የተለያዩ የማኅበራዊ ሳይንስ መረጃዎች ወጣት የሚለውን ፅንስ-ሃሳብ የእድሜ ክልልን መሠረት አድርገው ሲተነትኑ ይስተዋላል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ እድሜንና የትምህርት ደረጃን መሠረት በማድረግ የወጣትነትን ክልል ይወስናሉ፡፡ በኢትዮጵያ በ1996 ዓ.ም የወጣው ብሔራዊ የወጣቶች ፖሊሲ ከ15 እስከ 29 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘውን የኅብረተሰብ ክፍል ወጣት ብሎ ይደነግጋል፡፡
ወጣቶች አፍላ የልማትና የዴሞክራሲ ኃይሎችና ሀገር ተረካቢ ዜጎች ናቸው፡፡ በትምህርት የታነፀና የተገነባ አቅም ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የማኅበራዊ ሳይንስ ምሑራን ወጣትነት ቅን አመለካከት የሚስተዋልበት፤ አካላዊና አዕምሯዊ ችሎታና ብቃት የሚዳብርበት፤ በጥንካሬ የታጀበ እና ለሥራ ምቹ፤ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ አቅም ነው ይላሉ፡፡ እናም፤ ወጣቶች አፍላ ኃይል በመሆናቸው ፖሊሲዎችና በዕቅዶች ዝግጅት ተሳትፈው መወሰን ከቻሉ እና የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ በመንግሥትና በሚኖሩበት ማኅበረሰብ እውቅና ከተሰጠው ትልቅ ሚና ያላቸው ሰብዓዊ ሀብቶች ናቸው በማለት ወጣትነትን ይገልጻሉ፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገት የማይተካ ድርሻ ያላቸው እንደመሆኑ በተለያዩ ዘርፎች የሚኖራቸው ተሳትፎ ማደግ እንዳለበት ብዙዎች ይናገራሉ።
በቅርቡ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ጋር በመተባበር የታዳጊ ወጣቶች እና ወጣቶች ዲጂታል ተሳትፎ መድረክ የሆነውን ዩ-ሪፖርት የተሰኘ የአፕ መተግበሪያ ይፋ አድርጓል። መድረኩ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በተገኙበት ነው በይፋ የተጀመረው። በተጨማሪም አቡባካር ካምፖ (ዶ/ር)፣ የዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ተወካይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የለጋሽ ማኅበረሰብ አባለት፣ የሲቪል ማኅበራትና፣ ወጣቶች በመድረኩ ተገኝተዋል።
እኤአ በ2011 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በዑጋንዳ የጀመረውና በአሁኑ ወቅት ከ 90 በላይ ሀገራት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ 35 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን ማፍራት የቻለው ይህ መተግበሪያ፤ ታዳጊዎች እና ወጣቶች በሚመለከቷቸው ጉዳዮች ላይ እንዲናገሩ እና ጠቃሚ የሕይወት አድን መረጃዎችን እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ተብሏል። ላለፉት 13 ዓመታት ዩ-ሪፖርት ከተለያዩ አካላት ጋር በሠራው ሥራ ለውጥ ማምጣት መቻሉም ተገልጿል።
መተግበሪያውን ይፋ ያደረጉት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፥ መተግበሪያው የሀገራችን ወጣቶች በተለይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሀሳባቸውን በነፃነት እንዲለዋወጡ እና ወቅታዊ መረጃ እንዲያገኙ ያግዛል ብለዋል። በተጨማሪም ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን ከወጣቶቹ ለማሰባሰብ የሚያስችል ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
የወጣቶችን ድምፅና ሃሳብ የምንሰማበት ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ ወጣቶች መተግበሪያውን በመጠቀም ለዘላቂ ሠላምና ፀጥታ እንዲሁም ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በተለይ በአሁኑ ጊዜ ሀገራችን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም ለማስፈንና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በጥልቀት እየመከረች የምትገኝ ወቅት በመሆኑ ወጣቱ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል። ወጣቶች መተግበሪያውን ፍሬያማ በሆነ መንገድ፣ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እንዲገለገሉበትም በአፅንዖት አሳስበዋል።
ኤርጎጌ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ ይህንን መተግበሪያ ጥቅም ላይ እንዲውል ስታደርግ ሌሎች ሀገራት ያላቸውን ተሞክሮ በማየትና ምን ያህል መንግሥት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎችን ለመቅረጽ ይረዳል? የሚለውን ከሚመለከታቸው ሌሎች የመንግሥት ተቋማት ጋር ማለትም ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እንዲሁም ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ጋር ተደጋጋሚ ውይይት በማድረግ ወደ ሥራ እንዲገባ ስለመደረጉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ቁጥር 70 በመቶ የሚሆነው ወጣት እንደሆነ የተነገሩት ኤርጎጌ(ዶ/ር)፤ የዚህ ወጣት ድምፅ ተሰሚነት ሊኖረው እንደሚገባ ገልፀው፤ በተለይ ፖሊሲ አውጪ የሆኑ አካላት ወጣቱ የሚፈልገውን ነገር በመለየት ለተግባራዊነቱ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ዶክተር ኤርጎጌ፤ ዩ-ሪፖርት ወጣቶች በራሳቸው በአካባቢያቸው የሚያዩትን ችግር ለመፍታትና እንደ ወጣት ከፍተኛ ችግር ሆነው ያሉ ጉዳዮችን ለሚመለከታቸው አካላት እንዲያቀርቡና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ይህንን መሠረት አድርገው የተለያዩ ሥራዎችን እንዲሠሩ በዚህም የወጣቱን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዲችሉ አቅጣጫ እንደሚሰጥ ይናገራሉ።
የዩ ሪፖርት መተግበሪያ ወጣቱን በተመለከተ የተለያዩ ጥናቶችን ለመሥራት የሚወስደውን ረዥም ጊዜ በማስቀረት በአጭር ግዜ የወጣቱን የልብ ትርታ ማየትና ማወቅ የሚቻልበትን መንገድ እንደሆነ የሚናገሩት ሚኒስትሯ፤ መተግበሪያው ወጣቶች ድምፃቸውን ከማሰማት ባሻገር በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ተሳታፊ ሆነው ከመንግሥት ጋር በቅንጅት እንዲሠሩ የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል።
በተለይ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ አካታች ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ እንቅስቃሴ እያደረገች ባለችበት ሰዓት የወጣቱ ድምፅ የሚሰማ መሆኑን እርግጠኛ መሆን ይኖርብናል የሚሉት ክብርት ሚኒስትሯ፤ ቴክኖሎጂው ሀገራዊ ምክክሩን ጨምሮ በትምህርት፣ በጤና፣ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የወጣቶችን ተሰሚነት የሚያሳድግ ነው ይላሉ።
እስከአሁን ከአስራ ሦስት ሺህ በላይ በዚህ መተግበሪያ የተመዘገቡ ወጣቶች አሉ የሚሉት ኤርጎጌ (ዶ/ር)፤ ማኅበራዊ ሚዲያው ትክክለኛ ባልሆኑ መረጃዎች በተሞላበት በዚህ ወቅት ይህ ቴክኖሎጂ መኖሩ ትክክለኛ መረጃ በመለዋወጥ ማኅበረሰብን ለመለወጥ የሚሠሩ ሥራዎችን በመደገፍ የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ እንደሆነ ይናገራሉ።
እንደ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን ለማሳለጥ፣ የወጣቱን ስብዕና ለመገንባትና ከአልባሌ ሱሶች ተላቀው አምራች ዜጋ መሆን እንዲችሉ የተለያዩ ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችል የቴክኖሎጂ አማራጭ ይዞ የመጣ ነው ይላሉ።
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢ የሚገኙ ወጣቶች ስለቴክኖሎጂው መረጃ አግኝተው መጠቀም እንዲችሉ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የኢትዮጵያ ወጣቶች ካውንስልን ጨምሮ ከተለያዩ አጋር አካላትና ሚዲያዎች ጋር ሰፊ ሥራዎችን የመሥራት እቅድ እንዳለው የሚናገሩት ዶክተር ኤርጎጌ፤ በዚህ ረገድ የሚዲያ ተቋማት ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በጋራ ለመሥራት ዝግጁ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት የሚችሉ ሁሉም ወጣቶች በዚህ መተግበሪያ አማካኝነት ሀሳባቸውን መስጠት እንደሚችሉ የሚናገሩት ኤርጎጌ (ዶ/ር)፤ ወደዚህ ቴክኖሎጂ የሚቀላቀሉ ወጣቶች በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት የራሳቸውን ድርሻ ማበርከትና ድምፃቸውን ማሰማት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ይህ መተግበሪያ በተለያዩ ሀገራት ጥቅም ላይ ውሎ የአመለካከትና የዕድሜ ልዩነት ውስጥ ያለውን ወጣት ማለትም ሴት ወጣቶች፣ አፍላ ወጣቶች፣ በሱስ ውስጥ ያሉ ወጣቶች፣ የጤና እክል የሚገጥማቸው ወጣቶች፣ የአካል ጉዳተኛ ወጣቶች፣ በገጠርና በከተማ ያለ ወጣት በአጠቃላይ በዘርፈ ብዙ የሕይወት ልምምድ ውስጥ ያሉ ወጣቶችን እንዴት መስተዳደር እንዳለባቸው ትምህርት የሰጠ ቴክኖሎጂ ነው ያሉት ኤርጎጌ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያም ይህንን ልምድ በመቅሰም ሥራ ላይ እንዳዋለችው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ አቡባካር ካምፖ (ዶ/ር) በመድረኩ እንደተናገሩት “ወጣቶች በማንኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ አዎንታዊ እድገት ለማምጣት ትልቅ አቅም እንዳለቸው ገልፀው “በትምህርት፣ በክህሎት ግንባታ እና ምቹ አካባቢን በመፍጠር ዩኒሴፍ ከመንግሥታት እና ከሌሎች አጋሮች ጋር በመሆን ወጣት ኢትዮጵያውያን ሙሉ አቅማቸውን ጥቅም ላይ እንዲያውሉና ለማኅበረሰባቸው ትርጉም ያለው አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ያደርጋል ብለዋል።
አቡበከር (ዶ/ር) ‘U-Report Ethiopia’ ለአጠቃቀም ምቹና ቀላል የአፕ መተግበሪያ ሲሆን በ99 የዓለም ሀገራት ተግባራዊ ሲደረግ የነበረ መሆኑንና ኢትዮጵያን 100ኛ ሀገር ሆና መቀላቀሏን ገልጸዋል። አብዛኛው ወጣት የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግና ለማብቃት ታስቦ መዘጋጀቱንና ወጣቶችም በንቃት እየተሳተፉበት ያለ ውጤታማ መተግበሪያ ለመሆኑ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በማሳያነት አቅርበዋል።
አብዛኛው ወጣት የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግና ለማብቃት ታስቦ መዘጋጀቱንና ወጣቶችም በንቃት እየተሳተፉበት ያለ ውጤታማ መተግበሪያ ለመሆኑ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በማሳያነት አቅርበዋል።
ተወካዩ በተጨማሪነት መድረኩ የጤና መረጃን ለማሰራጨት እና ግንዛቤን ለመፍጠር በተለይም በበሽታዎች ወቅት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል ያሉ ሲሆን ለምሳሌ በዛምቢያ በዩ-ሪፖርት ተፅዕኖ ምክንያት በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የኤችአይቪ ምርመራ መጠን ከ24 በመቶ ወደ 40 በመቶ ጨምሯል። የወጣቶች ድምፆች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሰሙ ነው፣ ተቋማዊ ተግባራት ላይ በጎ ተፅዕኖ እያሳደሩ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል።
በመጨረሻም ክብርት ሚኒስትሯ ለመተግበሪያው እውን መሆን ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ዩኒሴፍ እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ሌላው የመተግበሪያ ማስተዋወቂያ መድረክ አስተባባሪና የኮሚቴ አባል የሆነው ወጣት ጉዲሳ እንደሚናገረው፤ ኢትዮጵያ ሰፊና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት የሚኖርባት ሀገር እንደመሆኗ ቴክኖሎጂው በየአካባቢው ያለው ወጣት በተለያዩ ጉዳዮች ማወቅ ያለበትን ነገር እንዲያውቅና ፍላጐቱን፣ ስሜቱን፣ እንዲገልጽ የሚያስችል መተግበሪያ እንደሆነ ይናገራል።
ለአብነት ስለሀገራዊ ምክክሩ ወጣቱ ምን ያህል ግንዛቤ አለው በሚል ጥያቄ በመውጣት የወጣቶችን ሀሳብ ለማዳመጥ ሙከራ ተደርጎ እንደነበር የሚናገረው ጉዲሳ፤ ስለ ምክክር ሰምቷል ወይ? ምን ተሳትፎ እያደረገ ነው? ስለ ምክክሩ ጠቀሜታ ምን ያህል መረዳት አለው? የሚለውን ይህ መተግበሪያ በቁጥርና በዳታ በመለየት አስፈለጊ መረጃ መስጠት የሚችል ነው ይላል።
ይህንን መተግበሪያ በመጠቀም ከወጣቶች የሚመጡ ምላሾችን በመውሰድ ወጣቱ ምን ያሳስበዋል? ምን አይነት ትኩረት ይፈልጋል? የሚለውን የተለያየ ዳታ በመሰብሰብ ለውጥ እንዲመጣ እንሠራለን የሚለው ጉዲሳ፤ ይህ ሥራ ከተሠራ በኋላ ሪፖርት በማውጣት ለሚመለከታቸው የፖሊሲ አውጪዎች በማጋራት የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚውል ይናገራል።
በተለያዩ ክልሎች በመሄድ ስለ መተግበሪያውን ምንነትና ጠቀሜታ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በቀጣይ እንደሚሠራ የተነገረው ጉዲሳ፤ በሂደት ቴክኖሎጂውን በመላው ሀገሪቱ በማላመድ ወጣቶችን በሚመለከት የትኛውም ፖሊሲ ከመውጣቱ በፊት የጉዳዩ ባለቤት የሆኑ ወጣቶች ሀሳብ እንዲሰጡ ማድረግ እንዲቻል ዕድል የሚሰጥ ነው ይላል።
ወጣቶች ዩ-ሪፖርትን በበርካታ ማኅበራዊ ሚዲያዎች፣ በቴሌግራም፣ በዋትስአፕ እና በፌስቡክ በኩል ማግኘት ይችላሉ የሚለው ጉዲሳ፤ በተለያዩ ጉዳዮች ጥያቄዎች ተዘጋጅተው ምን ያህል ወጣቱ ስለ ጉዳዩ ግንዛቤ አለው የሚለውን በመለየት የመፍትሔ ሀሳብ ለማምጣት እንደሚረዳ ተናግሮ፤ ወጣቶች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል።
ክብረዓብ በላቸው
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም