ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሰሜን ኮሪያ ገቡ

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሰሜን ኮሪያ ገብተዋል።

ፕሬዚዳንት ፑቲን በትናንትናው ዕለት ፒዮንግያንግ ሲገቡ ደማቅ የተባለ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን ሀገራት፣ ፑቲን ሩሲያ በዩክሬን ለምታካሂደው ዘመቻ ሙሉ ድጋፍ ወደሰጠችው ሰሜን ኮሪያ የሚያደርጉትን ጉብኝት በአንክሮ እየተከታተሉት ነው።

ከ24 ዓመት በኋላ ወደ ፒዮንግያንግ ያቀኑትን ፕሬዚዳንት ለመቀበል በኪም ሁለተኛ አደባባይ በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ ወጥቶ እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል።

ይህን ተከትሎ ፑቲን እና ኪም ንግግር ለማድረግ ወደ ኩምሱሳን ቤተመንግሥት አቅንተዋል።

“ሩሲያ በዩክሬን የምታካሂደውን ዘመቻ ጨምሮ ለሩሲያ ፖሊሲ ያለውን ወጥ ድጋፍ በእጅጉ እናደንቃለን” ሲሉ ፑቲን በውይይቱ መጀመሪያ ላይ መናገራቸውን ሮይተርስ የሩሲያውን ሪያ ዜና አገልግሎት ጠቅሶ ዘግቧል።

ፑቲን ሩሲያ የኢምፔሪያሊስቷ አሜሪካ እና አጋሮቿን የበላይነት እየተዋጋች ነው ብለዋል።

ኪም በበኩላቸው የሰሜን ኮሪያ-ሩሲያ ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መሆኑን ገልጸዋል።

“አሁን ላይ የዓለም ሁኔታ የበለጠ እየተወሳሰበ እና በፍጥነት እየተቀየረ ነው። በእንዲህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ከሩሲያ ጋር ያለንን ግንኙን የበለጠ እናጠናክራለን” ብለዋል።

ኪም አክለውም ሰሜን ኮሪያ “ሩሲያ ሉአላዊነቷን እና ደህንነቷን ለመጠበቅ በዩክሬን የምታደርገውን ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ ሙሉ ለሙሉ እንደግፋለን” ሲሉም ተናግረዋል።

ምዕራባውያን ሰሜን ኮሪያ ሩሲያ በዩክሬን ለምታደርገው ጦርነት ጥቅም ላይ የሚውል የጦር መሳሪያ ታቀርባለች ሲሉ ይከሷታል። ሰሜን ኮሪያ ግን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ነው በማለት በተደጋጋሚ አጣጥላዋለች።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You