ምድር ስትሠራ ለሰው ልጆች የሚያስፈልጉ ነገሮችን በውስጧም፣ በገጿም እንድትይዝ ሆና ነው፡፡ እነዚህ ለሰው ልጅ በሕይወት የመኖር ምክንያት የሆኑ የምድር ገጸ በረከቶች ታዲያ፤ በራሱ በሰው ልጅ የአጠቃቀም ችግር ምክንያት ሲመናመኑ እና ሲጠፉ ይስተዋላል፡፡ በዚህም ሰው የተሰጠውን አውቆ በአግባቡ መጠበቅና መጠቀም ባለመቻሉ ብቻ፤ ከፍ ላሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነልቦናዊና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሲዳረግ ይታያል፡፡
ለምሳሌ፣ መሬት ከፍ ያለ የደን ሽፋን እንዲኖራት ሆና መፈጠሯ፤ ከባቢን ለመጠበቅ፣ የአየር ንብረት ሚዛንን ለማስተካከል፣ ለሰው ልጆች የተመቸ ሥነምሕዳር እንዲኖር ነው፡፡ ይሁን እንጂ የሰው ልጆች በአንድም በሌላም ምክንያት ዛፎችን በመጨፍጨፍ ከባቢን በማራቆታቸው ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች እየተፈተነ ይገኛል፡፡ ድርቅ፣ ሰደድ እሳት፣ ጎርፍ፣ ወጀብና አውሎ ንፋስ፣… የመሳሰሉ ዛሬ ላይ ዓለማችንን እየፈተኑ የሚገኙ ክስተቶችም የዚሁ ውጤቶች ናቸው፡፡
በእነዚህ ክስተቶች ምክንያት ደግሞ የሰው ልጆች ለስደት፣ ለረሃብ፣ ለሥራ እጦት፣ ለኢኮኖሚ ችግር፣ ለሞት እና ሌሎችም የከፉ ችግሮች እየተጋለጡ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያም የዚህ ችግር ተጋላጭ ከሆኑ የዓለማችን ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ እናም የሰው ልጅ በራሱ የፈጠረውን ችግር በራሱ ሠርቶ ሊፈታው የተገባ እንደመሆኑ፤ ዛሬ ላይ ዓለማችን ከዚህ ችግር ለመሻገር የሚያስችላትን አቅጣጫ ነድፋ እየሠራች ነው፡፡
የካርበን ልቀትን መቀነስ አንዱ የዚህ ችግር መሻገሪያ ሆኖ የተቀመጠ ቢሆንም፤ በዋናነት ግን የተጎዱ ከባቢዎችን መልሰው እንዲያገግሙ የማድረጉ ተግባር ግን ተኪ የሌለው ነው፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገረ ምሳሌነት ያለው ተግባር ቢኖራትም፤ ከ2011 ዓ/ም ጀምሮ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ታግዛ እያከናወነች ባለው ተግባር ግን ዘርፈ ብዙ ውጤት እያስገኘ ያለ ዕድገት ማምጣት ችላለች፡፡
ምክንያቱም፣ ኢትዮጵያ የዐረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን በየዓመቱ የምታካሂድ ብቻ ሳይሆን፤ በየምዕራፍ ከፍላ እና ከየዓመቱ ተግባር ባሻገር በየምዕራፉ ማሳካት የሚገባትን ግብ በማስቀመጥ እየሠራች ትገኛለች፡፡ ለምሳሌ፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ ባሉት አራት ዓመታት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል አቅዳ፣ ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መትከል ችላለች፡፡
የዚህን ልምድ በመውሰድም፣ በሁለተኛው ምዕራፍ 25 ችግኞችን ለመትከል እና በሁለቱ በድምሩ 50 ቢሊዮን ችግኞችን ለማሳካት ወጥና ወደሥራ በገባችበት የመጀመሪያው ዓመት ተግባሯ እቅዷን ማሳካት እንደምትችል ያሳየችበትን ተግባር ፈጽማለች፡፡ ዘንድሮም የሁለተኛው ምዕራፍ ሁለተኛ ዓመት ተግባሯን ለማከናወን ሰሞኑን የቅድመ ዝግጅት ጅማሮ መርሐ ግብር አካሂዳለች፡፡
በዚህ ዙሪያ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ኢትዮጵያ ላለፉት አምስት ዓመታት፣ በተለይም በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተጠነሰሰው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አማካኝነት በየዓመቱ የችግኝ ተከላ ሥራ ስታካሂድ ቆይታለች። ዛሬ የባለፉት ዓመታት ጥረታችንን በማጤን የ2016ቱን ዙር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ቅድመ ጅማሮ መርሐ ግብር ተካሂዷል። በተካሄደውም የአረንጓዴ ዐሻራ ቅድመ መክፈቻ መርሐ ግብር ሁነት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ሪፖርት ይፋ የተደረገ ሲሆን፤ በዚህም የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በ2011 ዓ.ም ከነበረበት 17 ነጥብ ሁለት በመቶ ወደ 23 ነጥብ ስድስት በመቶ ከፍ ብሏል።
ይሄን አስመልክቶ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፣ “በአረንጓዴ ዐሻራ ጥረቶቻችን አማካኝነት ልናሳካው ለምንፈልገው ለውጥ የአመለካከት እና የአዕምሮ ውቅር ሽግግር ያስፈልገናል። እንደ ሀገር ልናሳካ ካለምነው 50 ቢሊዮን ችግኞች በያዝነው ዓመት 40 ቢሊዮን ችግኞች ላይ ለመድረስ እየጣርን በመሆኑ ዘንድሮ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን በጋራ መትከል ይኖርብናል። ለነገው ትውልድ ቅርስ ለመተው የሚሻ ሁሉ ዛሬ ላይ ማዋጣት የግድ ይለዋል” ብለዋል፡፡
ከዚህ መረዳት የሚቻለው፣ የእስካሁኑ መንገድ ውጤታማም፣ ዘርፈ ብዙ ዕድገትና ስኬት የተመዘገበበትም ነው፡፡ ምክንያቱም ተግባሩ የአካባቢን ሥነምሕዳር ከማስጠበቅ ባለፈ፣ ከምግብ ዋስትና መረጋገጥ፣ ከሥራ እድል ፈጠራ፣ ከጤና፣… የመሳሰሉ ማኅበራዊም፣ ኢኮኖሚያዊም አበርክቶዎቹ በግልጽ እየታዩም፤ ፍሬያቸውን ሕዝቡ እያጣጣመም ይገኛል፡፡ በመሆኑም ይሄንን የአረንጓዴ ዐሻራ ያስገኘውን ዘርፈ ብዙ ውጤት ማሳደግ እና የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን መሥራት ከሁሉም ይጠበቃል!
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም