ጀምበር ግን ታድላ…

ኩርፊያ መልክ ቢኖረው ቁርጥ ሩታን ይሆን ነበር። ጠይም ዘለግ ያለ፣ አይኖቹ ከከዋክብት የተዋለዱ የሚመስሉ፣ ጸጉሩን ቁጥርጥር የተሰራ ኩርፊያ ለንቦጩን ጥሎ ካያችሁ አትጠራጠሩ ሩታን ነው። በዳመነ ፊት ከንፈሩን በጥርሱ እየበላ በአንድ የሆነ ቦታ ላይ የመሸገ ፊት ካያችሁ ሩታ ስትሉ ጥሩት አቤት ይላችኋል። ምን እንደሚያስኮርፋት እንጃ..ነው ወይስ አኩርፋ የተፈጠረች ሴት ትሆን?

የጎረቤቴ ሚስት ናት…ያን ሞገድ አፍ ባሏ አድርጋ መኖሯን ሳስብ በሴት ነፍስ እዝነት ይይዘኛል። ብታዩት እኮ ከመጀመሪያው ሰው መሰል እንስሳ ላመል መለስ ቢል ነው። ከጥቁረቱ መልኩ…የሆነ ዳፍንታም። በውበት የሚበልጣቸው…በውበት የሚበልጣቸው ይኖሩ ይሆን? ጦጣና ዝንጀሮ እንደእሱ ሱፍና ከረባት አድርገው አጠገቡ ቢቆሙ አይደርስባቸውም። በዛ ላይ ኩራቱ…መሬት አይንካኝ እኮ ነው የሚለው። ወንድ ምንም ይሁን በቃ ከሴት አለም ሽቶ የሚያጣው የለም ማለት ነው?

ኩርፊያ አይወድም መሰለኝ ባኮረፈች ማግስት ድራሽ አባቱ ይጠፋል። ጠዋት የወጣ ማታ ነው ቤት የሚመለሰው። ያ ወጥቶ የሚመለስበት ጊዜ ለእኔ በአይነቱ የተለየ ለመቼም የማይዘነጋ ትውስታዬ ነው። ሰው መቼም ካለአንድ አመል አይፈጠር የእሷ ኩርፊያ የእሱ መመነኛ ለእኔ ደግሞ የእግዚኦታ ደብሬ ነው። በድሎት ከማነሳቸው በጎ ገጠመኞቼ መሀል ይሄኛው በሁለት መልኩ ይለያል። የመጀመሪያው በሚስቱ ኩርፊያ ሚስቱን ለማንም ትቶ መሄጃውን የሚሰውር ባል መኖሩ፣ ሌላኛው በባሏ መሄድ ጎረቤቷ ደረት ላይ በምትጽናና ሴት ነው። መቼም ይሄ እድል የእናንተ ቢሆን ቢብስ እንጂ አያንስም።

ሲያስኮርፋት ብን ወደእኔ…እኔም ያለስስት ደረቴን ስጥት። አይኗን ከድና ለጥ ደረቴ ላይ። ገርበብ ያለውን በር መለስ አደርግና በጠባቧ ቤቴ ውስጥ ውብ ሴት ያለችበትን ህልም አልማለው። በዚህ ጊዜም ሆነ ባለፈውና በሚመጣው ጊዜ ውስጥ እንደእኔ ቤት እድል የገጠመው ማነው? በእጆቼ ጸጉሯን እየደባበስኩ እስክትሽር እሽሩሩ እላታለው። የነፍሴን ትርታ እንደማጀቢያ ሙዚቃ ተጠቅሜ፣ በዛ ጅላጅል ባሏ የተሰጠኝን ነጻ ስጦታ እያጣጣምኩ፣ የሆነውንና እየሆነ ያለውን ባለማመን ነፍሴን አርዳለው። አንዳንድ ከእለታት ውስጥ የሚበቅሉ ይሄን መሳይ በእውን ሆነው ህልም የሆኑ ያህል የሚሰሙን ታሪኮች ይበቅሉብናል። ባለጊዜ ሆኜ ለዚህ ክብር ስታጭ አለም ጠበበችኝ። ድንቄም ክብር! አለኝ ውስጤ። የሰው ሚስት ማማገጥ ምኑ ነው ክብር? ላለኝ ውስጤ ‹መጣችብኝ እንጂ አልሄድኩባት ደግሞስ ደረቴን በነጻ ለመጽናኛ መስጠቴ ምኑ ነው ክፉ? ስል አንገት አስደፋሁት።

ወደሥራ ልወጣ በተሰናዳሁበት እና ሁሉ ነገሬን ጨርሼ ስከርቤን አንገቴ ላይ መጣል ብቻ በቀረኝ ማክሰኞ ጠዋት ላይ እንደልማዷ አኩርፋ ወደቤቴ ሰተት አለች። ጠዋት በሆነች ውብ ሴት ኩርፊያና ውበት ስር ምን እንደሚመስል የሚያውቅ ያውቀዋል። ደረቴን ሰጠኋት ወደቀችበት። የባሏ ኮቴ ከውጪው በር ደርሶ በሩን በኃይል ወርውሮ ሲያጋጨው የተሰማው ድምጽ እንደወጣ ቢቀር፣ መኪና ቢበላው፣ የሆነ ጥጋበኛ ማጅራቱን ብሎት ማታ መርዶው በመጣ የሚል እርግማን እንዳወርድበት አደረገኝ። ይሄን ያክል ምን አስጨከነኝ? ለምን ጠላሁት? ራሴን ታዘብኩት።

በባሏ እልህ ይሆን እንጃ ያኮረፈ ፊቷን ከደረቴ ላይ ፈንቅዬ ፊት ለፊቴ አቆምኩት። የብርሀን ግት የሚመስል ኩርፊያ ፊቴ ላይ ዘነበ። ግቱ ሲፈርጥ አራስ ብርሃናት እንደጎርፍ ካፊያ ላዬ ላይ አካፉ። ለዘላለም እንዲያ ሆናና ሆኜ ብንኖር..ተፈጥሮ ለአንድ ጊዜ ተፋልሶ እኔና እሷን በቆምንበት እንዳለንበት ቢረሳን…ቢተወን። እንደእሷ ኩርፊያ ምን የጣፈጠ ቀምሻለው? ምን የጣመ በልቻለው? በልጅነቴ የእናቴ ጡት፣ በአፍላነት የመክሊት ፍቅር፣ በወጣትነቴ ደግሞ የእሷ ኩርፊያ የታሪኬ ሰንበር ሆነው እስከማብቂያዬ ይከተሉኛል።

ኩርፊያዋ የውበቷ ካባ ነው…የሴትነቷ መውዜር። የነፍሷ ነፍስ፣ የአካሏ ጥላ…ተፈጥሮ በውብ ሸምኖ ያለበሳት ቡሉኮ። የአንዳንድ ነፍስ ኩርፊያ እንደታቦት ማደሪያ መንፈስ ቅዱስ የጸለለበት ነው። ከዓለም ውበቶች የሚበልጠውን ይዘው ለፍቅር አበሜኔት የታጩ። ገነት በአንዳንድ ፊቶች ኩርፊያ ጥላ ስር ያለች ትሆን? አልደረስ ያሉ ህልቆ መሳፍር መሻቶች በውብ ሴት ኩርፊያ ጀርባ ያሉ ይሆኑ? እንጃ ብቻ ስታኮርፍና ከማውቀው ነባር ሴትነቷ ስትሸሽ አብራ ወደሆነ የከፍታ ምኩራፍ ታሸሸኛለች። ከነኩርፊያዋ ደረቴ ላይ ተጋድማ ሳያት ገነት ከስረ መሰረቷ ደረቴ ላይ የተገነደሰችብኝ ይመስለኛል። ገነትን የማባብል፣ መንግስተ ሰማያትን የምደባብስ ይመስለኛል።

ያኮረፈ ፊቷን ፊት ለፊቴ አቁሜ ‹ጀምበር ግን ታድላ ሁለት ሀገር አላት…ወጥቶ መግቢያዋ ሁለት ነው› አልኳት በራፌን ጥሳ በገባችው የጠዋት ጀምበር ወሬ እየጀመርኩ።

እንዳልገባው በመሆን ፊቴ ላይ ስትምነሸነሽ…‹በምሥራቅ ጠፍ ስር ተጸንሳ፣ በምድር ወገብ ላይ ብራምባሯን ሰብራ፣ በምዕራብ በኩል ደህና እደሩ ትላለች›። ስል ተነተንኩላት። እያደመጠችኝ እንደሆነ ሳውቅ ‹ምዕራብ መሞቻዋ ይሆን? ከሆነ ደግሞ በምሥራቅ ብቅ አትልም ነበር› ስል ቀላመድኩ።

ፈገግ አለችልኝ። በኩርፊያ ውስጥ ፈገግታ ምን እንደሚመስል ለማየት የታደልኩት እኔ ሳልሆን አልቀርም። በኩርፊያ ውስጥ ፈገግታ እንዲያ መሳይ እንደሆነ አላውቅም ነበር። የእውነት በኩርፊያ ላይ ፈገግታ እንደተሲያት ጥላና እንደ ክረምት ጣይ ልዩ ስሜትን የሚፈጥር ክዋኔ ነው። ጣና ዳር ተቀምጦ ከደማቅ የብርሀን ትውከት ጋር የጀምበርን መሰወር ከማየት ጋር መሳይ ነው። ከሆነ ስሜት ጋር ወደጀምበር መውጫ ሀገር ኮበለልኩ..። ምሥራቅ አድማስ ፀሐይን ሊወልድ ሲያምጥ፣ የምድር ወገብ አራስ ጥየቃ ነጠላ ሲያገድም፣ ምዕራብ በበኩሉ ቄጠማ ሲጎዘጉዝ አለምኩ። አኩራፊዋ ሴት ወደደረቴ ስትከጅል ሊያዘነብል ባለው የጭንቅላቷ ጥላ ታዘብኩ። ከጅላም አልቀረች ትንፋሻችን ተቀላቅሎ በአንድ ሳንባና ጉሮሮ የምንተነፍስ እስኪመስል ድረስ ተጠጋችኝ..። ከደረቴ ዝቅ ብሎ ያለው ቦታ ላይ የጡቶቿ ቀንድ ሲጭረኝ ይታወቀኛል። አንገቴ ግድም የተወችው ሰንፋጭ መዐዛዋ ያናውዘኛል። ደረቴ የአንድ ጎን ምስሏን አትሞ ከወንድነቴ አቆራኝቷታል። ወገቤ ግድም እጇን ተወናግሮ ሳየው የምናገረው አጣሁ። አመጣጧ ለማረፍ እንዳይደለ ገባኝ። ከንፈሯ ደርቆ፣ ውብ ፊቷ ጠውልጎ ሳያት ደግሞ ከባሏ ሽሽት እኔ ቤት መምጣቷ እና ደግሞ እዚህ ደረት ላይ ምን ፈልጋ እንደምትወድቅ እየገባኝ መጣ። ቀርፋፋ ነኝ መቸኮል አልችልበትም። በእንቁርስሴ ብዙ የባከኑ እድሎች አሉኝ። በጓደኞቼ ዘንድ እድሎቼን ባለመጠቀም እታወቃለሁ…።

ባለማፈር፣ ከየት እንደመጣ በማላውቀው ድፍረት ከንፈሯ ላይ ሰነበትኩ..በደንብ አየኋት። አይን ለአይን መተያየት ያለው የሞገድ ኃይል እንደዛ ነው? መተያየት ያን ያክል የኤሌክትሪክ ሜጋ ዋት እንደተሸከመና ከመነካካትና ከመዳራት እኩል ስሜት ያለው ተፈጥሮ እንደሆነ አለማወቄ ከሴት የተገለልኩ እንደሆንኩ እንዳስብ ከማድረግ ባለፈ ከዛን መሳይ ስሜት መራቄ ቁጭትን ፈጠረብኝ። በዚህ ቀን ላይ በዚች ሴት ታሪኬን ለመቀየር ስል ይሆን አላውቅም ከዓለም ደፋሩን ሴት አውል ሆኘ አይኗ ስር ተገኘሁ። ውብ ናት…ሁሉም ሰው በእኩል የሚስማማበት ውበት አላት። ለውበቷ ድምቀት የሆነ የፊቷን አንድ ሦስተኛ የያዘ አይን አላት። ማንም ስለእሷ እርግጠኛ ሆኖ ከሚናገረው ውስጥ አንዱ የአይኗ ውበት እና ሌላው ደግሞ በኩርፊያ ውስጥ የሚገዝፍ ቁንጅናዋ ነው። ለሁለቱም መመረጤን ሳስብ ከወንድ እኔ እንደገና ከወንድ ያ ለንቦጫም ኩታራ ባሏ የፍቅር ጀብደኞች መሆናችን መጣብኝ። ፍቅርሽ የምሞትለት አላማዬ ነው፣ ነፍሴ ግዛቷ አድርጋሽ ሰንደቅሽን ተክላለች፣ የትኛውም ምድራዊ ኃይል ከአንቺ አያርቀኝም› ልላት ከአፌ ላይ መለስኩት..። የሰው ሚስት እንዲህ ትባላለች? ወደድኩህ አላለችኝ…ኩርፊያዋን በደረቴ ለመሻር ተጠጋችኝ እንጂ!

በትንፋሷ እየሞቅኩ ወገቤ ላይ ተጣብቃኝ ሳገኛት የሆነ ድፍረት ወደከንፈሯ እንድንደረደር አስገደደኝ…። ላድርገው አላድርገው ስል አመት የሰነበትኩ ይመስለኛል..በስተመጨረሻ…

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You