ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው የወርቅ ክምችት እንዳላት ይነገራል። በሀገሪቱ እስካሁን በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ከ517 ቶን በላይ የወርቅ ክምችት መኖሩ ተረጋግጧል። ይሁን እንጂ ይህን ሀብት በማልማት ጥቅም ላይ እንዲውል የማድረጉ ሂደት እምብዛም አልተሠራበትም። አሁን ላይ ግን መንግሥት ለማዕድን ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ ሥራዎች እየተሠሩ በመሆናቸው መሻሻሎችና ለውጦች እየመጡ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።
በተለይ በማዕድን ልማት ላይ ተሠማርተው የሚሠሩ ኩባንያዎችና ተቋማት ሀብቱን ከማልማት አንጻር ሥራዎች እየሠሩ ይገኛል። የኢትዮጵያ ማዕድን ኮርፖሬሽን በማዕድን ልማት ዘርፍ ተሠማርተው ከሚሠሩት ተቋማት መካከል ተጠቃሽ ነው። ኮርፖሬሽኑ የረጅም ጊዜ ልምድ ስላለው የተለያዩ ማዕድናትን እያመረተ ይገኛል። በተለይ ሜታሊክ ሚኒራል ከሚባሉት ውስጥ ወርቅ በማምረት ረገድ በርካታ ሥራዎች በመሥራት ላይ ይገኛል።
አቶ ሳዲቅ ከቢር የኢትዮጵያ የማዕድን ኮርፖሬሽን ከፍተኛ የማዕድን ባለሙያና የሥነ ምድር ተመራማሪ (ጂኦሎጂስት) ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ ኮርፖሬሽኑ በማዕድን ዘርፍ የታወቀና ትልቅ ሥራን ሲሠራ የቆየ ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያት በሀገር ደረጃ በሜታሊክ ሚኒራል ማዕድናት ዘርፍ ትልቅ ልምድ ካላቸው ተቋማት አንዱ ነው። ባለፉት ዓመታት ከነበረው ለውጥ ጋር ተያይዞ ሲሠሩ የነበሩት ሥራዎች የተቀዛቀዙ ቢሆንም የተለያዩ አማራጮችን በመውሰድ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።
ኮርፖሬሽኑ በተለይ በኢትዮጵያ የታወቀ የታንታለም ማዕድን ብቸኛ አምራች እንደነበር ጠቁመው፤ በኦሮሚያ ክልል ጎጂ ዞን የታንታለም ማዕድን ሲያመርት ቆይቶ በተለያዩ ምክንያቶች ማምረት ካቆመ ሰባት ዓመት በላይ መሆኑን አቶ ሳዲቅ ይናገራሉ።
ኮርፖሬሽኑ በተለይ የወርቅ ማዕድን ለማምረት የተለያዩ አማራጮችን ወሰዶ በርካታ ሥራዎች እየተሠራ መሆኑን ያመላክታሉ። በጋምቤላ ክልል 100 እስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታ ላይ ጥናት ለማድረግ ፈቃድ ወስዶ ጥናት እያካሄደ ሲሆን፤ በዘንድሮ ዓመትም ሁለተኛ ዙር ጥናት የተካሄደ መሆኑን ይገልጻሉ።
እንደእሳቸው ማብራሪያ፤ ወርቅ ጽንሰ ወርቅ እና ደለል ወርቅ ተብሎ በሁለት ዓይነት መንገድ ይጠናል። ጽንሰ ወርቅ በጣም ወደታች ተገብቶ የሚወጣና ተፈጭቶ በትልቅ ቴክኖሎጂ የሚመረት ነው። ደለል ወርቅ ግን ከላይ ያለው ድንጋይ በተለያዩ ምክንያቶች ሲበሰብስና ሲፈረካከስ ከዚያ ውስጥ ሊወጣ የሚችል የወርቅ አይነት ነው። ወርቅ አብዛኛውን ጊዜ ከተራራ የሚገኝ ሲሆን፤ በውሃ ወይም በንፋስ ዝቅ ወዳለ ቦታ እየሄደ ይመጣና ይከማቻል ይህ ሲሆን ደግሞ በአነስተኛ ቴክኖሎጂና በትንሽ ወጪ ሊመረት ይችላል።
ኮርፖሬሽኑ ጋምቤላ ክልል ሁለቱንም አይነት ወርቅ ለማምረት እየሠራ መሆኑን አቶ ሳዲቅ አመላክተዋል። ከዚህ በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ከአነስተኛ የወርቅ አምራች ማኅበራት ጋር አብሮ በመሥራት ቴክኖሎጂና ወጪውን በመሸፈን በሰፊው እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቅርቡም ደለል ወርቅ ማምረት እንደሚጀምር ይገልጻሉ። በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንደዚህ አይነት ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አስታወቀዋል።
ኮርፖሬሽኑ በወርቅ ማዕድን በጋምቤላ፣ በኦሮሚያ ክልል እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ ሰፋፊ ሥራዎች እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ በጉጂ ዞን 500 በላይ ሠራተኞች፣ ሰፊ ቦታዎች እና ወርክሾፖች ስላሉት በስፋት እየሠራበት እንደሚገኝ ገልጸዋል። በመመሪያ ደረጃ ደለል ወርቅ የሚያመርት ቢሮም ስላለው ሥራው በሰፊው ስለሚሠራ ይህን ለማሳለጥ ያስችል ዘንድ ከኦሮሚያ ማዕድን ቢሮ ጋር ለመሥራት ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
በተመሳሳይ እንዲሁ ታንታለም በማምረት ረገድም አሁን ላይ በጉጂ ዞን ታንታለም የሚያመርቱ ብዙ አነስተኛ አምራች ማኅበራት ያሉ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኮርፖሬሽኑ ከእነዚህ ማኅበራት የታንታለም ማዕድን በመግዛት ለውጭ ገበያ ለመላክ የሚያደርገውን ዝግጅት እያጠናቀቀ ይገኛል ብለዋል። በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ የተሟላ የሰው ኃይልና ቴክኖሎጂው ስላለው ቀደም ሲል ታንታለም ያመርትበት በነበረው ቦታ በድጋሚ እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ ማዕድን በሕገወጥ መልኩ ከሀገር ከሚወጣና ከሚባክን በሚል ማዕድኑን በመግዛት ወደውጭ በመላክ ገቢን የማስገኘት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ያስረዳሉ።
የሜታሊክ ሚኒራል ኮፐር፣ የብረት ማዕድን እና የመሳሰሉ ማዕድናትንም ይይዛል። ከዚህ ውስጥ አንዱ የሆነው የኮፐር ማዕድን በቤንሻንጉል ክልል አለ እየተባለ መሆኑን የገለጹት አቶ ሳዲቅ፤ ኮርፖሬሽኑ ወደ ክልሉ በመሄድ ለጥናት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።
እንደሳቸው ማብራሪያ፤ በዘንድሮ በጀት ዓመት በማዕድን ዘርፉ በጋምቤላ ክልል ጽንሰ ወርቅና ደለል ወርቅ ለማግኘት ጥናቶች ተደርገዋል። የደለል ወርቅ የሚባል በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊመረት የሚችል የወርቅ አይነት ሲሆን፤ በጥናቱ መሠረት በሚቀጥለው ዓመት ሥራ የሚጀመርበት የተባለ ሦስት እስኩየር ኪሎሜትር ቦታ ተለይቷል። ከዚህም 200 ኪሎግራም ወርቅ ይገኛል ተብሎ ተገምታል። ይህንንም ለማዕድን ሚኒስቴር በማሳወቅ የማምረት ፈቃድ ለማግኘት ጥያቄ በማቅረብ እንደተፈቀደልን ወደ ሥራ የሚገባ መሆኑን አመላክተዋል።
‹‹አሁን ላይ ያለው የወርቅ አመራረት ሂደትም ሆነ ከተመረተ በኋላ ያለ ሕገወጥነት መንግሥት ከዘርፉ ሊያገኝ የሚገባው ጥቅም እንዳያገኝ እያደረገ ነው። በመሆኑም ኮርፖሬሽኑ ሥራውን ቢጀምር ይህ ችግር የሚቀረፍ በመሆኑ ፈቃዱ በአጭር ጊዜው ውስጥ እንደሚፈቀድና በሚቀጥለው ዓመት ወደ ምርት እንገባለን ብለን እናምናለን›› ሲሉ ተናግረዋል ።
ጉጂ ዞን ባቢቹ ቁሊንሱ በሚባል ቦታ ላይ ከተደረገው ጥናት የተገኘው ውጤት አዋጭ በመሆኑ በዚህ ወር ከማኅበራት ጋር በመሆን የሚሠራው ወርቅ ማምረት ሥራ ይጀመራል ያሉት አቶ ሳዲቅ፤ አክለውም እዚያ በጉጂ ዞን በሌላ ሁለተኛ ቦታ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል። ጥናታቸው የተጠናቀቁ ማዕድናት ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ መመሪያው ዝግጅት ተጠናቀቆ በሚቀጥለው ዓመት ሥራው እንደሚጀመር ነው ያመላክቱት።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ የደለል ወርቅ ጊዜያዊ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ሊያልቅ የሚችል ነው። ትልቅ የሚባል ፅንሰ ወርቅ ነው። አሁን ላይ ያለው መረጃ እንደሚያሳየው የደለል ወርቅ በዚህ ደረጃ አለ ማለት ትልቅ ክምችት ያለው ፅንሰ ወርቅ እንዳለ አመላካች ነው። ፅንሰ ወርቅ በጥልቀት በትልቅ ቴክኖሎጂ እና ረጅም ጊዜ (ለ30፣ ለ40 እና ለ50 ዓመታት) የሚፈለግ ነው። ያለው ክምችት ቀላል የሚባል እንዳልሆነና ድንጋዮች ሲመረመሩም ጥሩ ውጤት መኖሩን ጥናቶች አመላክተዋል።
‹‹ፅንሰ ወርቅ ሲባል ቀላል አይደለም፤ በኢትዮጵያ ደረጃም ሊሠራ የሚችል አይደለም። እኛ እነዚህን ውጤቶችና ያለውን ሀብት ይዘን የውጭ ድርጅት ነው የምናፈላልገው። የውጭ ድርጅት ሲመጣ ቴክኖሎጂ፣ መሠረተ ልማት እና በጀት ይዞ ስለሚመጣ ከእነርሱ የሚወሰድ ትልቅ ልምድ አለ። ስለዚህ ፅንሰ ወርቅ ላይ የመጀመሪያ ሥራ እየተሠራ ነው›› ብለዋል።
200 ኪሎግራም የሚገመት ወርቅ የተገኘው በትንሽ ቦታ ላይ ነው። ወደፊት ደግሞ ባለው 100 እስኩየር ኪሎሜትር መሬት ላይ ሲሠራ የተሻለ ነገር ይገኛል። ይህ በመንግሥት ደረጃ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን አቶ ሳዲቅ ይገልጻሉ።
‹‹ኮርፖሬሽኑን ከችግር የሚያወጡትና ገቢ የሚያስገኙለት ማዕድናት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው›› ያሉት አቶ ሳዲቅ፤ አሁን ላይ የኮርፖሬሽኑ ትልቁ ገቢ የሚገኘው የኢንዱስትሪ ማዕድን ከሆነው ካኦሊን ምርት መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይ የወርቅ ማዕድን ማምረት በጣም አዋጭ እንደሆነ ይገልጻል። በመሆኑ የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል በሚቀጥለው ዓመት ከወርቅ ምርት ጥሩ ውጤቶች ማግኘት እንደሚቻል አስታውቀዋል።
አቶ ሳዲቅ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ብዙ የወርቅ ማዕድን ክምችት ያለባት ቦታ ስትሆን ማዕድን ዘርፉ ላይ ለመሰማራት ብዙ መልካም የሚባሉ ነገሮች አሏት። ከእነዚህ መካከል አንደኛው ጥናት የሚካሄድበት ቦታው ላይ የሚገኘው ድንጋይ የወርቅ ክምችት የሚታይበት መሆኑን ነው። ሁለተኛው ወርቅ ማዕድን ከተገኘ በኋላ በአካል ሆነ በላብራቶሪ የሚፈተሽበት ሁኔታ መኖሩ ነው። በዚህም ኮርፖሬሽኑ በራሱ ላብራቶሪ ማዕድናት እንዲፈተሹ የሚደረጉ መሆናቸው ባለፉት ጊዜያት ከተለያዩ ቦታዎች የተሰበሰቡት ማዕድናት ተመርምረው ጥሩ አመላካች ውጤት ታይቶባቸዋል።
የማዕድን ዘርፉ ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ እንዲሆን መደረጉ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ነው ያሉት አቶ ሳዲቅ፤ ይህ ደግሞ ዘርፉ ትኩረት አግኝቶ አስፈላጊው ሥራ እንዲሠራበት ያስችላል። ኮርፖሬሽኑም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ስር ትልቅ ገቢን ያመነጫሉ ተብሎ ከተለዩት ዘርፎች መካከል አንዱ ነው። ስለሆነም የቅርብ ክትትልና በፋይናንስ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ብዙ ሥራ እንዲጠበቅበት ያደርገዋል ብለዋል።
አቶ ሳዲቅ በሀገሪቱ የማዕድን ሀብቱ በብዛት ያለ ቢሆንም እስካሁን ብዙ ያልተሠራበት መሆኑን ይናገራሉ። አሁን ላይ ኮርፖሬሽኑ በዚህ ዘርፍ ያለውን ልምድ ተጠቅሞ አቅሙ፣ ሙያው፣ ካፒታሉ እና የውጭ ትልልቅ ኩባንያዎች ጋር ግንኙነት አጠናክሮ ብዙ ሥራዎች ለመሥራት አቅዶ እየሠራ መሆኑን አመላክተዋል።
የማዕድን ዘርፉ ብዙ ተግዳሮቶች ያሉበት በተለይ ማዕድናቱ በሚወጣባቸው አካባቢዎች ላይ በእጅጉ ፈታኝና ቢሮክራሲ የሚበዘባቸው ናቸው ያሉት አቶ ሳዲቅ፤ በክልሎች በመንግሥት ዘርፍ ለተሠማሩ ማዕድን አምራች ድርጅቶች ላይ የሚደርሰው ችግር ውስብስብ ስለሆነ ጫናው ይበዛል፤ ችግሮችን በቀላሉ መፍታት አይቻልም ይላሉ። በተጨማሪም በፌዴራል ደረጃ ፈቃድ በመውሰድ ክልል ሲኬድ ከክልሉ ተፈቅዶ ወረዳ ማዕድኑ በሚገኝበት ቦታው ላይ ለመግባት አላስፈላጊ ጥቅም የሚፈልጉ አንዳንድ አካላት የሚከለክልበት ሁኔታዎች ስላለ ይህ ደግሞ መንግሥት ለማዕድን ዘርፉ በሰጠው ትኩረት ልክ ለመሥራት አስቸጋሪ ያደርገዋል። በመሆኑም እንደመንግሥት ከላይ ጀምሮ እስከታች ድረስ ብዙ ሥራዎች መሥራት ያለባቸው መሆኑን ገልጸው፤ ኮርፖሬሽኑ በማዕድን ዘርፍ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆኖ ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነ ያስረዳሉ።
በተመሳሳይ የወርቅ ማዕድን አብዛኛውን ጊዜ የሚገኙበት ቦታ ርቀት ያላቸው ጠረፍ የሚባሉ አካባቢዎች እና አስቸጋሪ ቦታዎች ላይ በመሆኑ ከፀጥታ ጋር የሚያያዙ ችግሮች መኖራቸው ይጠቁማሉ። አሁን ላይ ግን የተሻለ መረጋጋትና ሠላም ሰላለ ለማዕድን ሥራው የተሻለ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
ችግሩን ለመፍታት ክልሎች ጋር በመተባበር እነዚህ አካላት ላይ ትኩረት በማድረግ ግንዛቤ እንዲፈጥሩ የሚያደርግ ሥራ በመሥራት ተገቢው ድጋፍና ትብብር እየተደረገ መሆኑን አቶ ሳዲቅ ተናግረዋል። ይህ ሲሆን ደግሞ ወርቁ በትክክል ይመረታል ተመዝኖ በሕጋዊ መንገድ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ እና ሁሉም የአካባቢ ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በማስፋት ረገድ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የማዕድን ዘርፉ በሕገወጥነት እየተሰፋፋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይህን ድርጊት የሚፈጸሙ ግለሰቦችን ወደ ሕጋዊነት ለማምጣት የሚሠሩ ሥራዎች እንዳሉ ሆነው ትልልቅ አቅም ያላቸው ኩባንያዎች እንዲሳተፍ ቢያደርግ የተሻለ ውጤት ማግኘት እንደሚቻል ነው አቶ ሳዲቅ የሚያመላክቱት።
በሌላ በኩል ማዕድን ዘርፉ ከላይ ጀምሮ ድጋፍ እና እገዛ እየተደረገበት መሆኑ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመው፤ ኮርፖሬሽኑ በማዕድን ዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችን በመፍታት ከክልሎች ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እየሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል። ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሠራ በመሆኑ ለሥራዎቹ እገዛ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። በአጠቃላይ ኮርፖሬሽኑ በማዕድን ዙሪያ በሚሠሩ ሥራዎች ዙሪያ ካሉ አጋርና አጋዥ አካላት ጋር በትብብር መሥራት ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ ለመሥራት አስችሏታል ሲል አስገንዘበዋል።
እንደ አቶ ሳዲቅ ማብራሪያ፤ ኮርፖሬሽኑ በሚቀጥለው በጀት ዓመት የያዛቸው ሰፊ ሥራዎች አሉ። የደለል ወርቅ ወደ ማምረት ሥራ የሚገባ ሲሆን፤ ሻኪሶ ባለው ወርክ ሾፕ የወርቅ ማጠቢያ ማሽኖች እየተሠራ ነው። ቢያንስ ሦስት ማጠቢያ ማሽኖችን በመትከል የማልማት ሥራዎች ይሠራሉ። የጽንሰ ወርቅ ጥናት ሥራውን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። ይህም በጥልቀት የሚቆፈር፣ ብዙ ወጪው የሚጠይቅ እና ከአቅም በላይ ስለሚሆን የውጭ ድርጅት በማፈላለግ የሚሠራ መሆኑን አመላክተዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም