በመንግሥት ፕሮጀክቶች በስፋት የሚስተዋሉት የጥራት እና ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ያለመጠናቀቅ ችግሮች እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ እያስከፈሉን ስለመሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። ችግሩ ቀደም ባለው ጊዜ በሀገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶች ሳይቀር በስፋት ሲስተዋል የነበረ፣ አሁንም እንደ ሀገር ያልተሻገርነው ትልቁ ችግራችን ነው።
ችግሩ ሕዝባችን እንደ ዓይኑ ብሌን በሚያየው የታላቁ የህዳሴ/የዓባይ ግድብ ላይ ሳይቀር ተከስቶ የነበረ፣ ዛሬም ፈተና የሆነ፣ በዚህም ከፍተኛ የሀገር ሀብት ለብክነት እየዳረገ የሚገኝ፣ የሕዝባችንን የልማት ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈታተነ የሚገኝ ነው።
የፕሮጀክት ግንባታ ጨረታ ላይ የሚጀምረው የዘርፉ የተበላሸ አሠራር፣ ፕሮጀክቶቹ ለተቋራጮች ከተሰጡ በኋላም ሥራዎች ተገቢነት ባለው የቁጥጥር እና የክትትል ሥርዓት እየታገዙ አለመከናወናቸው ለችግሩ በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው። ለተቋራጮች የሚሰጥ ያልተገባ/የማይመጥን የብቃት ማረጋገጫም የዚሁ ችግር አካል ነው ።
በተለይም ፕሮጀክቶችን በአንድም ይሁን በሌላ የመፈጸም አቅም ለሌላቸው ተቋራጮች በመስጠት የሚፈጠሩ የአፈጻጸም መዘግየቶችም ሆነ፣ የፕሮጀክቶች ግንባታ መቋረጥ ሀገርን ለከፍተኛ የሀብት ብክነት እየዳረገ ነው። ፕሮጀክቶችም ለታቀደላቸው ዓላማ እንዳይውሉ ተግዳሮት በመሆን፣ የሕዝብ ቅሬታ ምንጭ እየሆነም ይገኛል።
በቅርቡ ዋና ኦዲተር በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን የሚሠሩ የፌዴራል መንግሥት ፕሮጀክቶችን አስመልክቶ ባወጣው የኦዲት ግኝት ሪፖርት፣ በናሙና ከታዩ 41 የተቋረጡ ፕሮጀክቶች ውስጥ በመጀመሪያ ውለታቸው ሳይጠናቀቁ በሌላ ጨረታ ወደ ግንባታ የገቡ 13 ፕሮጀክቶች በመንግሥት ላይ በድምሩ 16 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ አስከትለዋል ይላል ፡፡
በፌዴራል በጀት የሚሠሩ ፕሮጀክቶችን ያያዙ ሥራ ተቋራጮች የያዙትን ፕሮጀክት ሳያጠናቅቁ ወይም አፈጻጸማቸው ሳይታይ በሌላ ጨረታ ላይ እንዳይወዳደሩ የሚከለክል አሠራር ሥርዓት ተዘርግቶ ቁጥጥር እና ክትትል ባለመደረጉ የውል ዋጋቸው በድምሩ 10 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በላይ የሆነ 12 ፕሮጀክቶች በሁለት ሥራ ተቋራጮች ተይዘዋል ፡፡
የፌደራል መንገዶች ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በውስን ፕሮጀክቶች የክትትልና የቁጥጥር ሥራ የጀመረ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ በምትተገብረው የፕሮጀክት ልክ የተደራጀና የተቀናጀ የቁጥጥርና ክትትል ሥራ ባለመከናወኑ በናሙና ከታዩ 41 የተቋረጡ ፕሮጀክቶች ውስጥ የ38 ፕሮጀክቶች ሁለት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር የመልካም ሥራ አፈጻጸም ዋስትና በውለታቸው መሠረት አልተወረሰም ወይም ገቢ አልሆነም ፡፡
ዋና ኦዲተር በናሙና ከተመለከታቸው 41 የተቋረጡ ፕሮጀክቶች ውስጥ ለ25 ፕሮጀክቶች ከተከፈለው የቅድመ ክፍያ ብር ሦስት ነጥብ ሁለት ውስጥ ሁለት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ተመላሽ ተደርጎ ለሌላ የልማት ሥራዎች እንዲውል አልተደረገም ፡፡
በሠራተኞችና በኅብረተሰቡ ጤንነትና ደህንነት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ለመከላከል የሚያስችል ጠንካራ ቁጥጥርና ክትትል እያደረገ ባለመሆኑም በናሙና የታዩ ግንባታ ላይ ባሉ ሰባት ፕሮጀክቶችን የሚሠሩ ተቋራጮች የቅድመ መከላከል ሥራዎችን አሟልተው እየሠሩ አይደለም፡፡
ለ24 ሥራ ተቋራጮች መመሪያው የማይፈቅደው ደረጃ ተሰጥቷል ለልዩ ሥራ ተቋራጭ የተሰጠው የብቃት ማረጋገጫ ዘርፍ እና በመመሪያው ላይ የተቀመጠው ዘርፍ የማይመሳሰል ሆኖም ተገኝቷል ፡፡
በሕንጻ፣ በመንገድና በልዩ ልዩ ሥራ ተቋራጭነት ዘርፍ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ 261 የውጭ ሀገር ሥራ ተቋራጮች እንዳሉ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ ቢያሳይም ከ11 ሥራ ተቋራጮች ውጭ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም የውጭ ሀገር ሥራ ተቋራጮች በምዝገባ መመሪያው በተቀመጠው መስፈርት መሠረት የብቃት ማረጋገጫ በመስጠት ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገባቸው አይደለም። ከ11 ሥራ ተቋራጮች ውስጥም ሦስቱ የተቀመጠውን አነስተኛ መስፈርት ሳያሟሉ የብቃት ማረጋገጫው ተሰጥቷቸዋል ፡፡
ባለሥልጣኑ ጊዜያቸውን ጠብቀው ፈቃድ በማያድሱ ሥራ ተቋራጮች ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ርምጃ እየወሰደ ባለመሆኑ ዋና ኦዲተር በናሙና ከተመለከታቸው 40 ሥራ ተቋራጮች ማኅደር ውስጥ 36ቱ ጊዜያቸውን ጠብቀው አለማደሳቸውን መታዘቡን በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
የዋና ኦዲተሩ ሪፖርት በዘርፉ ያለውን ችግር የቱን ያህል የገነገነ መሆኑን በተጨባጭ ያሳየ ነው፡፡ በተለይም እንደሀገር ለኮንስትራክሽን ዘርፉ እየተመደበ ካለው ከፍተኛ ሀብት አኳያ የተወካዮች ምክር ቤቱ ለሪፖርቱ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ የሚገኝበትን ጠንካራ ርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል።
በዘርፉ ተጠያቂነት የሰፈነበት አሠራር ማስፈን የሚያስችል ጠንካራ የክትትል እና ቁጥጥር ሥርዓት በመፍጠር፣ ሀገር በዘርፉ እያጣች ያለውን ከፍተኛ ሀብት መታደግ፣ ለዘርፉ የሚመደበው ሀብት በተገቢው መንገድ ሥራ ላይ ውሎ የሕዝባችንን የልማት ጥያቄ በአግባቡ መመለስ መቻሉን መከታተል ይኖርበታል። ይህ የማድረግ የሕግ እና የሞራል ኃላፊነት እና ተጠያቂነትም አለበት!
አዲስ ዘመን ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም