ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው!

የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዋነኛ ዓላማ በሀገሪቷ ብቁ፣ ተነሳሽነትና የፈጠራ ክህሎት ያለው የሰው ኃይል በመፍጠር ዕድገትና ብልጽግናን ማረጋገጥ ነው። ሥራ ፈላጊ ሳይሆን ፈጣሪ ዜጋም ማፍራትም ነው። ዘርፉ ጊዜው የሚፈልገውን የሰለጠነ ሰው ኃይል ለገበያ በማቅረብና ፈጠራም በማበረታታት የማይተካ ሚና ይጫወታል።

ቴክኒክና ሙያ ዜጎች በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ተቀጥረውም ሆነ በራሳቸው ሥራ ፈጥረው ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና አካባቢያቸውን መቀየር የሚችሉበትን ሙያ የሚያስታጥቅ ከመሆኑም ባሻገር ኢንዱስትሪዎች ባልተቋረጠ መልኩ ክህሎት ያለው የሰው ኃይል እንዲያገኙም የሚያስችል ነው። የስልጠና ዘርፉ የሚያፈራው የሰው ኃይል ከኢንዱስትሪው ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለውና የሀገርንም የኢኮኖሚ አቅጣጫ የመወሰን አቅምም ያለው ነው።

ሆኖም በኢትዮጵያ በነበረው ሁኔታ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፉ በቂ ትኩረት የተሰጠው አልነበረም። የትምህርት ሥርዓቱ በበቂ ሁኔታ ዘርፉን ለመደገፍ ተነሳሽነት ያልነበረው ከመሆኑም ባሻገር ከዘርፉ ተመርቀው የሚወጡትም ተገቢው ዕውቅናና ክብር የሚሰጣቸው አልነበሩም። በዚህም ምክንያት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ለሀገር ማበርከት የሚገባውን አስተዋጽኦ ማበርከት ተስኖት ቆይቷል።

ይህንኑ ችግር በመረዳት በተለይ ከ1994 ወዲህ አዲስ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ከተገባ በኋላ መጠነኛ ለውጦች ቢመዘገቡም ካለው ዕምቅ አቅም አንጻር የተሄደበት ርቀት ግን ብዙም የሚያወላዳ አልበረም፡: በተለይም ተቋማቱ ሲቋቋሙ በቂ ጥናት ተደርጎባቸው አለመቋቋማቸው፤ የአካባቢያቸውን ጸጋ መሠረት አድርገው ወደ ሥራ አለመግባታቸውና ከኢንዱስትሪዎች ጋር ያላቸው ትስስርም የላላ መሆኑ ዘርፉ በሚፈለገው መልኩ እንዳይራመድ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል።

ይህንኑ በመረዳት ከለውጡ ወዲህ መንግሥት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴርን በማቋቋምና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ማዕከላትን በማስፋፋት ለኢኮኖሚው ዕድገት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ በማድረግ ላይ ይገኛል። ሙያ ተቋማት ሲከፈቱ የአካባቢያቸውን ጸጋና ገበያ ማዕከል አድርገው እንዲከፈቱ በማድረግ፤ የተሻሻሉ ስልጠናዎች እንዲሰጡ በማድረግ እና ከኢንዱስትሪዎች ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከር ዘርፉ በሀገር ልማት ውስጥ ተፈላጊ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎንም የተቋማቱን አቅም በማጠናከር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ጭምር በቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንዲተኩ የማበረታታትና የመደገፍ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። ዘርፉ ባገኘው ድጋፍም ቴክኒክና ሙያ ኢንዱስትሪዎቻችን ምርታማነታቸው እንዲያድግ እና ተወዳዳሪነታቸው እንዲጨምር በአመለካከቱም ሆነ በክህሎት የበቃ የሰው ኃይል የማቅረብ ሚናውን ለማሳደግ ተችሏል።

በተሠሩት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችም ለቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ይሰጠው የነበረው የተዛባ አመለካከት መሻሻል አሳይቷል። ዩኒቨርሲቲ መግባት የሚያስችል ውጤት ያላቸው ዜጎች በፍላጎታቸው ወደ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት መግባትም ጀምረዋል። በአጭር ጊዜ የሙያ ባለቤት፣ የሥራ ባለቤት እሆናለሁ የሚለውን አመለካከት መፍጠር ተችሏል።

በአጠቃላይ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፉ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የዕድገትና የብልጽግና ጉዞ አጋዥ መሆን ጀምሯል። በተለይም የመንግሥት ዋነኛ ትኩረት የሆነውን ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካትና ፈጠራን በማበረታታት ረገድ ዘርፉ እየተጫወተ ያለው ሚና ተስፋ ሰጪ ነው።

በአሁኑ ወቅት በርካታ ወጣቶች ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሰልጥነው በመውጣት አዳዲስ ፈጠራዎችን በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ። በተለይም ለዲጂታል ዘርፉ የተሰጠውን ተኩረት በመጠቀም በርካታ ወጣቶች በጀማሪ ሥራ ፈጣሪነት (ሰታርትአፕ) በመሳተፍ ከራሳቸው አልፈው ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል።

ከባለ ሦስት እግሯ ባጃጅ እስከ ተንቀሳቃሽ አውቶሞቢል ፣ ከተንቀሳቃሽ ስልክ እስከ የግብርና ርጭት ማከናወኛ ድሮኖች፤ ኑሮን ከሚያቀሉ የቤት እቃዎች እስከ ግዙፍ ማሽነሪዎች፣ ለሕመም ፈውስ ወሳኝ የሆኑ የሕክምና መገልገያዎች እና ሌሎችም በርካታና ልዩ ልዩ ማሽነሪዎች ድረስ ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ማዕከላት በሚወጡ ወጣቶች እየተሠሩ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና በመወጣት ላይ ይገኛሉ።

ይህ ጅምር ተስፋ ሰጪ ውጤት የሚፈለገውን ግብ እስኪያሳካ በግንዛቤ ፈጠራ፣ በአመለካከት ለውጥ በተግባር የሚደረጉ ትኩረቶችና ድጋፎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል!

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You