነው የቆመው። ይሄን ስናይ ዞኑ ላይ አስፓልት እንዳይሰራ የተገደበ ነው የሚመስለው፡፡

ከሀገራዊ ለውጥ በኋላ ግን ለውጥ ማየት ጀምረናል። ከኦሮሚያ ክልል ኢሊባቦር ዞን ከጎሬ ማሻ ቴፒ 141 ኪሎ ሜተር ኮንክሪት አስፓልት መንገድ፣ ከሚዛን ቴፒ 50 ኪሎ ሜትር አስፓልት መንገድ፣ ከሺሽንዳ ቴፒ (ከቦንጋ ወደ ሚዛን) 74 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ሥራ የተጀመረው በአዲሱ መንግስት ነው።

ይሄ መልካም ሆኖ ሳለ ግን አፈፃፀም ላይ ጉድለቶች አሉ። የጎሮ ማሻ ኮንክሪት አስፓልት መንገድ ሥራ ከአራት አመት በፊት ነው የተጀመረው። አስፓልት የማልበስ ሥራ ቢጀመርም ሥራው አጥጋቢ ነው ማለት አይቻልም። ፕሮጀክቱ ተጓቷል። ትኩረት ያስፈልጋል። በተለይም የሺሽንዳ ቴፒ መንገድ ሥራ ወደኃላ ቀርቷል። አስፓልት የለበሰው ከ10 ሊሎሜትር አይበልጥም። የሥራውን መጓተት በተመለከተም ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ጥያቄ አቅርበናል።

ኮንትራክተሩ (ተቋራጩ) የአቅም ማነስ እንዳለበት ተነግሮናል ። ሥራውም ተቋርጧል። ከቴፒ ወደ ጅማ ቦንጋ ለመውጣት አቋራጩና ኪሎሜትሩ የሚቀንሰው መንገድ የቴፒ ሽሺንዳ መንገድ ነው። የዚህ መንገድ ሥራ መጠናቀቅ ወሳኝ ነው።

በአጠቃላይ የመንገድ መሠረተልማቱ ከሚያስፈልገው አንጻር ጊዜ ወስዷል። ለመንገድ ሥራ መጓተት አንደምክንያት ከሚነሳው አንዱ የካሳ ክፍያ ነው። ካሳ ክፍያ የሚፈጽመው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ነው። በዚህ በኩልም የትኩረት ማነስ ይስተዋላል።

አዲስዘመን፦ ዞኑ ባለው እምቅ ሀብት የአካባቢው ማህበረሰብ እንዲጠቀም በተለይም በአካባቢው ላይ በሚፈጠረው ኢንቨስትመንትም ሆነ የተለያዩ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር የተከናወኑ ሥራዎች ካሉ ቢገልጹልን?

አቶ አበበ፦ የፀጥታ መደፍረሱን ምክንያት አድርገው ጫካ ከገቡት ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ወጣቶች ነበሩ። በሰላም አፈላላጊ ኮሚቴ የሰላሙ ሁኔታ ከተረጋገጠ በኋላ ወጣቶቹ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ነው የተደረገው። አሁን ላይ በዶሮ እርባታ፣ ላቫይጆ(መኪና ማጠብ) ሥራ ላይ ተሰማርተው ለሌሎችም የሥራ እድል የፈጠሩ ወጣቶች በዞኑ ላይ ይገኛሉ።

የሥራ አለመኖር እራሱን የቻለ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል፣ ለፀጥታ ስጋትም አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ግንዛቤ በመያዙ የሥራ ዕድል ፈጠራው ላይ በትኩረት እየሰራን ነው። ከጫካ ተመልሰው ወደ ሥራ ከገቡት ወጣቶችም ትምህርት ተወስዷል፡፡

አዲስዘመን፦ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተነሳሽነት ከተጀመሩ የልማት ሥራዎች አረንጓዴ አሻራና የሌማት ቱሩፋት ይጠቀሳል። በዚህ ረገድ በዞኑ የተከናወኑትን ተግባራት ቢገልጹልን?

አቶ አበበ፦ የሌማት ቱሩፋት ላይ የዶሮ፣ የወተት፣ የንብ፣ የከብት ማደለቢያ መንደሮች ለይተን እየሰራን እንገኛለን። በተለይ ለንብ ማነብ በዞናችን ሁለት ወረዳዎች ውስጥ ምቹ ሁኔታ አለ። ዘመናዊ የንብ ቀፎን በመጠቀም ከፍተኛ የማር ምርት ማምረት ይቻላል። የአካባቢ አቅምን ለይቶ ማጠናከርና የሌማት ቱሩፋት ዓላማን ለማሳካት የሄድንባቸው ርቀቶች ቢኖሩም ሥራዎች ይቀሩናል።

የሌማት ቱሩፋት አንዱ ዓላማ ዜጎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ማድረግ ነው። አርሶአደሩ በዚህ መልኩ ተጠቃሚ ከሆነ በኋላ ደግሞ ከዘርፉ ገቢ በማግኘት የኢኮኖሚ አቅሙን ያሳድጋል። የሸማቹንም የኑሮ ውድነት በመቀነስ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ያበረክታል። የሌማት ቱሩፋት እንዲህ ያሉ በረከቶች አሉት።

አረንጓዴ አሻራን በተመለከተ፤ አካባቢው በራሱ በተፈጥሮ ፀጋ የታደለ በመሆኑ በአረንጓዴ የተሸፈነ ነው። ይህ መሆን የቻለው ሕዝቡ ከትውልድ ወደ ትውልድ እያሸጋገረ የመጣ የደን አጠባበቅ ባህላዊ ሥርዓት ስላለው ነው። ሕዝቡ አስጠብቆ ያስቀጠለው ሥርዓት እንዳለ ሆኖ፤ ለተለያየ ኢንዱስትሪ ግብአት የሚውሉ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውና ብዝሀ አገልግሎት ያላቸው የዛፍ ችግኞችን መትከልና መንከባከብ አስፈላጊ ነው። በሌላ በኩልም በደንነት የሚቀጠሉ ዛፎችንም መተካት ያስፈልጋል። በመሆኑም በበልጉም በመኸሩም የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር እየተተገበረ ይገኛል። ጥሩ የሚባል አፈጻጸምም ለማስመዝገብ ጥረት እያደረግን ነው፡፡

አዲስዘመን፦ በቆይታችን ያላነሳነው ካለ፣ መልእክትም እንዲያስተላልፉ እድሉን ልስጥዎ

አቶ አበበ፦ አካባቢው ላይ የሰላም ችግር የተፈጠረው ለተወሰነ ጊዜ ነው። አንዳንዶች ግን አካባቢው ሰላም እንደራቀው አድርገው ያነሳሉ። ይሄ የተዛባ አመለካከት እንደሆነ ሌሎች እንዲገነዘቡ እፈልጋለሁ፡፡

ከእናንተ ጋርም ተገናኝተን ስለአካባቢው አጠቃላይ ሁኔታ አንስተን መወያየት የቻልነው ሰላም በመሆኑ ነው። እናንተም በቆይታችሁ የገጠማችሁ ችግር እንደሌለ ያረጋገጣችሁ ይመስለኛል። የአካባቢው ነዋሪም እንግዳ ተቀባይ ነው። በህበረ ብሄራዊነትም ይታወቃል። ቀደም ሲል እንደገለጽኩትም የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች አሉ። በመልእክቴም ኑ ሸካ ዞን ላይ ኢንቨስት አድርጉ፤ እንቀበላችኋለን ዝግጁ ነን በማለት ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

ኢንቨስትመንቱ ላይ በተለይ እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ ባለሀብት ቢሰማራ ጥቅሙ ዘርፈብዙ ነው የሚሆነው። ቡናን ቆልቶ፣ ፈጭቶና አሽጎ ለገበያ ማቅረብ የሚቀረን ሥራ በመሆኑ ነው ይሄን መልእክት ማስተላለፍ የፈለኩት። አካባቢው በፍራፍሬ ምርትም ይመረታል። በተለይ አቮካዶ ግን ጥሬው ነው ለገበያ የሚቀርበው። የኛው ምርት እሴት ተጨምሮበት ተመልሶ ይቀርብልናል፡፡ቅመማ ቅመም ላይም በተመሳሳይ ሁኔታ ነው የሚስተዋለው። እሴት ጨምሮ ለማምረት የሚመጣን ባለሀብት እናበረታታለን፡፡

አዲስዘመን፦ ለነበረን ቆይታና ለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን፡፡

አቶ አበበ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You