እግሮች ወደ ችግኝ ተከላ፤ እጆች ወደ አረንጓዴ ዐሻራ …

የኢትዮጵያ ደን ልማት ታሪክ እና የደን ባለአሻራዎች ቅኝት በሚል ንዑስ ርዕስ እንዳስቀመጡት፤ ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ምድራዊ ስፋቷ 60 በመቶ በደን ሀብት የተሸፈነ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። በሂደት ግን በብዝኃ- ሕይወት መመናመን ምክንያት ጥቅል የደን ሽፋን ወደ ሦስት በመቶ ይነገራል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክት ደግሞ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ወደ 20 በመቶ መመንደጉን ይጠቁማሉ:: በተለይም ደግሞ የቀድሞ ጠቅላይ መኒስት መለስ ዜናዊ በአረንጓ ዐሻራ ላይ የነበራቸው የተቃና እይታ በዓለም አቀፍ ደረጃም ኢትዮጵያን ዕውቅና ያጎናጸፋት መሆኑ ይታወቃል:: በእርሳቸው እግር የተተኩት ጠቅላይ መኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም በሥልጣን ዘመናቸው በአረንጓ ዐሻራ መርሐ ግብርን ለማስቀጠል ጥረት ማድረጋቸው አይካድም::

ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሀገሪቱን ችግኝ የመትከል ባህል እጅግ ወደ ላቀ ደረጃ ያሻገረውን የአረጓዴ ዐሻራ ተግባራዊ አድርገዋል:: በዚህም ቀደም ባለው ጊዜ በሚሊዮን ሲተከሉ የነበሩ ችግኞችን ወደ ቢሊዮን ማሳደግ ተችሏል::

ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገጽ ላይ ‹‹አረንጓዴ ዐሻራ፤ የትውልድ ቅርስና ውርስ›› በሚል ርዕስ ይስሐቅ ቀለመወርቅ የተባሉ ፀሃፊ ካስቀመጡት ዘለግ ያሉ ፅሁፍ ለዚህ ሃሳቤ የበለጠ ለማጠናከር ይረዳኝ ዘንድ የተወሰነውን መረጃ ቀንጨብ ለማድረግ ወድድኩኝ::

እንደ መረጃው ከሆነ፤ የኢትዮጵያን የደን ልማት ጅማሮ መቼት በእርግጠኝነት ለመናገር አዳጋች ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ይዘትና ቅርጹ ይለያይ እንጂ ነባር የችግኝ ተከላ ባህልና ልምድ አለው። ይህም ሆኖ በሺህ ዘመናት ባለታሪኳ ኢትዮጵያ ደን በመደነን መንግሥታዊ ቁርጠኝነት ወስደው የሠሩ መሪዎችም ነበሯት። ለአብነትም በመካከለኛው እና በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ተሞክሮዎችን ማውሳት ይቻላል ።

ከመካከለኛው ዘመን ታሪክ የኢትዮጵያ ንጉሠ- ነገሥት መካከል አፄ ዳዊት ከ1375- 1404 በነበሩ የግዛት ዘመናቸው ደን ጭፍጨፋና የእንስሳትን አደን ለመከላከል በሀገሪቱ ሰባት የአካባቢ ጥበቃ ጣቢያዎች አቋቁመው እንደነበር ዜና መዋዕላቸው ይናገራል። ልጃቸው አፄ ዘርዓ ያዕቆብም ኢትዮጵያን የደን ካባ ለማልበስ ጥረዋል።

ችግኞችን አፍልቶ የመትከል ሥራዎች ደግሞ በአፄ ልብነ-ድንግል ዘመነ-መንግሥት ስለመጀመራቸው ይወሳል። ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ በሚገኘው የሱባ ደንም ንጉሠ-ነገሥቱ ከወፍ ዋሻ የዛፍ የሱባ/መናገሻ/ ደን ውስጥ ዛፎችን ስለመትከላቸው ይነገራል። በእርግጥ በመካከለኛው ዘመን ደን የመንከባከብና ዛፍ የመትከል ጅማሮ በዘመነ-መሳፍንት ተዳክሟል።

ሌላው በደን ደንና ታሪካቸው የሚነሳው አፄ ምኒልክ ናቸው። የአፄ ዘርዓ ያዕቆብን ‘የንጉሥ ደን ጥብቅ ሥፍራ’ ጽንሰ-ሃሳብን አጠናክረዋል። በዘመናቸው ያጋጠማቸውን ፈተናም ለደን ድነና ተጨማሪ ኃይል የገፋፋቸው ይመስላል። አፄ ምኒልክ የደን የሕግ ማዕቀፍ አውጥተዋል፤ አማካሪም ቀጥረዋል። ደን ሁሉ የመንግሥት ንብረት እንዲሆንም ደንግገዋል። ፈጥኖ-አደግ የዛፍ ዝርያዎችን ከውጭ አስመጥተዋል።

ዛሬ ሀገሪቷን የተቆጣጠረው አውስትራሊያዊው ባሕር ዛፍ (ኢካሊፕተስ) የትመጣነቱ ዳግማዊ ምኒልክ መሆኑ እሙን ነው። አፄ ምኒልክ በመንግሥት ከሚለማው ደን በተጨማሪ ተራው ዜጋ በባለቤትነት በደን ድነና እንዲሳተፍም አዋጅ አውጥተው እንደነበር የመዕዋለ ዜና ዘጋቢያቸው ጸሐፊ ትዕዛዝ ገብረሥላሴ ወልደ አረጋይ ጽፈዋል።

አዋጁም ዛፍ የተከለ የመሬት ግብሩን ምሬዋለሁ የሚል ነበር። ለደን ጨፍጫፊዎችም ንብረታቸውን እንዲወረስና ብርቱ ቅጣት እንዲቀጡ ሕግ አርቅቀው እንደነበር ይወሳል። አፄ ምኒልክ ራሳቸው ከተከሏቸው ችግኞች መካከል በእንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን እና በደቡብ ወሎ ወረኢሉ ከተማ ይገኛሉ።

በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ-መንግሥትም ዛፍ መትከል ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ተግባር እንደነበር ይነገራል። በደርግ ዘመን የተከሰተው ድርቅና ረሃብ ደግሞ በኢትዮጵያ ለሌላ ተጨማሪ የችግኝ ተከላ ዘመቻ መንስዔ ሆኗል። በወቅቱ የተደረገው የተራቆቱ አካባቢዎችን በተለይም ተራሮችን ዛፍ የመትከል ዘመቻ ፍሬ አፍርቷል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አረንጓዴ ኢኮኖሚ እስከማለት ድረስ የዘለቁበትና ለምዕራቡ ዓለም ያስተዋወቁት ፓኬጅም የሚጠቀስ መሆኑን ፀሀፊ ያትታሉ።

በተመሳሳይ መልኩ ከስድስት ዓመት በፊት ወደመነበረ ሥልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አረንጓዴ ኢኮኖሚን፣ የአካባቢ ጥበቃንና የተፈጥሮ ሀብት መንከባከብን ትልቅ ትኩረት ሰጥተውታል። ከትኩረትም በዘለለ የዓለም መገናኛ ብዙሃንን አውታሮችን ቀልብ ሰቅዘው የሚይዙ አይገመቴ ተግባራትን በማከናወን ላይ ናቸው::

ከ2011 የክረምት ወቅት ጀምሮ በየዓመቱ ‹አረንጓዴ ዐሻራ› ገቢራዊ እያደረጉ ይገኛሉ። በመላ ሀገሪቱ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች እያሳተፈ መርሃ-ግብሩ እንደቀጠለ ነው። ኢትዮጵያን በአፍሪካና በዓለም አቀፍ መድረክ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ተምሳሌት ያደረገ ተግባር ነው። አሁን ላይ ደግሞ የችግኝ መትከል ባህል ከመንግሥት ቅስቀሳና ከግለሰቦች ጥረት ባለፈ ሀገራዊ ቅርፅ የያዘ ሲሆን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ትልቁ ማሳያ ነው።

እንግዲህ አሁን በያዝነው በጀት ዓመት በተለይም ከዚህ ሰኔ ወር እስከ ነሀሴ አጋማሽ ድረስ በአረንጓዴ ዐሻራ ላይ ሰፊ ዘመቻ የሚካሄድበት ወቅት መሆኑ ዕሙን ነው:: መንግሥትን ሀገር ልምላሜ ሊኖራት ይገባል በሚል ጠንካራ አቋሙ፤ በአንዲት ጀንበር በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን እየተተከሉ ነው:: የኢትዮጵያ የዕድገትና ብልጽና ምዕራፍ ተለይቶ አይታይም የሚል እሳቤም በማህረሰቡ እንዲሰርፅ ሰፋፊ ሥራዎች ተከናውነዋል:: ‹‹አረንጓዴ ኢትዮጵያ››ን ዕውን ለማድረግም ከገጠር እስከ ከተማ መላው የኢትዮጵያ ዜጎችን የሚያሳትፍ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በትኩረት እየተሠራበት ነው::

በዚህም የተነሳ በሀገሪቱ ያለው የደን ሽፋን ባልተጠበቀ ሁኔታ ምንዳጌ እያሳየ ነው:: ይህ መርሐ ገብር በመኖሩም በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው:: በተለይም የተደራጁ ወጣቶች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሠማርተዋል:: ኢትዮጵያ በማር ምርት፣ የጣውላ ንግድ እና ሌሎች ከደን ከሚገኙ ምርቶችና ውጤቶችም በቅርቡ የትተረፈረፈ ሀብት ባለቤት እንደምትሆንም መረጃዎች ይጠቁማሉ:: ከዚህም በዘለለ ኢትዮጵያ በደን ልማት ከሚገኝ የካርቦን ሽያጭ በሰፊ ተጠቃሚ ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑ አይካድም::

‹‹ከሰው መርጦ ለሹመት፤ ከእንጨት መርጦ ለታቦት›› የሚል ብሂል ይዞ ያደገ ማህበረሰብ በደን ልማት ላይ በዚህ ደረጃ ቢሳተፍ ላያስገርም ይችላል:: ምክንያቱም ጥቅሙን በእውንም በታሪክም ያውቀዋልና:: በበርካታ የኢትዮጵያ ክፍሎች ደን እንኳ በሕይወት እየኖረ ላለ አካል ቀርቶ ለሞት አካልም መድሃኒት ነው ብሎ ይታመናል:: የደን ጥቅም ሕይወት ላለው አካል ጥቅሙ ይህ ነው ተብሎ መዘርዘር አስፈላጊነቱ አይታየኝም- ለሁላችንም ግልጽ ነውና::

አስክሬን የሚከፈነውና የሚቀበረውም በድምር ውጤቱ ሲታይ ችግኝ ተተክሎ ከለመለመ ደን ከሚገኝ ግብዓት ነው:: እንግዲህ ከሕይወት እስከ ሞት የችግኝ ወይንም ደን ውለታ ግልጽ ነው:: ማንም ሰው የሚረዳው ጥሬ ሃቅ ነው::

በመሆኑም በክረምቱ መርሐ ግብር በሚካሄዱ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሮች ሁላችንም ታሪክ የሚያወሳው፤ ብል የማይበላው፣ ሞት የማይሸፍነው ጀብድ እንፈፅም:: እግሮች ሁሉ ወደ ችግኝ ተከላ ሥፍራ፤ እጆች ሁሉ ወደ አረንጓዴ ዐሻራ ያምሩ በሚል መንፈስ ኃላፊነታችንን እንወጣ::

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን  ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You