በሀገራችን ቡና በስፋት ከሚለማባቸው አካባቢዎች መካከል የኦሮሚያ ክልሎቹ የወለጋ ዞኖች ይጠቀሳሉ። ዞኖቹ ባለፉት ዓመታት ሰላም ርቋቸው የቆየ ቢሆንም፣ በአካባቢው ሰላምን ለማምጣት በተደረጉ ጥረቶች በዞኑ ሰላም ከመስፈኑም በተጨማሪ ሰፋፊ የግብርና ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በቅርቡ በክልሉ ቄለም ወለጋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ተዘዋውረን ጉብኝት ባደረግንበት ወቅት ማረጋገጥ እንደቻልነው፣ በዞኑ በግብርናው ዘርፍ ሰፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው። በወቅቱም አርሶ አደሮችና የአካባቢው የመንግሥት ኃላፊዎችም ይህንኑ አረጋግጠውልናል።
በቄለም ወለጋ ዞን በስፋት ከሚለሙ ሰብሎች መካከል ቡና አንዱ ነው። በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የሚካሄደው ይህ የቡና ልማትም ውጤታማ መሆኑን የዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች አርሶ አደሮችና የሥራ ኃላፊዎች ይገልጻሉ። በዞኑ የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን በመጠቀም እንዲሁም ያረጁ የቡና ዛፎችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመጎንደል እና ምርታማነታቸውን በመጨመር ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።
በቄለም ወለጋ ዞን በዳሌ ሰዲ ወረዳ የአዊቱ ገንዳሶ ቀበሌ ማህበር ነዋሪው አርሶ አደር ተርፋሳ ፊጤ ሞዴል ገበሬ ናቸው። በፊት በቆሎ ብቻ ያመርቱ የነበሩት አርሶ አደሩ፣ ወደ ቡና ልማቱም በስፋት ገብተዋል። በግላቸው ብቻ አምስት ሄክታር የቡና እርሻ አላቸው። ከበቆሎ፣ ከቡና እና ከሌሎች ሰብሎችም ጭምር እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር እያገኙ መሆናቸውንም ይገልጻሉ።
የአዊቱ ገንዳሶ ቀበሌ በቡና አምራችነት ሞዴል ቀበሌ መሆኑን አርሶ አደሩ ጠቅሰው፤ ያረጁ የቡና ዛፎችን በማደስ፣ ዘራቸው የተበላሸ ነው ተብሎ የታመነባቸውን ከስር ነቅሎ በመጣልና አዲስ በመትከል የተሻለ ምርት ለማግኘት እየተሰራ ይገኛል ይላሉ።
በቡና አምራችነት በሚያገኙት ገቢ እየተዳደሩ እና ልጆቻቸውንም አስተምረው ለክብር ማብቃታቸውን አቶ ተርፋሳ ይናገራሉ። በዳሌ ሰዲ ወረዳ በዋናነት በቡና ልማት ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ይገልጻሉ። እሳቸውም በወረዳው በቡናና ሻይ ልማት ዘርፍ ለቡናና ለአርሶ አደሩም ምርታማነት ማደግ አርሶ አደሩን እያስተማሩና እና እያስተባበሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
አርሶ አደሩ እንዳሉት፤ በቡና ልማት በኩል አርሶ አደሩ አዲስ ቴክኖሎጂን እንዲለማመድ ጥረት እየተደረገ ነው። እኛም ሞዴል ገበሬዎችም ለሌሎች ገበሬዎች ምሳሌ እየሆንን እያሳየናቸው እንገኛለን፤ እነሱም ከኛ እየተማሩ ቴክኖሎጂን መሰረት ባደረገው ቡና ልማት በስፋት በመሳተፍ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ ሲሉ ያብራራሉ።
የወረዳው ቡናና ሻይ ልማት ሠራተኞች ባሳዩን መሰረት ያረጁ የቡና ዛፎችን ከላይ ከሁለት እስከ ሦስት ቅርንጫፎቹንና ግንዱን ከስር በማስቀረት ሌላውን ለዚህ ዓላማ በተዘጋጀ መቀስ በመቁረጥ የቡና ዛፍ በአዲስ መልኩ ምርት እንዲሰጥ ለማድረግ እየተሠራ ነው ይላሉ። አርሶ አደሮቹም በወረዳው በሚሰጣቸው መመሪያ መሰረት በስፋት መስራታቸውን አርሶ አደሩ ጠቅሰው፣ ሌሎች አርሶ አደሮችም ከእነሱ ልምድ በመውሰድ አያስፋፉት መሆናቸውን ይናገራሉ።
ካረጀውና ከታደሰው የቡና ዛፍ ከፍተኛ ምርት እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ የልማቱ ቱሩፋት ይህ ብቻ እንዳልሆነ ነው የሚናገሩት፡ ፡ እሳቸው እንዳብራሩት፤ አርሶ አደሮቹ የበሰለውን /ቀዩን/ ቡና ብቻ እየለቀሙ በማስፈልፈል ለውድድር ይቀርባሉ። በውድድሩ አሸናፊ የሆኑት አርሶ አደሮች በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ሜዳሊያ በመሸለም በተለያዩ መልኩ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ።
በዚህ በመበረታታትም የቡና ልማቱን በተሻለ መንገድ ለማስፋፋት እየሰሩ ይገኛሉ። በአካባቢው ያሉትንም አርሶ አደሮች የእሳቸውን ልማት እያዩ እየተማሩ በተግባርም እያሳዩ በስፋት እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አርሶ አደር ተርፋሳ በዚህ ልማት ውጤታማ በመሆናቸው የመኖሪያ ቤት ሠርተዋል፤ ከቡና ልማቱ በተጨማሪ የእንስሳትና የአታክልት ልማት እያካሁሄዱም ናቸው። በአጠቃላይ በእርሻ ሥራቸው እስከ ሁለት ሚሊን ብር ካፒታል አፍርተዋል።
የዳሌ ሰዲ ወረዳ የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ሥራ ሂደት ኃላፊ ኦሊቃ አብዲሳ እንዳሉት፣ ቡና የወረዳው አርሶ አደር ዋና የገቢ ምንጭ ነው። ከወረዳው 27 የገጠር ቀበሌዎች እና ሶስት የከተማ አካባቢ ቀበሌዎች በድምሩ 30 ቀበሌዎች ቡና ከወንዝ እስከ ጓሮ ድረስ በስፋት ያመርታሉ። አርሶ አደሩ ገቢ በማግኘቱ ቤቱን የሚያስተዳድረው በዋናነት በቡና ላይ ተመርኩዞ ነው።
በጉብኝቱ ከተካተቱት ቀበሌዎች መካከል የአዌቱ ገንዳሶ ቀበሌ አርሶ አደር በክላስተር የሚያካሂደው የቡና ልማት ተጎብኝቷል። በ20 ሄክታር ላይ እየተካሄደ ያለው የቡና ልማትም ከ40 በላይ አርሶ አደሮችን የያዘ ነው። ከቀበሌው የቡና ተክል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ተጎንድሏል።
የቡና ተክሉን በመጎንደል ምርታማነቱን ለማሳደግ በስፋት ተሰርቷል። የዚህም ተሞክሮ ተቀምሯል፤ ስልጠናዎችን በተለይ በሞዴል ገበሬዎች ላይ ተግባራዊ በማድረግ ምርታማነቱ መጨመሩ ታይቷል፤ በእዚህ ልማት በ2012 ሜዳሊያ የተሸለሙ ሞዴል አርሶ አደሮች እንዳሉበትም አስታውቀዋል።
የቄለም ወለጋ ዞን የላሎ ቅሌ ወረዳ አስተዳዳሪ ፈዬራ ኢተፋ ፤ የላሎ ቅሌ ወረዳ በ2016/17 የምርት ዘመን የቡና ልማት እንቅስቃሴን አስመልክተው ሲያብራሩ እንዳሉት፤ በምርት ዘመኑ 30 ሚሊዮን የቡና ችግኝ ለመትከል ታቅዶ፣ 35 ሚሊዮን ችግኞችን በችግኝ ጣቢያ ዝግጁ ማድረግ ተችሏል።
ይህ ችግኝ ከሚተከልባቸው አካባቢዎች ውስጥ በኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ እና በቄለም ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ገመቹ ጉርሜሳ የተመራው ቡድን የተጎበኘው የቡና ተከላ ክላስተር/ ኩታ ገጠም ሥራ/ አንዱ መሆኑንም አመላክተዋል።
ኩታ ገጠም/ ክላስተር/ ሲባል ማህበረሰቡ ለየግሉ ቡናን ከመትከሉ ይልቅ በቅንጅት አንድ ላይ ሆኖ በመትከሉ ውጤታማነቱን ያየበት መሆኑን ጠቅሰው፤ በቡና ተከላ ክላስተር ላይ በስፋት እየተሰራበት መሆኑን አመላክተዋል። የላሎ ቅሌ ወረዳ ባለፉት ዓመታት በበቆሎና ዳጉሳ ልማት ላይ መቆየቱን ተናግረው፣ የበለጠ ምርትና ጥቅም እያገኘበት ያለው ግን የቡና ልማቱ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቀደም ሲል ቡና ሲለማ የነበረው ከወንዝ ዳር ከሚዘጋጅ እንዲሁም ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በተመረተው ቡና የተዘጋጀ ችግኝ በመትከል እንዳልሆነም ጠቅሰው፤ በራሱ ጊዜ ከእናት የቡና ተክል ስር የበቀለውን ችግኝ ወስዶ በመትከል እንደነበር ያስታውሳሉ።
አሁን ግን ልማቱ በመንግሥትና በግብርና ባለሙያዎች እገዛ ሳይንሳዊ መንገድን በመጠቀም ችግኝ ተፈልቶ ተከላው እንደሚካሄድ አስታውቀዋል። ለችግኝ ተከላ የሚያስፈልገው ጉድጓድም የራሱ በሆነ መጠን በወቅቱ ዝግጁ እንደሚደረግ ጠቁመው፣ ችግኙም በወንዝ አካባቢ አስፈላጊው እንክብካቤ ተደርጎለት ለተከላ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ይህም የወረዳውን ኅብረተሰብ ምርታማነት እና ገቢውን በመጨመር ሰፊ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰው፤ሀገሪቱ ወደ ውጪ የምትልከውን የቡና ምርት በማሳደግ በኩልም ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው አስታውቀዋል። የአካባቢው ህብረተሰብም ይህን ተገንዝቦ በቡና ልማቱ በሰፋት እየሰራበት መሆኑን ጠቁመዋል።
የቄለም ወለጋ ዞን ሰዲ ጫንቃ ወረዳ የግብርና ባለሙያ አቶ ሰይድ ይመር እንደሚሉም፤ ወረዳው በቡና ልማትና ምርቱ በጣም ይታወቃል። ከወረዳው በየዓመቱ ሁለት ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ይቀርባል።ከወረዳው በ2016 ዓ.ም እስካሁን ድረስ ብቻ ሁለት ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ተልኳል።
አቶ ሰይድ በወረዳው በተለያየ የሰብል እና የአትክልት ዘርፎች ልማት እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፤ የወረዳው አግሮ ኢኮሎጂ ለሰብል ልማትም ሆነ ለተለያዩ የግብርና ሥራዎች ምቹ መሆኑን አስታውቀዋል። በሰብል ልማት በተለይ በሩዝ፣ በሰሊጥ እንዲሁም በአቮካዶ ኩታ ገጠም እርሻዎች /ክላስተሮች/ እንደሚታወቅም ይናገራሉ።
ወረዳው በ2009 ዓ.ም መመስረቱን ጠቅሰው፣ በበጋ መስኖ የለማ በቆሎ ማሳንም አስጎብኝተውናል። እሳቸው እንዳብራሩት፤ በቆሎው በ235 ያህል ሄክታር መሬት ላይ የለማ ነው። በክረምት እርሻም ቢያንስ ወደ ሰባት ሺህ ሄክታር መሬት በበቆሎ ለማልማት ዝግጅት ተደርጓል። በተመሳሳይም ሁለት ሺህ ሄክታር የሚሆን መሬት ላይ ሰሊጥ ለማልማት እየተሠራ ነው።
አጠቃላይ በወረዳው ወደ 32 ሺህ 574 ሄክታር መሬት በማልማት ወደ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሠራ ነው፤ እስካሁንም 18 ሺህ 700 ሄክታር መሬት በሰብል ልማት ተሸፍኗል። በዘር ያልተሸፈኑ ማሳዎችንም በሰኔ ወር መጨረሻ ዘርቶ ለመጨረስ እየተሠራ ይገኛል።
በወረዳው በበጋ ስንዴ መስኖ ልማት ወደ ሦስት ሺህ 950 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ሁለት ሺህ ኩንታል የሚሆን ምርት ለገበያ ማቅረብ መቻሉንም ተናግረዋል።
የቄለም ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገመቹ ጉርሜሳ በበኩላቸው ፤ ከ2008 አንስቶ በዞኑ ከነበረው የጸረ ሰላሞች እንቅስቃሴ ተላቆ ወደ መልካም ገጽታው መመለሱን አስታውቀዋል። ሰላምን የሚፈልገው የዞኑ ኅብረተሰብ ከፌዴራል መንግሥቱም ከክልሉም የጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም ከዞኑ ሚሊሻ ጎን በመሆን ሰላማችንን በሚገባ በማረጋገጥ ሙሉ ለሙሉ ወደ ልማታችን እንመለስ በሚል በመሰራቱ ሰላም ማስፈን መቻሉን አመልክተዋል። አሁን የቄለም ወለጋ ዞን የሰላም እና የልማት ምድር እየሆነ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ በዞኑ በአጠቃላይ ሰላም መስፈኑን ተከትሎ ዞኑም ኅብረተሰቡን ከችግሩ ለማውጣት በቅንጅት እየሠራ ይገኛል።
በዚያ ችግር ውስጥ መቆየት ከባድ እንደነበርም አስታውሰው፣ ይህንን ታሪክ ማድረግ እንደሚገባም ነው ያስታወቁት። የቄለም ወለጋ ዞን ሕዝብ ሸኔ ወደ አካባቢው ሲመጣ ለኦሮሞ እንደሚታገል፣ የኦሮሞን መብት እንደሚያስጠብቅ አምኖ እንደነበር ጠቅሰው፤ ቆይቶ ግን በቡድኑ ላይ የተሳሳተ እይታ መያዙን መረዳቱን አስታውቀዋል።
ዛሬ ግን ሕዝቡ መንግሥት የራሱ መሆኑን ተረድቶ እየሠራ መሆኑን ተናግረው፤ አሁን በትላልቅ መድረኮችና በሰላማዊ ሰልፍ ጭምር በሸኔ ላይ ተቃውሞውን በማሳማት፣ ባለው አቅምም በመመከት እና ለመንግሥት መረጃ በመስጠት ከዞኑ መንግሥት ጎን እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዋና አስተዳዳሪው እንደገለጹት፤ ዞኑ ለግብና ሥራ ሊውል የሚችል እምቅ አቅም ባለቤት ነው። ለእርሻ ልማት ብቻ ሊውል የሚችል 109 ሺህ 90 በላይ ሄክታር መሬት አለው። ከ467 ሺህ ሄክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይም ቡና ያለማል። በዚህ ላይ በስፋት ከተሠራ፣ እንስሳት፣ ወተትና ዶሮ ላይ ከተሠራ ደግሞ ከእስከ አሁን በላይ እጥፍ መሥራት ይቻላል። በዚህ ዓመትም 367 ሺህ ሄክታር ወይም ካለፈው ዓመት 23 በመቶ ጭማሪ ባለው መሬት ላይ ልማቱ እየተካሄደ ይገኛል። በዚህም ምርቱን በ14 ነጥብ አምስት በመቶ ለመጨመር እየተሠራ ነው።
እስካሁንም የመሬት ዝግጅቱ ተጠናቅቋል፤ 150 ሺህ በላይ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ቀርቦ ከዚህ ውስጥም 50 በመቶው ተሰራጭቷል። ማዳበሪያ በቂ እንዳልሆነ ታውቆ ተጨማሪ እየተጠበቀ ይገኛል። ከአራት ሺህ በላይ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘርም ተዘጋጅቷል።
አሁን ደግሞ ቡና ላይ በስፋት መሥራት ጀምረናል የሚሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ ባለፈው ዓመት /በ2015/16 የምርት ዘመን / ብቻ 197 ሚሊዮን የቡና ችግኞች መተከላቸውን አስታውቀዋል። የዚህ አካባቢ የአየር ሁኔታ ምቹ ከሆነና የመሬት አሲዳማነቱ መታከም ከተቻለም የቡናውን ምርታማነት በእጥፍ ለማሳደግ እንደሚቻልም ተናግረዋል። ለእዚህም ታስቦበት በመንግሥት እና በሕዝብ የችግኝ ጣቢያዎች 378 ሚሊዮን ችግኞች ተዘጋጅተው እየተተከሉ መሆናቸውን አመላክተዋል።
አቶ ገመቹ እንዳስታወቁት፤ በሰብል ልማት በኩል ባለፈው ዓመት ብቻ ቢያንስ 280 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኖ፣ 10 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማግኘት ተችሏል። በዚህ ዓመት ደግሞ ይህንን እጥፍ ለማድረግ ታቅዶ የተለያዩ የከተማ እና የገጠር ልማት ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው።
ሥራዎቹ ሲታዩ የዞኑ አቅም ገና እንዳልተነካ ያመላክታሉ ሲሉም ተናግረዋል። በዞኑ በሚገባ ከተሠራ በብዙ መልኩ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል። ቄለም ወለጋ ዞን በውሃ ሀብት ብቻ ሁለት ሺህ በጋ ከክረምት የሚፈሱ በርካታ ወንዞች አሉት። ይህ ሀብት ለመጪው ትውልድም ሊሻገር የሚችል ነው። እንደ ኦሮሚያም በጋ ከክረምት ማምረት ከተቻለ፣ ኦሮሚያን ማብላት እንደሚቻል ተግባብተንበት እየሠራን ነው ብለዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም