የኮርፖሬሽኑና የኩባንያው ስምምነት – የሴራሚክ ምርትን በሀገር ውስጥ ለመተካት

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው አንዱ ተግዳሮት ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶችን በሚፈለገው ልክና ወቅት ማግኘት አለመቻል መሆኑ ይገለጻል:: እነዚህን ግብዓቶች ለማስገባት የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አለመቻልም ሌላው ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል:: በተለይ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ማጠናቀቂያ ግብዓቶች በአብዛኛው ከውጭ የሚመጡ መሆናቸው ግንባታዎች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዳይበቁ ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ::

በተለይ የሴራሚክ ምርቶች በሀገር ውስጥ እየተመረተ ያለው በጣም ጥቂት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ/ እሱም በቅርቡ ነው መመረት የጀመረው /አብዛኛው የሴራሚክ ምርት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ እየተደረገ ነው ከውጭ የሚገባው:: በሀገሪቱ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት የሚደረገው ጥረት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን በተለይ የማጠናቀቂያ ግብዓት ችግር ለመፍታት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ታምኖበት እየተሠራበት ነው:: ሰሞኑንም በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሽንና ካም ሴራሚክ በተሰኘ ሴራሚክ ለማምረት ወደ ሥራ በገባ ሀገር በቀል ኩባንያ መካከል የተደረገው ስምምነትም ይህንኑ ያመለክታል::

በስምምነቱ ወቅት የወጡ መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ ለሴራሚክስ ማምረቻ የሚሆነው ግብዓት /አፈር/ በከፍተኛ አቅም በሀገራችን የሚገኝ ቢሆንም፣ አስካሁንም ድረስ በዋነኛነት አፈርን በጥሬ እቃነት የሚጠቀመው ሴራሚክ ከውጭ ይገባል። ይህም አፈርን ከውጭ ሀገር እንደማስገባት የሚቆጠር ሲሆን፣ ከውጭ ከሚገባውም ሴራሚክ 30 በመቶው ያህሉ በመሰባበር ይባክናል።

በሀገሪቱ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሴራሚክ ፋብሪካ አልነበረም፤ በቅርቡ ሁለት የውጪ የሴራሚክ ፋብሪካዎች ማምረት ቢጀምሩም፣ የሴራሚክ ፍላጎቱን የሚመልሱ አይደሉም፤ ካም ሴራሚክ የተሰኘ ሀገር በቀል የሴራሚክስ ማምረቻ ፕሮጀክት ግንባታውን ከጀመረ ቢቆይም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሥራ አልገባም። ኬንያን በመሳሰሉ ሀገራት በቀን እስከ 60 ሺህ ካሬ ሴራሚክስ የሚያመርቱ አራት ያህል ኩባንያዎች እንዳሉም መረጃዎች አመላክተዋል።

ከካም ሴራሚክ ጋር ስምምነት ያደረገው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሸን በ2017 የሴራሚክስ ተኪ ምርቶችን ከውጭ ማስገባቱን ለማቆም እና በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት አቅዶ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን አስታውቋል። የዚህ እንቅስቃሴው አንዱ አካል የሆነውም ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገር ውስጥ ሴራሚክ ለማምረት ከጫፍ ተደርሷል። እስከ ጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም 20 ሺ ካሬ ሴራሚክ በቀን ማምረት የሚቻልበት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው።

ይህን እቅድ ለማሳካት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከካም ሴራሚክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ጋር የአክሲዮን ድርሻ ስምምነት አድርጓል። ስምምነቱንም የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ ዮናስ አያሌው (ኢንጂነር) እና የካም ሴራሚክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር ካሳሁን ሙሉጌታ ተፈራርመዋል።

የካም ሴራሚክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አጠቃላይ ካፒታል ሁለት ቢሊዮን ስምንት መቶ ሚሊዮን ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን 30 በመቶ ወይም 624 ሚሊዮን የአክሲዮን ድርሻውን ገዝቶታል።

ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው እንደገለጹት፣ ከካም ሴራሚክስ ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ ብዙ ውይይቶች ተደርገዋል። ውይይቱ ከአንድ ዓመት ከአምስት ወር በላይ ወስዷል። የፊርማ ሥነሥርዓቱ እውን እንዲሆን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ትልቅ ሚና ነበራቸው።

ኢንጂነር ዮናስ ስምምነቱ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ያለበትን ችግር እንደሚቀርፍ ገልጸዋል። የኮንስትራክሽን ሥራ የሴራሚክስ ግብዓት በብዛት እንደሚፈልግ ኢንጂነሩ ጠቅሰው፣ ስምምነቱ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለማግኘት ይረዳል ብለዋል፤ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ትብብርንም እንደሚያመለክት ሥራ አስፈጻሚው አመልክተው፣ በቀጣይ የምርት አቅሙን የማሳደግ ሥራ እንደሚሠራም አስታውቀዋል። በሁለት ወር ውስጥ ወደ ምርት እንዲገባ በማድረግ ከውጭ የሚገባ ምርትን የመተካት ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

የካም ሴራሚክስ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋሪዮ ገልገሎ እንዳሉት፤ የካም ሴራሚክስ ሴራሚክ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የፕሮጀክት ሀሳቡን የጀመረው ከሰባት ዓመት በፊት ነው። የመሬት እና የተለያዩ ጉዳዮች በመጓተታቸው ፕሮጀክቱ እስካሁን ዘግይቷል።

አንድ ሴራሚክ ፋብሪካ ከአንድ ዓመት ተኩል እስከ ሁለት ዓመት ወደሥራ ማስገባት ይቻላል ሲሉ ጠቅሰው፣ ካም ሴራሚክስ የኮቪድ-19 ወረርሽኝና የውጭ ምንዛሪ ችግር መሬት ከማግኘት ጋር ተያይዞ በተከሰተው ችግር የተነሳ ፕሮጀክቱን መጓተቱን አስታውቀዋል::

ድርጅቱ ከኮቪዱ ወቅት ቀደም ብሎ የውጭ ምንዛሪ እንዳገኘ ለፋብሪካው የሚያስፈልገውን ከ300 ኮንቴይነር በላይ መሣሪያም ሀገር ውስጥ ገብቶ አብዛኛው መሣሪያም መተከሉን አስታውቀዋል። ለተለያዩ ሥራዎች የሚረዱ መጋዘኖች እና ሌሎች አብዛኛዎቹ አብረው የሚሄዱ የሲቪል ሥራዎች ሳይጠናቀቁ መቆየታቸውን አመልክተዋል።

ከኮንስትራከሸን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጋር መገናኘት የተቻለው ከባንክ ጋር የተያያዘው ጉዳይ እየተጎተተ ባለበት ወቅት መሆኑን ጠቅሰው፣ በፕሮጀክቱ ግንባታ ወቅት የፋይናንስ አቅርቦት በተፈለገው ጊዜ ካልተገኘ ፕሮጀክቱ ለተፈለገው ዓላማ ሊውል እንደማይችል አስታውቀዋል።

ለምርቱ ሥራ ከሚያስፈልገው ጥሬ እቃ አብዛኛው በሀገር ውስጥ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል:: ፋብሪካው ከውጭ የሚገቡ ሴራሚክ ምርቶችን የሚተካ ከመሆኑም አንፃር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንና ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚሉ ሀሳቦች ሲሰጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል:: ሚኒስትሮችና የክልል ባለሥልጣናትም ፕሮጀክቱን መመልከታቸውንና ችግሩም መፈታቱን አቶ ዋሪዮ አስረድተዋል።

በመቀጠልም በባንክ በኩል ገንዘቡ የመጎተት ሁኔታ በአብዛኛው የቀረውን የሲቪል ሥራውን ከኮርፖሬሸኑ ጋር ለመጨረስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምልከታዎች መደረግ መጀመራቸውን ጠቅሰው፣ በዚህ ሂደትም ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሸን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጋር ለመሥራት ስምምነት መደረሱን አስታውቀዋል።

አቶ ዋሪዮ እንዳብራሩት፤ የካም ሴራሚክስ የማምረት አቅም በቀን 20 ሺህ ካሬ ነው። ይህም ከሀገሪቱ የሴራሚክ ፍላጎት አኳያ ሲታይ በጣም ኢምንት ነው። ፍላጎቱን ለመመለስ ፋብሪካው አልቆ ማምረት ሲጀምር በሁለት እና በሦስት ዓመት ራሱን እጥፍ እያደረገ እና እያበዛ መሄድ ይኖርበታል።

አሁን ለፕሮጀክቱ በመንግሥት በኩልም ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረው፣ በቀጣይ የተሻለ ምርታማነት እንደሚኖር ግምታቸውን አስቀምጠዋል። ከኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ጋር መሥራት ከተጀመረ በኋላ ግንባታው በጥሩ እየሄደ ነው ብለዋል። አሁን ያለው ቀሪ ሥራ ከሦስት እና አራት ወር የማያልፍ መሆኑንም አመላከተዋል::

ሴራሚክ ከወቅት ጋር የሚሄድና አፈርን እንደሚጠቀም ጠቁመው፣ አፈሩም ከተለያዩ አካባቢዎች እንደሚመጣ አስታውቀዋል:: ዝናብ በሚጀምርበት ወቅት አፈሩን ለማምጣት ስለማያስችል ደረቅ ወቅት ይጠበቃል ብለዋል። የፕሮጀክቱ የሲቪል ሥራ ቢያልቅም ወደ ምርት ለመግባት ክረምቱ እስኪጠናቀቅ /እስከ ጥቅምት/ መጠበቅ የግድ መሆኑንም አስታውቀዋል:: ለሴራሚክ ማምረቻነት የሚውሉ ጥሬ እቃዎች በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በስፋት እንደሚገኙም ተናግረዋል::

የካም ሴራሚክስ ማምረቻ ፋብሪካ በቢሾፍቱ እንደሚገኝ አስታውቀው፣ ጥሬ እቃውም ጉጂ አካባቢ በስፋት ይገኝ እንደነበር አስታውሰዋል:: አሁን ግን በተለያዩ ጥናቶች ከዝዋይ ወዲህ ባለው ራዲየስ እስከ ሰላሌ፣ ጉራጌ አካባቢ በስፋት መኖሩ ታውቋል ብለዋል። አንዳንዴም እስከ 60 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ድረስ ከደብረብርሃን ጀምሮ ዝዋይ አካባቢም እንደሚገኝ አብራርተዋል።

አቶ ዋሪዮ በሴራሚክስ ምርት ላይ በኬንያ ያደረጉትን ምልከታ አስመልክተው እንደተናገሩትም፣ በኬንያ አንድ የሴራሚክስ ፋብሪካ ብቻ 60 ሺህ ካሬ በቀን ያመርታል። በሀገሪቱ ይሄንን አቅም ይዘው የሚያመርቱ አራት ፋብሪካዎች አሉ። አራቱም የማምረት አቅማቸውን በእጥፍ አሳድገው 120 ሺህ ካሬ በቀን ለማምረት ፕሮጀክት ላይ እንደነበሩ ያስታውሳሉ።

በኢትዮጵያ አሁን እያወራን ያለነው ስለ 20 ሺህ ካሬ ነው ሲሉ ጠቅሰው፣ የሀገሪቱ ፍላጎት ከውጪ የሚመጣውን መተካት ነው፤ 20 ሺ ካሬ ሲባልም የባሕር ላይ ጠብታ አይነት ነው ሲሉ አስገንዝበዋል። ሴራሚክ በሀገር ውስጥ መመረቱ ከውጭ የሚገባውን ተኪ ምርት በተወሰነ መልኩ ይቀንሳል የሚሉት አቶ ዋሪዮ፣ መቀነሱም ብቻ ሳይሆን ከውጭ ሲታዘዝ ወደ ሀገር ቤት እስኪገባ የሚቃጠለውን ጊዜ ማሳጠሩ እና ገበያው በመጠኑም ቢሆን በቀጣይነት ግብዓቱን ማግኘቱ ትልቅ ተስፋ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

በሀገር ውስጥ መመረቱ፣ ምርቱ ሲፈለግ በወቅቱ እንዲገኝ እንደሚያስችል ጠቅሰው፣ ከውጭ እንደሚገባው ገበያ የመጣው ሲያልቅ እና ዳግም ለማምጣት ኤልሲ ሲከፈት መጠበቅና የመሳሰሉት ችግሮች ይቀረፋሉ ብለዋል። ፋብሪካውም 20 ሺህ ካሬ በቀን የሚያመርተው ሲጠራቀም ፍላጎት ማሟላት ከሚለው በተሻለ ገበያውን የማረጋጋት ውጤቱ ከፍተኛ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በስምምነቱ ወቅት የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ለሀገራዊ እድገት ያለውን አበርክቶ ይበልጥ ለማሳደግ ስምምነቱ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል:: ፕሮጀክቱም በተለይ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በጋራ ለመሥራት ያደረጉት ስምምነት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፣ መንግሥት ቅድሚያ ሰጥቶ ከሚሠራባቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ የሴራሚክስ ምርትን ማሳደግ ነው። ሀገሪቱ ታላቅ ሀገር ብትሆንም፣ የኮንስትራክሸን ኢንዱስትሪው እንደ ሀገር ገና አላደገም፤ ነገር ግን ያድጋል። ለእድገቱም ሁኔታዎች ያስገድዳሉ።

ሀገሪቱ ከተፈጥሮ ሀብትም ሆነ ከሰው ኃይል አኳያ ለማደግና ለመበልፀግ፣ ኢኮኖሚ ለማመንጨት የተዘጋጀች ናት ሲሉም ተናግረው፣ የመንግሥት የአሠራር ሥርዓቱ እየተሻለ በተለይ ለኢንዱስትሪው ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ከሄደ ኢንዱስትሪው ሊያድግ እንደሚችል ብዙ አመላካች ሁኔታዎች አሉ ብለዋል።

አቶ ታረቀኝ እንዳስረዱት፤ አሁን መንግሥት ኢንዱስትሪው ማኅበራዊ ሽግግር እንዲያመጣ የተለያዩ ፖሊሲዎችን አጽድቋል። የኢንዱስትሪው ባለቤት እና ኢንዱስትሪ እድገቱን የሚያመጣው የግሉ ዘርፍ ነው ተብሎ ይታመናል። በመሆኑም በግሉ ዘርፍ የሚመራ የኢንዱስትሪ ሥርዓት እንዲገነባ ይፈልጋል።

ከዚያ ውጪ አሁን በተጀመረው አይነት በሽርክናም ይሠራል። ተኪ ምርትን የሚያመርቱ የካም አይነት ኩባንያዎች ሁለት፣ ሦስት፣ አራት እያሉ በቁጥራቸው የሚያድጉ መሆናቸውን አመላክተዋል። በዚህ ሂደትም የአሠራር ሥርዓቶች እየተሻሻሉ ችግሮችም እየተቀረፉ እንደሚመጡ ጠቅሰው፣ በተለይ በሽርክና የሚሠሩት በአትራፊነትም በአምራችነትም ፋይዳቸው እየጎላ እንደሚመጣ ተናግረዋል።

በአብዛኛው በአገራችን በሴራሚክ ምርት እስካሁን በውጭ ሀገር ጥገኛ ሆነን ቆይተናል ሲሉም ጠቅሰው፣ ሁለት ኢንዱስትሪዎች /ኢስት ኢንዱስትሪያል ዞን ውስጥ ዱዋል የሚባለው ሴራሚክስ፤ እንዲሁም አረርቲ ደግሞ በአማራ ክልላዊ መስተዳድር ውስጥ ያለው/ ብቻ በዚህ የሴራሚክ ምርት ማምረት ሥራ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል:: ሁለቱም ፋብሪካዎች በውጭ ዜጎች የተያዙ መሆናቸውን አመላክተው፣ አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ በሽርክና የተጀመረው የካም ሴራሚክ የመጀመሪያው ሀገር በቀል የሴራሚክ ማምረቻ ኢንዱስትሪ መሆኑን አመላክተዋል።

መንግሥት አሁን ትኩረት ከሰጠው ከተኪ ምርት አኳያ ከውጭ የሚመጣውን ሀገር ውስጥ የሚተካ የሚል ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ በትኩረት እየተተገበረ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም የመንግሥትን ዓላማ ከማሳካትም, አኳያ ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል:: ከዚህ አኳያም የሴራሚክ ፋብሪካውን መንግሥት የሚደግፈው፣ ክትትል የሚያደርግለት ፕሮጀክት ነው ሲሉ ጠቅሰው፣ እንደ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ክትትል እንደሚደረግለት አስታውቀዋል።

ካም ሴራሚክስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማምረት ጀምሮ ሀገራዊ ፍጆታውን እንደ ሀገር በአጭር ጊዜ መሸፈን ከተቻለ ከውጭ የሚመጣውን የሴራሚክስ ምርት እናቆማለን ብለዋል። የፋብሪካው የማምረት አቅም እያደገ ከመጣም የውጭ ምንዛሪ በማውጣት አፈር ከውጭ ማምጣት ተገቢ አይሆንም ሲሉም አስገንዝበዋል።

አፈር ከውጭ ጭነን ስንመጣ 30 በመቶ ተሰባብሮ ይጠፋል ሲሉም ጠቅሰው፣ መንግሥት ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ያቀደው አንዱ ምርት ሴራሚክስ ነው ሲሉም አስታውቀዋል:: በሚቀጥለው ዓመት በ2017 ሴራሚክስን በሀገር ውስጥ ምርት ሙሉ ለሙሉ ለመተካት መንግሥት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፤ ይደግፋልም ብለዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You